የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ሥር በሚገኙ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጣቢያዎች የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ በተደረገ ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በግልገል በለስ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ የመተከል ዞን ፍትሕ መምሪያ፣ ፖሊስ መምሪያና የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች፣ ከየወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የመጡ የፖሊስ አዛዦች፣ የአቤቱታ ቅበላና የወንጀል ምርመራ ሥራ ሂደት አስተባባሪዎች እና የፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
በውይይት መድረኩ በፖሊስ ጣቢያዎች ያለው የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን የተመለከተ የክትትል ሪፖርት ቀርቦ፣ የተለዩ መልካም እመርታዎች እና አሳሳቢ ጉዳዮች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በፖሊስ ጣቢያዎች ለብዙ ጊዜ ታስረው የሚቆዩ ተጠርጣሪዎች ቁጥር መቀነስ፤ በፖሊስና በዐቃብያነ ሕግ መካከል ቅንጅታዊ አሠራሮች መኖር፤ ተጠርጣሪዎች በቤተሰቦቻቸውም ሆነ በማንኛውም አካል እንዲጎበኙ መፈቀዱ እና በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች የቧንቧ ውሃ ለተጠርጣሪዎች እንዲቀርብ መደረጉ በክትትሉ በመልካም እመርታነት ተጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ያለመያዣ ትእዛዝ ወይም መጥሪያ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል፤ ያላግባብ የጅምላ እስር መኖር፤ በፍትሐ ብሔር ደንብ መተላለፍ ሰዎችን ያላግባብ ማሰር፤ ለተጠርጣሪዎች የተያዙበትን ምክንያት እና በሕግ ባለሙያ የመወክል መብት እንዳላቸው ያለመንገር፤ በሕግ በተቀመጠው 48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት አለማቅረብ፤ በፍርድ ቤት ዋስትና የተፈቀደላቸውን ሰዎች አለመፍታት እና በጸጥታ አካላት የሚፈጸም ድብደባ መኖር በተጠርጣሪዎች ላይ ከተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል የተጠቀሱ ናቸው።
ከዚህ ጎን ለጎን በአብዛኛው ፖሊስ ጣቢያዎች ለተጠርጣሪዎች በቂ የመጠጥ እና የንጽሕና መጠበቂያ ውሃ አቅርቦት አለመኖር፣ ለተጠርጣሪዎች የምግብ በጀት አለመያዝ፣ በቂ የሆነ የማቆያ ክፍሎች አለመኖር፤ በማቆያ ክፍሎችና መጸዳጃ ቤቶች የሚስተዋለው የንጽሕና ጉድለት፤ በመጸዳጃ ቤት አጠቃቀም ላይ ገደቦች መኖር፤ የሕፃናትና የአእምሮ ሕሙማን ተጠርጣሪዎች ማቆያ ቦታ የተለየ አለመሆኑ፣ የተጠርጣሪዎች መረጃ በተደራጀና ወጥ በሆነ አግባብ አለመያዝ እንዲሁም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍና እንክብካቤ አለመኖር ክትትል በተደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች በአሳሳቢ ጉዳይነት የተለዩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በኢሰመኮ የቀረበውን የክትትሉ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን እንደሚቀበሉት ገልጸው፣ ለፖሊስ ተቋማት የሚመደበው በጀት ማነስን እና የተለያዩ ጣልቃ ገብነቶችን በተግዳሮትነት አንስተዋል። አክለውም የተነሱ ክፍተቶችን ለማረም በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
የኢሰመኮ አሶሳ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጉርሜሳ በፉጣ በውይይት መደረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በፖሊስ ጣቢያዎች ያለው የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ መሻሻሎች እያሳየ መምጣቱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም በተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች በተጠርጣሪዎች ላይ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማሰቀረት የተጠያቂነት ሥርዓትን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ አክለውም “የፍትሕ አካላት የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብቶች በማክበር እና በማስከበር ረገድ በቁርጠኝነትና በቅንጀት ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል፡፡