የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በድኅረ ግጭት ዐውድ ውስጥ በሚገኙ የትግራይ ክልል እና የተፈጥሮ አደጋዎች ባሉባቸው የሶማሊ ክልል አካባቢዎች የትምህርት ተገኝነት እና ተያያዥ የሕፃናት መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በውይይቱ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የትግራይ እና የሶማሊ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ትምህርት ቢሮዎችና ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች፣ በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ 17 ትምህርት ቤቶች መምህራን እና ርዕሰ መምህራን እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

ኢሰመኮ በክትትሉ የለያቸው ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በዚሁ መሠረት በትግራይ ክልል በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የቤተ-መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ እና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ማእከላት መልሶ ግንባታ ወይም ጥገና ያልተደረገላቸው በመሆኑ ፣ የማስተማሪያ እና የመማሪያ ግብዓቶች እጥረት መኖር እንዲሁም በተወሰኑ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች በተፈናቃዮች መጠለያነት ስለሚያገለግሉ የሕፃናትን በተለይም የአካል ጉዳተኞችን እና ሴቶችን ደኅንነት የጠበቀ፣ ምቹ እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ያሟላ የትምህርት አገልግሎት ለመስጠት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አለመሆናቸው ተጠቅሷል። በተመሳሳይ በሶማሊ ክልል በተደረገ ክትትል በጎርፍ የተጎዱ ትምህርት ቤቶች ተገቢ እድሳት አለማግኘታቸው፣ በክልሉ በድርቅ ምክንያት ከፍተኛ የውሃ እጥረት በመኖሩ ሕፃናት ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል አዳጋች እንደሆነባቸው፣ ንጽሕና የጎደላቸውና የተሰባበሩ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች፣ መስኮትና በር የሌላቸው መማሪያ ክፍሎች እንዲሁም የመምህራን እጥረት በተግዳሮትነት የቀጠሉ ሁኔታዎች መሆናቸው ተመላክቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የውይይቱ ተሳታፊዎች በድኅረ ግጭት፣ በግጭት ወቅት እንዲሁም ድርቅ እና የጎርፍ አደጋ ክስተቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚማሩ ሕፃናት ቀጣይነት ያለው ዘላቂ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ተመጣጣኝ በጀት መመደብ እንዳለባቸው፣ ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትም በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል። በተጨማሪም በኢሰመኮ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ለመፈጸም የሚያግዝ የድርጊት መርኃ ግብር ያዘጋጁ ሲሆን መንግሥት የዓለም አቀፉን የትምህርት ቤቶች ደኅንነት መግለጫ (Safe School Declaration) በመቀበል ሥራ ላይ እንዲያውል ኢሰመኮ ውትወታ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ የውይይቱ ተሳታፊዎች በድርጊት መርኃ ግብር ያቀዷቸውን በተለይም በአጭር ጊዜ ለሚከናወኑ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል። አክለውም በድኅረ ግጭት እና በተፈጥሮ አደጋ ዐውድ ውስጥ በሚገኙ ክልሎችና አካባቢዎች የሚማሩ ሕፃናትን ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል መንግሥት ለሁኔታው አስፈላጊ በጀት ሊመድብ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ የሚያከናውነውን ውትወታ፣ ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።