የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል ከሰኔ 25 እስከ ሐምሌ 2 ቀን እና በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም. እንዲሁም በኅዳር ወር 2017 ዓ.ም. በ5 ማረሚያ ቤቶች እና 18 ፖሊስ ጣቢያዎች ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ግኝቶች ላይ የካቲት 3 እና 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ 2 ዙር የውይይት መድረኮችን አካሂዷል። በውይይት መድረኮቹ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን፣ የማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊዎች፣ የዞን ፖሊስ አዛዦችና መርማሪዎች፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ፍትሕ ቢሮ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በውይይት መድረኩ ክትትል በተደረገባቸው ማረሚያ ቤቶች ትምህርትና ስልጠና ተጠናክሮ መሰጠት መጀመሩ፤ ፍርደኝነትን፣ ዕድሜንና የቅጣት መጠንን መሠረት ያደረገ ለይቶ የመያዝ ሁኔታ መኖሩ፤ ከመደበኛ የወንጀል ሕግ ሂደት ውጪ ታስረው የቆዩ ሰዎች እንዲለቀቁ ለማድረግ አስፈላጊውን ደንብ እና የአፈጻጸም መመሪያ ለማውጣት ሥራ መጀመሩ እንዲሁም ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መጀመሩ በመልካም ጎን የተጠቀሱ ናቸው። በሌላ በኩል ማረሚያ ቤቶቹ በሰው ኃይል እጥረትና በበጀት ማነስ ምክንያት የተለያዩ አገልግሎቶችን በተሟላ መልኩ መስጠት አለመቻላቸው፣ የሕክምና መሣሪያዎች እና ቁሳቁስ እጥረት መቀጠሉ፣ የይግባኝ መብትን ተግባራዊነት በማመቻቸት ረገድ የተሽከርካሪ እጥረትን ጨምሮ ሌሎች ክፍተቶች መኖራቸው እንዲሁም የፍራሽ አቅርቦት አለመኖሩ በተግዳሮትነት ተጠቅሰዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በፖሊስ ጣቢያዎች በተደረገ ክትትል ሁሉም ተጠርጣሪዎች ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸው፣ ተጠርጣሪዎች በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ መቻላቸው፣ ለሴት ተጠርጣሪዎች የተለየ ማቆያ ክፍል መኖሩ እና በሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች የምግብ አቅርቦት መጀመሩ አበረታች መሆኑ ተገልጿል፡፡ በአንጻሩ የሴቶች እና የወንዶች ማቆያ ቦታ በአጥር ያልተለየ መሆኑ፤ የተጠርጣሪዎች ማደሪያ ክፍሎች፣ መታጠቢያና መጸዳጃ ቤቶች የንጽሕና ጉድለት ያለባቸው መሆኑ፤ የተሟላ የቅሬታ ማስተናገጃ ሥርዓት አለመኖሩ፤ በተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች በተጠርጣሪዎች ማቆያ ክፍሎች በቂ መብራት አለመኖሩ፤ እንዲሁም የማደሪያ ክፍሎች ከተጠርጣሪዎች ቁጥር አንጻር ተመጣጣኝ አለመሆኑ በክትትሉ የተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች አብዛኛዎቹን ግኝቶች እንደሚስማሙባቸው እና ከክትትል ሥራው በኋላ የተሻሻሉ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ከኢሰመኮ ባለሙያዎች ጋር በተዘጋጀው የድርጊት መርኃ ግብር መሠረት ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተወልደብርሃን ተስፋዓለም ተቀራርቦ መሥራት ለሰብአዊ መብቶች መከበር የጎላ አስተዋጽዖ እንዳለውና በኢሰመኮ የቀረበው የክትትል ሪፖርት ክፍተቶችን ለመለየት እና ተግባራዊ ግብረ መልስ ለመስጠት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃፍቱ ሚኪኤለ በበኩላቸው ፖሊስ ባለው የሰው ኃይልና በጀት የተነሱ ክፍተቶችን ለማረም እንደሚሠራ ገልጸው፣ ከሰው ኃይልም ሆነ ከበጀት እጥረት ጋር ግንኙነት የሌላቸው እንደ ያልተመጣጠነ የኃይል አጠቃቀም፣ ከቤተሰብና ከጠበቃ ጋር አለማገናኘት የመሳሰሉት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቆም እንዳለባቸው በአጽንኦት አስረድተዋል። በተጨማሪም ኮሚሽነሩ ፖሊስ ጣቢያዎች ኃላፊዎች ችግሮችን በዳሰሳ ጥናት ለይተው ለክልሉ ወረዳ አስተዳደር በማቅረብ በጀት በማስያዝ ችግሮችን እልባት ለመስጠት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ከክልሉ ተቋማት በተለይም ከማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ጋር በቅርበት ለመሥራት እንዲሁም የመቐለ ጽሕፈት ቤት ሥራ መጀመሩ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ዕቅድ ሊፈጸሙ የሚገባቸው ተግባራትን በመለየት ኢሰመኮ አፈጻጸሙን ለመከታተል እና ድጋፍ የሚያደርግበትን መንገድ በተሻለ ሁኔታ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም “የታራሚዎችን እና የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብቶች ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስታዋጽዖ ማድረግና በቅንጅት መሥራት አለባቸው” ብለዋል።