የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከግንቦት ወር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ የሚታሰበውን ዓለምአቀፍ የወላጆች እና አሳዳጊዎችን ቀን አስመልክቶ ባስተላለፈው ጥሪ፣ የፌዴራል እና የክልል የቤተሰብ ሕጎች በየጊዜው የሴቶችን እና የሕጻናትን ሰብአዊ መብቶች ከማስከበር አኳያ ሊፈተሹ እንደሚገባ ገለጸ። ከግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ዓመታዊ የእቅድ አተገባበር ግምገማ እና ዝግጅት ስብሰባ በማድረግ ላይ የሚገኘው የኮሚሽኑ የሴቶች እና ሕጻናት መብቶች ዲፓርትመንት ዘንድሮ “ምስጋና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ወላጆች እና አሳዳጊዎች” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወላጆች እና አሳዳጊዎችን ቀን አስቦ ውሏል።
የስብሰባው ተሳታፊዎች የፌዴራልም ሆነ የክልል የቤተሰብ ሕግ የሴቶችንና ሕጻናትን መብቶች ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጾ ቢኖረውም፣ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መርሆዎች እና ድንጋጌዎች ጋር የሚጣረስ ከሆነ እነዚህን የማኅበረሰብ ክፍሎች ለድርብ ተጋላጭነት ሊዳርግ የሚችል መሆኑን አስረድተዋል። በተመሳሳይ መልኩ የሕጻናትን ስብእና በማነጽና ሰብአዊ ክብርን በማስተማር ረገድ ወላጆች እና አሳዳጊዎች ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚወስዱ ለማስታወስና ተገቢውን እውቅና ለመስጠት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የተሰየመው ይህ ቀን፣ በተለይም በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም. የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የወላጆችን እና የአሳዳጊዎችን ሚና ጎልቶ እንዲታይ ማድረጉ ቀኑን ለማሰብ በተዘጋጁ የተለያዩ አህጉራዊና ዓለምአቀፍ መድረኮች እየተገለጸ ነው።
በአገር አቀፍ ደረጃም ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተጨማሪ በትግራይ ክልል ያለውን ጦርነት ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በግጭቶች እና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ሳቢያ ከመኖሪያ ቦታቸው የተፈናቀሉ፣ የተሰደዱ፣ የቤተሰብ አባላቶቻቸውን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ያጡ፣ በጎዳና ለመኖር፣ ለጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች እና ለተለያዩ አካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳቶች የተዳረጉ ሕጻናት እና አሳዳጊዎች መኖራቸው፣ በእነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ሕጎች እና ፖሊሲዎችን ወቅታዊነትና አግባብ ዳግም ለመፈተሽ የሚያስገድድ ነው።
ስለሆነም በ2014 ዓ.ም. የሚያካሂዳቸውን ዝርዝር ተግባራት እና እቅድ በመወያየት ላይ የሚገኘው የኢሰመኮ የሴቶች እና ሕጻናት መብቶች ዲፓርትመንት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚያከናውናቸው የሕግ፣ የፖሊሲ፣ የአተገባበር እና የመዋቅር ማሻሻያዎች ምክረ ሃሳብ እና ግፊት ስራ ካቀዳቸው ዋና ዋና መስኮች አንዱ የፌዴራል እና የክልል የቤተሰብ ሕግ መሆኑን ገልጿል። በአንድ በኩል የክልል የቤተሰብ ሕጎች እንደየክልሉ በተለያዩ የአተገባበር ደረጃ የሚገኙ በመሆናቸው የሚታቀዱ ተግባራት ከዚሁ ጋር የሚናበቡ እና የሚጣጣሙ ይሆናሉ። ለምሳሌ፣ በሶማሌ፣ በአፋር እና በሲዳማ ክልሎች የቤተሰብ ሕግ ባለመደንገጉ አልያም በመረቀቅ ሂደት ላይ በመሆኑ ሕጎቹ ወቅታዊውንና የክልሎቹን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አውድ ያገናዘቡ፣ እንዲሁም የሴቶችን እና የሕጻናትን ሰብአዊ መብቶች የጠበቁ እንዲሆኑ ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር እና ግፊት ለማድረግ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል።
በሌላ በኩል፣ የቤተሰብ ሕግ ባጸደቁ ክልሎች የሕጉን አተገባበር፣ በተለያዩ የሕግ አስፈጻሚ አካላት መካከል ያለውን የአረዳድ እና የአሰራር ልዩነት፣ ሕጉ በሴቶች እና ሕጻናት መብቶች ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ እና አዎንታዊ ተጽእኖ፣ በክልሉ ካለው ወቅታዊ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ጋር ያለውን ክፍተት እና የመሳሰሉትን ተያያዥ ጉዳዮች በተገቢው መልኩ ማጥናት አስፈላጊ ይሆናል። ይህንን በተመለከተም፣ ለምሳሌ የቤተሰብ ሕግ ባጸደቁ አንዳንድ ክልሎች የቤተሰብ ሕጉን ድንጋጌዎች በመተርጎም አኳያ በፍርድ ቤቶች ውስጥ ጭምር የተለያየ አሰራር መኖሩ፣ ሕጉ ነባራዊ ማኅበራዊ ጎጂ ልማዶችን ያስቀረበት አጋጣሚዎች እንዳሉ ሁሉ በእነዚህ ልማዶች ላይ ምንም አይነት ለውጥ ማምጣት ያልቻለባቸው ወይም የተባባሰባቸው ሁኔታዎች መኖራቸው፣ እንዲሁም ሕጉ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት አናሳ መሆኑ በኮሚሽኑ ዓመታዊ ስብሰባ ተሳታፊዎች ከተነሱ ነጥቦች መካከል ናቸው።
ይህንኑ ባገናዘበ መልኩ የፌዴራል እና የተለያዩ ክልሎች የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ ኮሚሽኑ የሚያተኩርባቸውን የሕግ እና የፖሊሲ ማእቀፍ ቀረጻና ማሻሻያ የማድረግና የመተግበር ግፊት ስራዎች ተለይተዋል። ሆኖም ግን ዓለምአቀፍ የወላጆች እና የአሳዳጊዎች ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት ጥሪ፣ እስከ ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚቆየው ዓመታዊ የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕጻናት መብቶች ዲፓርትመንት ተሳታፊዎች፣ የፌዴራል እና የክልሎችን የቤተሰብ ሕግ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችና ድንጋጌዎች ለማጣጣምና የሴቶችን እና የሕጻናት መብቶችን የሚያስጠብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በቀጣይነት በሚደረጉ ግፊቶች የሚመለከታቸው መንግስታዊ እና የኃይማኖት ተቋማትን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና ማኅበራዊ አደረጃጀቶችን ጨምሮ መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻዎች ተሳትፎ እና ርብርብ እንደሚያሻ ገልጸዋል።