የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብአዊ መብቶች ማእከል ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች አተገባበር ላይ ትኩረት ያደረገ ብሔራዊ የፖሊሲ ምክክር መድረክ ነሐሴ 22 እና 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። መድረኩ “በኢትዮጵያ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ግዴታዎችን የማክበር ሁኔታ፤ መሻሻል ወይስ ወደ ኋላ መመለስ?” (‘The Status of Compliance with Socio-economic Rights Obligations in Ethiopia – Progression or Regression?’) በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ፖሊሲዎች፣ ክፍተቶችና ተግዳሮቶች እንዲሁም የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ያተኮረ ነበር። በምክክር መድረኩ የፌዴራል እና የክልል ምክር ቤቶች ተወካዮች፣ የትምህርት፣ የጤና እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እና የትምህርት ማኅበረሰብ አባላት፣ የክልል ቢሮዎችን ጨምሮ የሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የምክክር መድረኩ በዋነኝነት የጤና፣ የመኖሪያ ቤት፣ የትምህርት፣ የሠራተኞች እንዲሁም የምግብ መብቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች አተገባበር ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን እና የፖሊሲ ክፍተቶችን መለየትን፤ የመብቶቹን ተፈጻሚነት ለማሻሻል የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦችን ማቅረብን እንዲሁም በመንግሥት ተቋማት፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና በትምህርት ማእከላት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ መብቶችን አተገባበር ለማሻሻል ያለመ ነው።
በምክክር መድረኩ ከኢሰመኮ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን እና ባለሙያዎች ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ አቀራረብን፤ የመኖሪያ ቤት፣ የምግብ እና የሠራተኞች መብቶችን፤ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን የተመለከቱ የመንግሥት ግዴታዎችን እንዲሁም የፖሊሲ እና አተገባበር ክፍተቶችን የተመለከቱ ጽሑፎች ቀርበዋል። በተጨማሪም የትምህርት እና የጤና መብቶች፣ የፖሊሲ እና የአተገባበር ደረጃን የሚያመላክቱ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ መብቶች የሕግ፣የፖሊሲ እና የአተገባበር ማዕቀፎችን ከማሻሻል አንጻር እየተወሰዱ ስላሉ እና በቀጣይ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ያነሱ ሲሆን፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ከሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሚመነጩ ግዴታዎችን ተፈጻሚነት በተመለከተ የፌዴራል እና የክልል ሕግ አውጪ እንዲሁም ፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሕግ አስፈጻሚ አካላት የግዴታዎችን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ሊወስዷቸው ስለሚገቡ እርምጃዎች እና በሂደቱም ታሳቢ ሊያደርጓቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ሐሳባቸውን ሰጥተዋል። በተጨማሪም፣ በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዚህ የሰብአዊ መብቶች ዘርፍ በቂ ትኩረት በመስጠት ክትትላቸውን እንዲያጠናክሩ ሐሳብ ቀርቧል።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው ግጭት እና አለመረጋጋት፣ ድርቅ እና መሰል አደጋዎች ከሌሎች ክስተቶች ጋር ተዳምረው የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች በተለይም የምግብ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የትምህርት፣ የጤና እና የሥራ መብቶች በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። አያይዘውም የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ እና ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች በቂ ትኩረት በሚሰጥ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን እንዲሁም ተገቢውና አስፈላጊው የፖሊሲ እና መዋቅራዊ ለውጦችን ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል።