የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር ክልል በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ባካሄደው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ሐምሌ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለን ጨምሮ የክልሉ ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የክልሉ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል፣ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት፣ የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ እና ከማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በውይይቱ ኢሰመኮ ከጥቅምት 25 እስከ ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በ14 ፖሊስ ጣቢያዎች እና በ2 ማረሚያ ቤቶች ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሁም ከመጋቢት 24 እስከ ሚያዚያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በ17 ፖሊስ ጣቢያዎች እና በ1 ማረሚያ ቤት የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም በድምሩ በ31 ፖሊስ ጣቢያዎች እና 3 ማረሚያ ቤቶች ላይ ያካሄደው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሪፖርት ቀርቧል። ክትትል በተደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች በተጠርጣሪዎች ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በፈጸሙ የፖሊስ አባላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱ፣ በአብአላ የፖሊስ ጣቢያ የሴት ተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ መሻሻሉ፣ በገዋኔ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት ለዐቅመ አዳም ከደረሱ ሰዎች ተለይተው መያዛቸው እንዲሁም በዱብቲ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ የውሃ መስመር ጥገና በፖሊስ አባላት መዋጮ ከመሠራቱም በላይ በኤሊ ውሃ ከተማ ንኡስ ፖሊስ ጣቢያ የተጠርጣሪዎች ማቆያ መገንባቱና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማሟላቱ መሻሻል የታየባቸው ጉዳዮች ናቸው። በተመሳሳይ፣ በማረሚያ ቤቶች 24.70 ብር የነበረው የታራሚዎች የቀን በጀት በእጥፍ ተሻሽሎ 50 ብር መደረጉ፣ በመደኃኒት አቅርቦትና በሕክምና አገልግሎት ረገድ በተለይም በሃሪ ረሱ ማረሚያ ቤት ከፍተኛ መሻሻል መኖሩ እንዲሁም በክልበቲ ረሱ እና ሃሪ ረሱ ማረሚያ ቤቶች የሙያ ስልጠና መጀመሩ አበረታች መሆኑ ተገልጿል።
በሌላ በኩል በክትትሉ የተለዩ ክፍተቶች በውይይቱ ላይ የቀረቡ ሲሆን በፖሊስ ጣቢያዎች በጾታ የተለየ ማቆያ ክፍል የሌለ በመሆኑ ሴት ተጠርጣሪዎች ከማደሪያ ክፍል ውጪ ወይም ደጅ ላይ እንዲያድሩ መደረጉ እንዲሁም በበርካታ ፖሊስ ጣቢያዎች የመታጠቢያ እና መጸዳጃ አገልግሎት አለመኖሩ ተነስቷል። በተጨማሪም፣ በማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን በፍርድ ዐይነት፣ በዕድሜ፣ እንዲሁም ታራሚዎችን ከተጠርጣሪዎች፣ ተላላፊ በሽታ ያለባቸውን እና የተለየ አያያዝ የሚሹ እንደ የአእምሮ ሕመምተኞችን ከሌሎች ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች ለይቶ አለመያዝ፣ በክልበቲ ረሱ ማረሚያ ቤት የታራሚዎች ማደሪያ ክፍሎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣ በቂ ብርሃን እና አየር የማያስገቡ፣ የተጨናነቁ እንዲሁም ንጽሕና እና ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሌላቸው መሆናቸው ተጠቁሟል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሳ አብዶ በኢሰመኮ የቀረበው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትል ሪፖርት የማረሚያ ቤቶችን እና የፖሊስ ማቆያዎችን መልካም ጎኖች እና ችግሮች በሚገባ ያሳየ መሆኑን ገልጸው፣ በተሰጡት ምክረ ሐሳቦች መሠረት ችግሮቹን ለመቅረፍ እንደሚሠሩ ተናግረዋል። በተጨማሪም በክልል ደረጃ ወንጀል ነክ ነገር ውስጥ የገቡ ሕፃናት ማቆያ ለማደራጀት ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮን ጨምሮ ከክልሉ ፍትሕ አካላት ጥምረት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢስማኢል መሃመድ በበኩላቸው ኢሰመኮ የሚያደርገው ክትትል ለክልሉ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ መሻሻል ደጋፊ መሆኑን ገልጸው የማረሚያ ቤቶች በጀት ላይ ማሻሻያ መደረጉ ለሰብአዊ መብቶች መከበርና መሻሻል የጎላ ሚና ያለው መሆኑን፤ በቀጣይም ኢሰመኮ የለያቸውን ክፍተቶች በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች መሠረት በአፋጣኝ ሊፈቱ የሚችሉትን በመለየት መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ገዶ ሃመሎ በሰጡት አስተያየት ክልሉ በግጭት ውስጥ የነበረ እና የበጀት ውስንነት ያለበት ቢሆንም ኢሰመኮ ከሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል በተቋማቱ በጀት እና አስተዳደራዊ ዐቅም ሊተገበሩ የሚችሉትን ለይተው እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል። አያይዘውም የክልሉ መንግሥት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እንዲሻሻል የፍትሕ ሥርዓቱ አካል የሆኑትን የፖሊስ ኮሚሽንን እና የማረሚያ ቤቶችን ዐቅም በፈቀደ መጠን እንደሚደግፍ ገልጸዋል፡፡
ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ የታራሚዎችንና የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል ኢሰመኮ ለፖሊስ አባላት ተደጋጋሚ ሥልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። አክለውም በቀጣይ በባለድርሻ አካላት ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገቡ ምክረ ሐሳቦች በታቀደው ጊዜ ስለመፈጸማቸው ኢሰመኮ በቅርበት እንደሚከታተል እና የውትወታ ሥራውንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡