የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ለሚገኙ የፖሊስ አባላት፣ ወጣቶች፣ ሲቪክ ማኀበራት እና የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ አካላት በመጋቢት እና በሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ስልጠና ሰጥቷል። የተሰጡት ስልጠናዎች ሰላም፣ አብሮነት፣ መቻቻል እና የሽግግር ፍትሕ፤ በወንጀል የተጠረጠሩና የተያዙ ሰዎች መብቶች፤ በአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች፤ በሴቶች እና ሕፃናት መብቶች፤ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡
- ሰላም፣ አብሮነት፣ መቻቻል እና የሽግግር ፍትሕ ስልጠና (ከመጋቢት 11 እስከ 15 እንዲሁም ከመጋቢት 25 እስከ 29 ቀን 2015 ዓ.ም.)
ኮሚሽኑ ከሰላም፣ አብሮነት፣ እና መቻቻል አንጻር እንዲሁም የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ የአምስት ቀናት ስልጠና በሁለት ዙር ሰጥቷል። በስልጠናው ከወልዲያ፣ ሰመራ፣ ጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ወሊሶ፣ አሰላ፣ አምቦ፣ ሻሸመኔ፣ ሶዶ፣ አርባ ምንጭ፣ ጅግጅጋ፣ ቦንጋ ከተሞች እና ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ 304 የወጣት ማኀበራት መሪዎችና አባላት ተሳትፈዋል፡፡
የስልጠናው ዋና ዓላማ ወጣቶች ሰብአዊ መብቶችን እና የሰብአዊ መብቶች እሴቶችን መሠረት ያደረገ ዕውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት በመገንባትና የሽግግር ፍትሕ ጽንሰ ሐሳብና መርሖችን እንዲገነዘቡ በማድረግ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በጋራ በሰላም እንዲኖሩ ማስቻል፤ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ያሉ የሐሳብ ልዩነቶችን መሠረት አድርገው የሚከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመከላከል እና ዘላቂነት ያለው ሰላም ለማምጣት በሚያግዙ ሥራዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ማብቃት ነው፡፡
ስልጠናው ሰብአዊ መብቶች እና በግጭት ወቅት ስለሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች፣ የራስን መብት ለማስጠበቅ በሚደረግ እንቅስቃሴ የሌሎችን ሰዎች መብቶች ማክበርና ማስከበር አስፈላጊነትን የሚያስገነዝቡ የሁኔታ ትንተና እና የቡድን ውይይቶች የተካተቱበት ነበር፡፡
2. በወንጀል የተጠረጠሩና የተያዙ ሰዎች መብቶች ስልጠና (ከመጋቢት 4 እስከ 8 ቀን 2015 ዓ.ም.)
ኢሰመኮ በወንጀል የተጠረጠሩ እና የተያዙ ሰዎች ሰብአዊ መብቶቻቸው ሳይሸራረፉ እንዲከበሩላቸው ለማስቻል በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ቀጥተኛ ተሳታፊ ለሆኑ በአማራ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ለሚገኙ 61 የፖሊስ አመራሮችና አባላት የተጠረጠሩ እና የተያዙ ሰዎች መብቶችን በተመለከተ በኮምቦልቻ እና በጅማ ከተሞች የአምስት ቀናት ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ኮሚሽኑ በሰጠው ስልጠና የፖሊስ አመራሮችና አባላት ስለሰብአዊ መብቶች ያላቸውን ዕውቀት፣ አመለካከት እንዲሁም ክህሎት እንዲያዳብሩ እና ለሰብአዊ መብቶች መከበር የሙያ እና የሕግ ግዴታቸውን በማክበር ዓይነተኛ ሚና እንዲጫወቱ እገዛ አድርጓል፡፡
ስልጠናው ሰብአዊ መብቶችን ማክበርና ማስከበር ከፖሊስ ሥራ ጋር ያላቸውን ትስስር አስመልክቶ ሰልጣኝ የፖሊስ አባላት በዋናነት መሠረታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች እሴቶች ማለትም ሰብአዊ ክብር፣ እኩልነት፣ ነጻነት፣ አድልዎ አለመፈጸም እና ኀላፊነት የመሳሰሉትን አስመልክቶ ያላቸውን ዕውቀትና አመለካከት ለማዳበር የሚያስችሉ ክንውኖችን ያካተተ ነበር፡፡
3. የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ስልጠና (ከመጋቢት 18 እስከ 22 ቀን 2015 ዓ.ም.)
ኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞችን ሰብአዊ መብቶች ለማስከበርና ለማስፋፋት የሚረዱ ስልጠናዎችን በባሕር ዳር እና በድሬዳዋ ከተሞች ለሚገኙ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት አመራሮች እና አካላት ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው 53 አካል ጉዳተኞች እና በዘርፉ ላይ የሚሠሩ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ ኮሚሽኑ በሰጠው ስልጠና በዓለም አቀፍ እና በብሔራዊ ደረጃ የተደረሰ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ላይ ዕውቅና የተሰጣቸው የሰብአዊ መብቶች እሴቶች እና መርሖችን በሰፊው በመዳሰስ መብቶቹን ማስገንዘብና ማስፋፋት ተችሏል፡፡
4. የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ስልጠና (ከመጋቢት 18 እስከ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲሁም ከሚያዝያ 16 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም.)
ኮሚሽኑ የሴቶች መብቶች ተግባራዊነትን ለማስፋፋት በአዲስ አበባ ከተማ፣ በጉራጌ፤ በሃዲያ እና በስልጤ ዞኖች የማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለሚሠሩ 29 ወንድ እና 31 ሴት በድምሩ ለ60 የመንግሥት ተቋማት እና ለሲቪክ ማኅበረሰብ ባለሙያዎችና ተወካዮች የአምስት ቀናት የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ የሕፃናት መብቶችን በማስጠበቅ ረገድ ባለድርሻ ለሆኑ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዲሁም ከኦሮሚያ ማኅበራዊ እና ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ለተውጣጡ 23 ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
ስልጠናው ስለሕፃናት እና ሴቶች መብቶች ዕውቀት ማስጨበጥ፣ የሰብአዊ መብቶች እሴቶችን መሠረት ያደረገ አመለካከትን ማጎልበት እንዲሁም ተሳታፊዎች ያገኙትን ዕውቀትና አመለካከት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ማስቻል ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ በስልጠናውም ተሳታፊዎች በዚህ ወቅት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚስተዋሉ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ጥሰቶችን መለየት እና መወሰድ ስላለባቸው የእርምት እርምጃዎች በቡድን ውይይት ማዳበር የቻሉበት ነበር፡፡
5. የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ስልጠና (ከሚያዝያ 16 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም.)
ኮሚሽኑ በአፋር ብሔራዊ ክልል አወሲ፣ ዱፍቲ እና ኪልበቲ አካባቢዎች ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አገልግሎት ለሚያቀርቡ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ባለሞያዎች የአምስት ቀን ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው 24 ወንድ እና 5 ሴት በአጠቃላይ 29 ሰልጣኞች የተሳተፉበት ሲሆን የስልጠናው ዓላማ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞች በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያላቸውን ዕውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎት በማዳበር፣ ለተፈናቃዮች የሚሰጡት አገልግሎት ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡