የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍነውን ሁለተኛውን የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ባለ 106 ገጽ ሪፖርት ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ ሪፖርቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የተላከ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
የትጥቅ ግጭቶችን በሰላም በመፍታት ረገድ አበረታች ጅማሮዎች መኖራቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አስታውሶ፣ ዘላቂ እና በሀገራዊው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ተጨባጭ መሻሻል እንዲያመጡ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የሚደረጉ የሰላም ጥረቶች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉና፣ በተለይም ተጎጂ ማኅበረሰቦችን በማሳተፍ ረገድ አካታች ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስቧል። በሕግ እና ፖሊሲ ማሻሻያዎች፣ የኮሚሽኑን ምክረ ሐሳቦች ተቀብሎ በማስፈጸም ረገድ እና በተለይም ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መፍትሔ በማስገኘት ረገድ የታዩ መልካም እመርታዎች ቢኖሩም፣ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በተለያየ ወቅት የሚያገረሹ ወይም በአዲስ መልኩ የሚከሰቱ የትጥቅ ግጭቶች እና ጥቃቶች በሕይወት የመኖር እና የመንቀሳቀስ መብቶች ላይ እያደረሱት ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ በአጠቃላይ ሀገራዊው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ላይ ትርጉም ያለው መሻሻል እንዳይኖር እንቅፋት መሆኑን የሚመለከታቸው አካላት አጽንዖት እንዲሰጡት ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
ሪፖርቱ ኢሰመኮ የትኩረት መስክ አድርጎ በለያቸው የሲቪልና የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ የሴቶችና የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን፣ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች መብቶች ዘርፎችን የሚዳስስ ሲሆን፤ በተጨማሪም በጥበቃ ሥር ያሉ እና የተያዙ ሰዎች መብቶች ሁኔታን፣ ኮሚሽኑ ባስተናገዳቸው የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ አቤቱታዎች እና አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች ግዴታዎችን ከመወጣት አንጻር ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታንም በዝርዝር አብራርቷል።
በተለይ በትጥቅ ግጭት ዐውድ ውስጥ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ኃይሎች ከሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተጨማሪ፣ በጸጥታ እና ደኅንነት አካላት የሚፈጸሙ አስገድዶ የመሰወር፣ የዘፈቀደ እና ሕገ ወጥ እስር እንዲሁም በሰላማዊ ሕዝባዊ ስብስቦች ወቅት ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል በመጠቀም የሚደርሱ ጥሰቶች በሰዎች ላይ አስከፊ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። በሚዲያ፣ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ በማኅበረሰብ አንቂዎች እና ሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ያነጣጠሩ ወከባ እና እስሮች፣ የጸጥታ ችግሮችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶችና አካባቢዎች ጊዜያዊም ሆነ ረዘም ያለ ጊዜ የቆዩ የመንቀሳቀስ ገደቦች በእራሳቸው የመብት ጥሰቶች ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ በሰዎች ላይ እያደረሱ ያሉት ሥጋት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ሀገራዊውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አሳሳቢ ካደረጉ ሁኔታዎች መካከል ናቸው፡፡
ዓመታዊ ሪፖርቱ ካለፈው ዓመት አንጻር ግጭቶችን በሰላም በመፍታት ረገድ አበረታች ጅማሮዎች ቢስተዋሉም፣ በሪፖርት ዘመኑ ተለዋዋጭ እና ዘርፈ ብዙ የመብቶች ጥሰቶች በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች እና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት መፈጸማቸውን አብራርቷል። የዘፈቀደ እስርና ተገቢ ያልሆነ አያያዝ፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል አጠቃቀም፣ በሚዲያና ተቃዋሚዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፣ ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀሰ መብት ላይ የተጣለ የዘፈቀደ ገደብ፣ ሕጋዊ ሂደትን ያልተከተለ የቤቶች ፈረሳ፣ በግዳጅ ማስነሳትና በኑሮ ውድነት የተነሳ የደረሰው እንግልትና የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲሁም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም አሳሳቢነታቸው ከቀጠሉ ጉዳዮች ውስጥ እንደሚገኙ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. በተደረገው ዘላቂ ተኩስ ማቆም እና የሰላም ስምምነት መሠረት ማብቃቱና፤ ኮሚሽኑና የተ.መ.ድ. ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በጣምራ ባካሄዱት ምርመራ ከሰጧቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል አንዱ የሆነውን የሽግግር ፍትሕ የሰላም ስምምነቱ አካል እንዲሆን መደረጉ፣ ይህንንም ተከትሎ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ የፖሊሲ አማራጮች (Green Paper) ማዘጋጀቱ እና ማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች ማካሄድ መጀመሩ፣ እንዲሁም በተወሰነም ደረጃ ቢሆን የተጀመሩ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች፣ የተቋረጡ ማኅበራዊ እና ሌሎች አገልግሎቶች መመለሳቸው፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸው በሪፖርቱ ከተጠቀሱ መልካም እመርታዎች መካከል ናቸው።
ሆኖም በተለይም በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. የተጀመረው የክልሎችን ልዩ ኃይሎች መልሶ የማደራጀት እንቅስቅሴ ተከትሎ፣ በተለይም በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች እና የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር፣ በኦሮሚያ ክልል በግጭት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣት፣ እንዲሁም በሁሉም ክልሎች ዘላቂ መፍትሔ ባለማግኘታቸው በተደጋጋሚ በሚያገረሹ ግጭቶች ሳቢያ የሚደርሰው ሞት፣ አካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የመሠረተ ልማቶች እና የንብረት ውድመቶች አሁንም አሳሳቢነቱ መቀጠሉ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ ክትትል ባደረገባቸው 49 ማረሚያ ቤቶች እና 346 የፖሊስ ጣቢያዎች በጥበቃ ሥር ያሉ እና የተያዙ ሰዎች አያያዝን በተመለከተ የታዩ በርካታ መሻሻሎች እና ጅማሮዎች በሪፖርቱ ተመላክተዋል፡፡፣ ሆኖም የዘፈቀደ እና ሕገ ወጥ እስሮች፣ አስገድዶ መሰወር፣ የዋስ መብትን አለማክበር፣ ድብደባና የማሰቃየት ድርጊቶች መፈጻመቸው ተጠቁሟል፡፡
በጦርነት እና በትጥቅ ግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም፣ እንዲሁም ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ከመስጠት አስፈላጊነት በተጨማሪ፣ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣት በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መብቶች ላይም ከፍተኛ ጫና እና ጥሰት አስከትሏል። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት እና ታዳጊዎች ከትምህርት ውጪ ሆነዋል፣ የጤና እና የማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተሟላ ዐቅማቸው አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ላይ የደረሰው ጉዳት ቀጥሏል፡፡ በግብርና እና በተያያዥ ሥራዎች የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ወደ ምርታማነት እንዳይመለሱ የማዳበሪያና የሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች እጥረት አግዷል። በዚህም ሳቢያ የድጋፍ ፈላጊዎች ቁጥር ጨምሯል። በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እና በሶማሊ ክልሎች እና በአጎራባች አካባቢዎች ለበርካታ ወራት የቆየው ድርቅ አሁንም ዘላቂ ምላሽ የሚሻ ነው። እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ መሠረታዊ በሆኑ የምግብ እና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ የሚታየው ዋጋ መናር እና በአሁኑ ወቅት ያለው አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሰዎችን ለከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየዳረጉ መሆኑ ኮሚሽኑ አሳሳቢ ጉዳዮች ብሎ ካመላከታቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ በተለይም አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ሴቶች እና ሕፃናት እንዲሁም በመፈናቀል እና በስደት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ለተደራራቢ የመብቶች ጥሰት ተጋላጭነታቸው በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር ያስታወሰው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ፣ በግጭትና በጦርነት ዐውድ ውስጥ ለደረሱ ጾታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶች ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ለጥሰቱ ሰለባዎችም ተገቢውን መፍትሔ ከማስገኘቱ ጥረት ባልተናነሰ መልኩ፣ የአካል ጉዳተኝነት እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጉዳይ የመንግሥትን ትኩረት እንዲያገኝ አሳስቧል። በተጨማሪም በሽግግር ፍትሕ ሂደቱም ሆነ በማናቸውም ሀገራዊ ሂደቶች የአካል ጉዳተኞችን፣ የሴቶችን፣ የአረጋውያንን እና የተጎጂ ማኅበረሰቦችን ትርጉም ባለው መልኩ በማሳተፍ ረገድ አሁንም የረዥም ጊዜ ጥረት የሚፈልግ በመሆኑ፣ የመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትም አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
በመጪው በጀት ዓመት የኮሚሽኑንም ሆነ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ቀጣይ ክትትል የሚሹ ዋና ዋና የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች የተመላከቱ ሲሆን፣ ለሰላም እና ደኅንነት እጦት እና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሥር መንስኤ ለሆኑ ጉዳዮች አሳሳቢነታቸውን የሚመጥን ጥረት እና አፈጻጸም ከማድረግ በተጨማሪ መንግሥታዊ በሆኑ መዋቅሮች የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የመከላከል አቅምን ማጠናከር የሚሉት ተካትተዋል። በተጨማሪም በክልሎች መካከል እና በአንድ ክልል ውስጥ ያሉ አስተዳደራዊ፣ የመዋቅር እና የድንበር መካለል ጥያቄዎች ለተጨማሪ ግጭት እና የሕይወት መጥፋት ምክንያት እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል ተጠቅሰዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በ2015 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ ባስተላለፉት መልዕክት “ሰዎች በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ ከቦታ ቦታ በነጻነት የመንቀሳቀስ እና የመሥራት መብቶቻቸው ባልተከበረበት ሁኔታ የተመዘገቡ መልካም ለውጦች ዘላቂነት አይኖራቸውም” ብለው፣ የትጥቅ ግጭቶችን ዘለቄታዊ በሆነ መልኩ ለማስቆም እና የሰዎችን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ መከናወን ካለባቸው ተግባራት በተጨማሪ የፍትሕ እና የአስፈጻሚ አካላት ተቋማት በቁርጠኝነት የሕግ የበላይነትን ሊያስከብሩ” እንደሚገባ አሳስበዋል።