የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 123 ፖሊስ ጣቢያዎች ባካሄደው የሰብአዊ መብቶች ክትትል በለያቸው ግኝቶች እና በሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ እና የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን ተወካዮች እንዲሁም የዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዦችና ምርመራ ክፍል ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በውይይቱ የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ክትትል በተደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች በወንጀል ተጠርጥረው የሚያዙ ሰዎች በአብዛኛው በሕጋዊ መንገድ መስተናገዳቸው፣ የተጠርጣሪዎች መረጃ አያያዝ መሻሻል ማሳየቱ፣ ስልታዊ የሆነ አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት አለመኖሩ፣ የተጠርጣሪዎች በቤተሰብ የመጎብኝት መብት ተግባራዊነት መሻሻሉ እና በተጠርጣሪዎችና በሌሎች ሰዎች ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ የፖሊስ አባላት ላይ የወንጀል እና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ከመውስድ አንጻር አበረታች ጅምሮች መኖራቸው በክትትሉ ከተለዩ አበረታች ጉዳዮች መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል፣ በተለይም “በወቅታዊ ሁኔታ” በሚል የሚያዙ ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓት ውስጥ ወይም ሙሉ በሙሉ ፍርድ ቤት አለማቅረብ፣ በፍርድ ቤት ነጻ የተባሉ ወይም የዋስትና መብታቸው የተጠበቀላቸው እንዲሁም የምርመራ መዝገባቸው በዐቃቤ ሕግ አያስከስስም ተብሎ የተዘጋ ሰዎችን አስሮ ማቆየት፣ በወንጀል ተጠርጣሪዎች ምትክ የቤተሰብ አባላትን ማሰር፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በአስተዳደር አካላት፣ በመከላከያ ሰራዊት እና በፖሊስ አባላት ሰዎችን ከሕግ ውጭ ማሰር፣ አልፎ አልፎ ተጠርጣሪዎችን ከፖሊስ ጣቢያ ውጭ በኢመደበኛ ቦታዎች እንዲቆዩ ማድረግ እና በተወሰኑ ፖሊስ ጣቢያዎች በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች በተለይም ባልተከፈሉ ዕዳዎች ምክንያት ሰዎች ታስረው መገኘታቸው በክትትሉ ከተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በተወሰኑ የፖሊስ ጣቢያዎች ተጠርጣሪዎች የተያዙበት ምክንያት በወቅቱ እንደማይነገራቸው፣ አልፎ አልፎ በተያዙበት ጊዜ እና ፖሊስ ጣቢያ ከገቡ በኋላ በፖሊስ አባላት ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው፣ በመንግሥት የሚቀርበው የምግብ፣ የውሃ እና የሕክምና አገልግሎት ውስን በመሆኑ በተለይ ከቤተሰብ ርቀው የሚታሰሩ ተጠርጣሪዎች ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን መገንዘብ እንደተቻለም ተጠቁሟል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘሪሁን ዱጉማ ኢሰመኮ በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ክትትል አድርጎ ያቀረባቸውን ግኝቶች የሚቀበሏቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በክልሉ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የፈጠራቸው ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል። መሥሪያ ቤታቸው ከኢሰመኮ በየጊዜው የሚቀርቡ ምክረ ሐሳቦችን መነሻ በማድረግ በርካታ የእርምት እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ለሰብአዊ መብቶች መከበር ፖሊስ ያለውን አወንታዊ ሚና አስታውሰው የፖሊስ ሥራ በጥብቅ ሕግ እና ዲሲፕሊን ካልተመራ በሰዎች መብቶች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በኢሰመኮ የተለዩ ክፍተቶችን ለማረም ከዚህ በፊት የጀመራቸውን ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እና አሠራሮችን የማሻሻል ተግባራትን በማስቀጠል የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብቶች በዘላቂነት ለማስከበር ተግባራዊ የለውጥ እርምጃዎችን እንዲወስድ አሳስበዋል፡፡