የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ ከየካቲት 14 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በድርቁ ጉዳት ደርሶባቸው እና ለናሙና የተመረጡ አካባቢዎችን በመዘዋወር የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል በማድረግ ያዘጋጀውንና በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነውን ሪፖርት ሐምሌ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ማውጣቱ ይታወሳል። በሪፖርቱ ላይ ከፌዴራል፣ ከኦሮሚያ እና ከሶማሌ ክልሎች ከተውጣጡ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከተውጣጡ ተሳታፊዎች ጋር ነሐሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ እንዲሁም መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በጅግጅጋ ከተማ የምክክር መድረኮች ተካሂደዋል፡፡ በተደረገው ምክክር በኢሰመኮ የተሰጡ የሪፖርቱ ምክረ ሐሳቦች አተገባበር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት መሆኑ አጽንዖት ተሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ኢሰመኮ በክትትል ሪፖርቱ የተሰጡትን ምክረ ሐሳቦች አተገባበር ለመከታተል ከየካቲት 22 እስከ መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. መረጃዎችን በመሰብሰብ እና ከመስክ ሥራ በኋላም መረጃዎችን በርቀት በመከታተል የአተገባበር ክትትል ሪፖርት አዘጋጅቷል፡፡
በዚህ የአተገባበር ክትትል በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን 40 ቁልፍ መረጃ ሰጭ ግለሰቦች ጋር ቃለመጠይቆችን እና 9 የቡድን ውይይቶችን፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልል 38 ቁልፍ መረጃ ሰጭ ግለሰቦች ጋር ቃለ መጠይቆችን እና 6 የቡድን ውይይቶችን፣ በአጠቃላይ 78 ቃለመጠይቆችን እና 15 የቡድን ውይይቶችን በማድረግ መረጃዎች እና ማስረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ በተሰበሰቡ መረጃዎች የምክረ ሐሳቦችን አተገባበር በመዋቅር፣ በሂደት እና በውጤት አመልካቾች ተተንትነዋል፡፡
በዚህም መሠረት የአተገባበር ክትትል የተደረገባቸው ቦታዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት በድርቅ የሚጠቁ አካባቢዎች ሲሆኑ፣ የድርቁ አደጋ በተለየ መልኩ በመራዘሙ ማለትም ከ3 እስከ 5 የዝናብ ወቅቶች ያልዘነበበት እንዲሁም ሰፊ ቦታዎችን ያካለለ እንደሆነ የክትትሉ ግኝት ያሳያል፡፡ በመሆኑም በማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ላይ የደረሰው ተጽዕኖ ከበፊቱ ጨምሮ ይገኛል፡፡ በሁለቱም ክልሎች በምግብ እጥረት የሚገለጽ በአረጋውያን፣ በነፍሰ ጡር እና በሚያጠቡ እናቶች እና ሕፃናት ላይ የሚታይ ጉዳት ጨምሯል፡፡ ይህም በአፋጣኝ እንዲተገበሩ ተብለው ከተሰጡት ምክረ ሐሳቦች መካከል የምላሹ በቂነት ከተደራሽነት፣ ከተስማሚነት እና ከተመጣጣኝነት አንጻር ሲገመገም ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
በሂደት እንዲተገበሩ ተብለው ከተሰጡት ምክረ ሐሳቦች መካከል የዘላቂ መፍትሔ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በተለይ በቦረና ዞን ያለው የፊና ውሃ ልማት ፕሮጀክት አተገባበር የተሻለና የሚበረታታ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በሁለቱም ክልሎች በአሁኑ ወቅት ዝናብ መገኘቱ በሂደት እንዲተገበሩ በማለት የተሰጡትን የተወሰኑ ምክረ ሐሳቦችን ለመተግበር፣ በተለይም የሕብረተሰቡን መተዳደሪያ ማስፋት እና የዘላቂ መፍትሔ ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት እንዲሠራ የተሻለ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ ይህንኑ አስመልክተው የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት እየተተገበሩ ያሉ ምክረ ሐሳቦችና የተወሰዱ እርምጃዎች አበረታች ቢሆኑም፤ አተገባበሩ በተደራሽነቱ፣ በተስማሚነቱ እና በተዛማጅነቱ እየጨመረ ማኅበረሰቡ መልሶ እስከሚቋቋም ድረስ ሊቀጥል ይገባል፤ በአሁኑ ወቅት ዝናብ መገኘቱም የድርቁ አደጋ ማብቂያ ተደርጎ መወሰድ የለበትም” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።