የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የክልሉ የአስተዳደር እና የጸጥታ አካላት የመከላከያ ሰራዊት አባል ለመሆን የሚፈልጉ ዜጎችን ምልመላ እናከናውናለን በሚል የሰራዊቱን አሠራር እና መስፈርቶች በጣሰ ሁኔታ ሕፃናትን ጨምሮ ሰዎችን በግዳጅ ስለመያዛቸው እና የተያዙትን ለመልቀቅ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ ስለማስገደዳቸው የደረሱትን መረጃዎች ተከትሎ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከኅዳር 4 እስከ 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ክትትል እና ምርመራ አከናውኗል።

ኢሰመኮ በዚህ ክትትል እና ምርመራ በኦሮሚያ ክልል፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በጅማ እና በሻሸመኔ ከተሞች የሚገኙ እጩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ማቆያ ስፍራዎችን በመጎብኘት፤ በማቆያ ስፍራዎቹ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን በማነጋገር፤ እንዲሁም የሚሊሻ እና የፖሊስ ተቋማትን ጨምሮ ከክልል እስከ ቀበሌ መዋቅር ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን በማወያየት ስለጉዳዩ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን አሰባስቧል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 17 ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ነጻነቱን ሊያጣ፣ ሊያዝ እንዲሁም ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር እንደማይችል ይደነግጋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸውና በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሀገሪቱ የሕግ አካል የሆኑት የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን፣ የሕፃናት መብቶች ስምምነት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች ለነጻነት መብት ጥበቃ ያደርጋሉ።

የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ቁጥር 1286/2015 በአንቀጽ 6 (1) የመከላከያ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመዘኛ መሠረት ለወታደርነት ብቁና ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ሊመለምል እንደሚችል ይደነግጋል። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መመሪያ መሠረት በዝቅተኛው መስፈርት በውትድርና ሙያ ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ፣ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 24 ዓመት የሆኑ፣ ስምንተኛ ክፍልን ያጠናቀቁና የትምህርት ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ እና ሌሎች ተጨማሪ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ዜጎች እንዲመዘገቡ ማስታወቂያ አውጥቷል። የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርም የምልመላ ሂደቱን በመከላከያ ሚኒስቴር መስፈርቶች መሠረት እንዲያከናውን የተጠየቀ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። ሆኖም የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር አካላት እና የጸጥታ ኃይሎች አባላት በመከላከያ ሚኒስቴር ከተገለጸው የምልመላ መስፈርት ውጪ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን “የመከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉ” በሚል በግዳጅ እንደያዙ እንዲሁም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በዚህ አግባብ የተያዙ ሰዎችን ለማስለቀቅ ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ማስገደዳቸውን ኢሰመኮ ባከናወነው ምርመራ አረጋግጧል።

ኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራ ባደረገባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ከክልሉ አመራሮች ጋር በመተባበር “የመከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉ” በሚል ተይዘው የነበሩ ሕፃናትን እና የአእምሮ ሕሙማንን ጨምሮ በግዳጅ የተያዙ በርካታ ሰዎችን ለማስለቀቅ ተችሏል። በወቅቱ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም በጅማ እና በሻሸመኔ ከተሞች የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ችግሩ መኖሩን አምነው የማቆያ ስፍራዎችን በመፈተሽ የእርምት እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆናቸውን እና ድርጊቱን በፈጸሙ የመንግሥት ኃላፊዎች እና የሚሊሻ አባላት ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ለኢሰመኮ ገልጸዋል። ኢሰመኮ ክትትል ባደረገባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችም ከመስፈርት ውጪ የተደረገ ምልመላ መሆኑን በመግለጽ በክልሉ የጸጥታ አካላት የተያዙ ሰዎች ከማቆያ ስፍራዎች እንዲለቀቁ ያደረጉ መሆኑን ተገንዝቧል።

ይህ የምርመራ ሪፖርት በመጠናቀር ላይ በነበረበት ወቅት በተለይም ኅዳር 14 እና 15 ቀን 2017 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሲከናወን የቆየው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራ መጠናቀቁን እና ሰራዊቱ በፈቃደኛነት የተመዘገቡ እና የምልመላ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ምልምሎችን ለይቶ ወደ ማሰልጠኛ ተቋማት እንዲገቡ ማድረጉን ኢሰመኮ ተገንዝቧል።

የተያዙ ሕፃናትን በተመለከተ

ኢሰመኮ በሻሸመኔ ከተማ ባደረገው ክትትል እና ምርመራ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች መሆኑን የገለጹ ሕፃናት “ወታደራዊ ስልጠና ትገባላችሁ” በሚል ወደ ማቆያ አዳራሾች እንዲገቡ መደረጋቸውን አረጋግጧል። በሁሩፋ ክፍለ ከተማ፣ ሀሌሉ ወረዳ ውስጥ በማቆያ አዳራሽ ከነበሩ እና ኢሰመኮ ካነጋገራቸው 32 ሰዎች መካከል 14ቱ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 16 ዓመት መሆኑን የገለጹ ሲሆን አንድ ሕፃን ደግሞ ዕድሜው 11 ዓመት መሆኑን ገልጿል። ከትምህርት ቤት ሲወጡ ከነዩኒፎርማቸው ሀሌሉ ወረዳ ወደ ሚገኘው ማቆያ አዳራሽ እንዲገቡ የተደረጉ የ5ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ ሁለት የ15 ዓመት ሕፃናት ወደ አዳራሽ ከገቡ ሁለት ሳምንት እንደሆናቸው ገልጸው የገቡበትን ሁኔታ ሲያስረዱ፦

“ከትምህርት ቤት ስንመለስ መከላከያ ለሚገቡ 25,000 ብር ይሰጣል ብሎ አንድ ግለሰብ በባጃጅ አሳፈረን፤ ከዚያ 010 ቀበሌ (ሀሌሉ ወረዳ) ወደ ሚገኘው አዳራሽ ገባን፤ ነገር ግን ከገባን በኋላ መውጣት አልቻልንም” ሲሉ ለኢሰመኮ ገልጸዋል፡፡

በጅማ ከተማ ኢሰመኮ ያነጋገረው የ14 ዓመት ሕፃን ስለተያዘበት ሁኔታ ሲያስረዳ፦

“ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡30 ሰዓት አካባቢ ወደ ቤት እየሄድኩ እያለሁ መንገድ ላይ ቆመው የነበሩ ሚሊሻዎች ባትሪ አብርተውብኝ አስቆሙኝ፤ መታወቂያ ሲጠይቁኝ ዕድሜዬ ገና 14 ዓመት ነው፤ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ መታወቂያ የለኝም ብዬ ስመልስ፣ ቀበሌ ሄደህ ጉዳይህ ይጣራል በማለት ወደ ቀበሌ ወስደው ብዛታቸው ከ20 በላይ ከሚሆኑ ወጣቶች መካከል ቀላቅለውኝ ሄዱ። ለመከላከያ ሰራዊት አባልነት መያዜንም ወጣቶቹ ናቸው የነገሩኝ። በማግስቱ በድብቅ ለቤተሰቦቼ ደውዬ ካሳወቅኩ በኋላ ለመውጣት ችያለሁ” ብሏል።

በግዳጅ የተያዙ ሰዎች

በሻሸመኔ ከተማ ሁሩፋ ክፍለ ከተማ ሀሌሉ ወረዳ (010 ቀበሌ) ማቆያ አዳራሽ ውስጥ ከነበሩ እና ኢሰመኮ ካነጋገራቸው 32 ሰዎች መካከል፣ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ 13 ሰዎች ያለ ፈቃዳቸው በፖሊስ እና በሚሊሻ አባላት ተይዘው እንደገቡ፤ በአዳራሹ ከሳምንት በላይ እንደቆዩ እና መውጣት እንዳልቻሉ ገልጸዋል። በማቆያው ውስጥ የነበረ 1 ሰው ስለተያዘበት ሁኔታ ለኢሰመኮ ሲያስረዳ፣ በምሽት ወደ ቤቱ እየሄደ ሳለ ሚሊሻዎች ይዘውት ወደ አዳራሽ እንዳስገቡት እና ከተያዘ 4 ቀናት እንደሆነው አስረድቷል። ሌላ ለኢሰመኮ ምስክርነቱን የሰጠ ሰው ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ለልጁ እራት ለመግዛት ከቤት ሲወጣ ያለምንም ምክንያት በሚሊሻ ተይዞ ወደ አዳራሹ እንደገባ ገልጿል።

በዚሁ በሀሌሉ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው አዳራሽ ተይዘው ከነበሩ እና ኢሰመኮ ካነጋገራቸው ሰዎች መካከል ዕድሜው 45 ዓመት እንደሆነ እና 4 ልጆችን ያለ እናት እንደሚያሳድግ የገለጸ አንድ ግለሰብ፣ ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ ከቤቱ ሲወጣ እንደተያዘ ገልጿል።

በተመሳሳይ በሁሩፋ ክፍለ ከተማ ቡልቻና ወረዳ ውስጥ በሚገኝ አዳራሽ ተይዘው ከነበሩ እና ኢሰመኮ ካነጋገራቸው 22 ሰዎች መካከል 4 ሰዎች፣ እንዲሁም በአለቼ ክፍለ ከተማ በአዋሻ ወረዳ ኢሰመኮ ካነጋገራቸው 10 ሰዎች መካከል 2 ሰዎች ከምሽቱ 2፡00 እስከ 3፡00 ሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ከሥራ ሲመለሱ በሚሊሻ እና በፖሊስ አባላት ተይዘው ያለፈቃዳቸው ወደ ማቆያ አዳራሽ እንደገቡ ገልጸዋል፡፡ ኢሰመኮ በጎበኛቸው የማቆያ አዳራሾች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በተመሳሳይ መንገድ በተለይ በምሽት በርካታ ሰዎች ከፈቃዳቸው ውጪ በሚሊሻ እና በፖሊስ ተይዘው ወደ ማቆያ አዳራሾቹ እንደገቡ ገልጸዋል። በተጨማሪም ኢሰመኮ በቡልቻና ወረዳ አንድ የአእምሮ ሕመም ያለበት ሰው በሚሊሻ አባላት በግዳጅ ወደ ማቆያ አዳራሹ እንዲገባ መደረጉን ከቤተሰቡ እና ከግለሰቡ ጋር ከነበረው ውይይት ለመገንዘብ ችሏል።

ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ዱከም ክፍለ ከተማ ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን አካባቢ ለዕለት ሥራ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት ወጣቶች “ለመከላከያ ሰራዊት አባልነት ትመለመላላችሁ” በሚል ከሌሎች 15 ከሚሆኑ ወጣቶች ጋር በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት እንደተያዙ እና ለሁለት ቀናት ከታሰሩ በኋላ በቤታሰቦቻቸው እና በዘመዶቻቸው ጥረት በተደረገው ድርድር መለቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡

የተያዙ ሰዎችን ለመልቀቅ ገንዘብ እንዲከፍሉ ስለማስገደድ

አንዳንድ የክልሉ ሚሊሻ አባላት ወጣቶችን ለመከላከያ ሰራዊት አባልነት ምልመላ በሚል ከያዙ በኋላ ለመልቀቅ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገደዱ መሆኑን ኢሰመኮ አረጋግጧል። ይህ ገንዘብ እንዲከፈል የማስገደድ ድርጊት በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ሪፖርት የተደረገ ሲሆን በተለይም በአዳማ ከተማ እና አካባቢው ተስፋፍቶ ሲፈጸም የነበረ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

በአዳማ ከተማ በአንጋቱ ወረዳ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ ዳቦ ለመግዛት ከቤት የወጣ የ15 ዓመት ሕፃን እና የ8ኛ ክፍል ተማሪ በወረዳው ሚሊሻዎች ተይዞ ጨፌ ቀበሌ ፊት ለፊት በሚገኝ የእህል መጋዘን ውስጥ ተይዞ እንደነበር የገለጸች ኢሰመኮ ያነጋገራት እናት ምግብና ልብስ መውሰድ እንደማይፈቀድና በሚሊሻ እንደሚቀርብለት እንደነገሯት፤ በመጋዘኑ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ወጣቶች በተመሳሳይ ሁኔታ ተይዘው እንደነበሩ እና የአብዛኞቹ ቤተሰቦች ከ20,000 እስከ 100,000 ብር መጠየቃቸውን መስማቷን ገልጻለች። በዚሁ ጨፌ ቀበሌ ፊት ለፊት በሚገኘው መጋዘን ተይዞ የነበረ ሌላ የ15 ዓመት ሕፃን ወላጆች 20,000 ብር ካልከፈሉ ልጃቸው “ለወታደራዊ ስልጠና” እንደሚላክ የተነገራቸው መሆኑን ለኢሰመኮ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ 1 መረጃ ሰጪ ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት 12፡00 ሰዓት አካባቢ “ውትድርና ስልጠና ይሄዳል” በሚል 6 በሚሆኑ የሚሊሻ አባላት የተያዘ የ25 ዓመት ወንድሙን ለማስለቀቅ 30,000 ብር እንዲከፍል መጠየቁን እና ኢሰመኮ ባነጋገረው ወቅት ገንዘቡን በማፈላለግ ላይ እንደነበር አስረድቷል። ወንድሙ በተያዘበት ስፍራ ሌሎች በርካታ ሰዎች ተይዘው እንደነበረ እና ዐቅማቸው የሚፈቅድ የተያዙ ሰዎች ቤተሰቦች ከ20,000 እስከ 30,000 ብር እየከፈሉ ያስለቀቁ መሆኑን ገልጿል።

ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት አካባቢ በአዳማ ከተማ ደካ አዲ ወረዳ ነዋሪ የሆነ አንድ የ21 ዓመት ወጣት ከሥራ ወደ መኖሪያ ቤት በመመለስ ላይ እያለ ተይዞ በወረዳው አስተዳደር አዳራሽ ለ4 ቀናት እንዲቆይ ተደርጓል። የወረዳው ሚሊሻ አባላት ወላጅ እናቱን 25,000 ብር ካልከፈለች “ለውትድርና ስልጠና” ወደ ሌላ ቦታ እንደሚልኩት በማስፈራራት ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላ ወጣቱን መልቀቃቸው ተገልጿል። 

ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ በአዳማ ከተማ ጨፌ ቀበሌ 1 በቀን ሥራ የሚተዳደር የ16 ዓመት ሕፃን በቀበሌው ሚሊሻ አባላት በቁጥጥር ሥር ውሎ ቤተሰቦቹ 30,000 ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን እና ዐቅም የሌላቸው መሆኑን ከገለጹ በኋላ ወደ ቀበሌው አስተዳደር እንዳይመለሱ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው፤ ሕፃኑም መረጃው ለኢሰመኮ እስከደረሰበት ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ተይዞ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።

የመንግሥት አካላት ምላሽ

ኢሰመኮ በክትትል እና ምርመራው የደረሰባቸውን ግኝቶች አስመልክቶ በወቅቱ ያነጋገራቸው የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ችግሩ መኖሩን የሚያውቁ መሆኑን ገልጸው የመከላከያ ሰራዊት ካስቀመጠው መስፈርት ውጪ የተከናወኑ ምልመላዎች በአፋጣኝ እንዲታረሙ መመሪያ መሰጠቱን፤ በክልል አመራር ደረጃ ወደታችኛው አስተዳደር እርከን መዋቅር በመውረድ የምልምል ማቆያ ስፍራዎችን በመጎብኘት ያለፈቃዳቸው ወይም የመከላከያ ሰራዊት መስፈርቶችን በማያሟላ መንገድ እንዲመለመሉ በሚል የተያዙ ሰዎች እንዲለቀቁ በማድረግ ላይ የሚገኙ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም በመደለያም ሆነ በግዳጅ ሕፃናትን ጨምሮ ከመስፈርቱ ውጪ የሆኑ ሰዎችን የመለመሉ የጸጥታ አባላት ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

ሻሸመኔ እና ጅማ ከተሞች የሚገኙ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው አመራሮችም በተመሳሳይ በወቅቱ ከመደበኛ የምልመላ ሥርዓት ውጪ ሰዎች በግዳጅ እየተያዙ ስለመሆኑ መረጃ እንዳላቸው እና ያለፈቃዳቸው ወደ ማቆያ ስፍራዎቹ የገቡትን እያጣሩ በመልቀቅ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው ነበር። በተጨማሪም የኢሰመኮ የክትትል እና ምርመራ ግኝቶችን ተከትሎ በጅማ እና በሻሸመኔ ከተሞች ከሚገኙ የመንግሥት አመራሮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ከሕግ እና ከሰራዊቱ መስፈርቶች ውጪ የተያዙ 8 ሕፃናት እና 1 የአእምሮ ሕመምተኛን ጨምሮ ከ36 በላይ ሰዎች እንዲለቀቁ ለማድረግ ተችሏል።

በወቅቱ ኢሰመኮ ያነጋገራቸው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችም መረጃውን መሠረት በማድረግ ከመስፈርት ውጪ የተመለመሉ ሰዎች ከማቆያ ስፍራዎች እንዲወጡ በማድረግ ላይ መሆናቸውን እና በምልምል ወታደርነት ወደ ሰራዊቱ ማሰልጠኛ ስፍራዎች ለመረከብ ፈቃደኛ ያለመሆናቸውን ገልጸዋል። ለምሳሌ በሻሸመኔ ከተማና አካባቢው የመከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል በፈቃዳቸው ከተመዘገቡ እንዲሁም በግዳጅ ከተያዙ 1172 ሰዎች መካከል የመከላከያ ሚኒስቴር ፈቃደኛ የሆኑና የምልመላ መስፈርቶችን የሚያሟሉ 602 ሰዎችን ብቻ በምልምል ወታደርነት የተቀበለ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

ኢሰመኮ ለመከላከያ ሚኒስቴር እና ለኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በጻፋቸው ደብዳቤዎች የተመለመሉ ሰዎች ወደ ሰራዊቱ ማሰልጠኛ ተቋማት ከመላካቸው በፊት ሕፃናትን ጨምሮ ከሰራዊቱ የምልመላ መስፈርቶች ውጪ በግዳጅ እና በመደለያ የተያዙ ሰዎች እንዲለቀቁ የማድረግ ሥራ በሁሉም ምልመላ በተደረገባቸው የክልሉ አካባቢዎች በተደራጀ ሁኔታ ስለመከናወኑ እንዲሁም ሰዎችን በግዳጅ የያዙ እና የተያዙ ሰዎች ቤተሰቦችን ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገደዱ በክልሉ በተለይም በከተማ፣ ወረዳ እና ቀበሌ ደረጃ የሚገኙ የአስተዳደር እና የጸጥታ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ላይ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የተከናወኑ ወይም በመከናወን ላይ የሚገኙ ተግባራት ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠይቅም ይህ ሪፖርት ይፋ እስከተደረገበት ድረስ ተቋማቱ ምላሽ አልሰጡም።

መደምደሚያ

ኢሰመኮ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን ባሰባሰበባቸው የተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች “የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ” በሚል ሕፃናትን ጨምሮ በግዳጅ የተያዙ ሰዎችን የመከላከያ ሰራዊት በምልምል ወታደርነት ያለመቀበሉን ለማወቅ ተችሏል። ስለሆነም በሂደቱ ከሕግ አግባብ ውጪ ተይዘው የሚገኙ ሰዎች ጉዳይ በዋናነት በግዳጅ ምልመላ (conscription) ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 17 መሠረት በነጻነት መብት ማዕቀፍ እንዲሁም የሕገወጥ እና የዘፈቀደ እስራት ክልከላን በሚመለከቱ ድንጋጌዎች መሠረት የሚታይ ነው።

ኢሰመኮ ካነጋገራቸው ተጎጂዎች እና ምስክሮች፣ በአካል ምልከታ ካደረገባቸው የማቆያ ስፍራዎች እና ከክልሉ የጸጥታ እና አስተዳደር አካላት ባሰባሰባቸው ማስረጃዎች በኦሮሚያ ክልል የተከናወነው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ በተለይም በወረዳ፣ ከተማ እና በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ የክልሉ መንግሥት ኃላፊዎች እና የጸጥታ አካላት የተቀመጠላቸውን የምልመላ ኮታ ለማሟላት አንዳንዶች ደግሞ በሂደቱ ያልተገባ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት በተስፋፋ ሁኔታ ሕፃናትንና ሌሎች ሰዎችን በመደለያ እና በግዳጅ መያዛቸውን እንዲሁም አልፎ አልፎ የተያዙ ሰዎችን ለማስለቀቅ ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገደዱ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። 

እነዚህ ተግባራት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች እና በሕገ መንግሥቱ ጥበቃ የተደረገለትን የነጻነት መብት የሚጥሱ የሕገወጥ እና የዘፈቀደ እስራት ናቸው።

ምክረ ሐሳብ፦

ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

  • ከመከላከያ ሰራዊት መስፈርቶች ውጪ ለምልመላ በሚል ሰዎችን በግዳጅ በመያዝ ላይ የተሳተፉ እንዲሁም የተያዙ ሰዎችን ለመልቀቅ የገንዘብ ክፍያ የጠየቁ፣ የተቀበሉ እና ይህንኑ የመከላከልና የመቆጣጠር ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የጸጥታ እና የአስተዳደር አካላት ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተከናውኖ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፤
  • በቀጣይ በክልሉ የሚከናወኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች በሰራዊቱ መስፈርቶች እና አሠራር ሥርዓቶች መሠረት ብቻ ሕግን በተከተለ እና ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ አግባብ መከናወናቸውን እንዲያረጋግጥ፤

ለኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሚኒስቴር

  • በኦሮሚያ ክልል እና በሌሎች ክልሎች የሚካሄዱ የሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች በሰራዊቱ መስፈርቶች እና አሠራር ሥርዓቶች መሠረት ብቻ መከናወናቸውን ለማረጋገጥ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ፤
  • በኦሮሚያ ክልል ከሰራዊቱ መስፈርቶች ውጪ በግዳጅ ሰዎችን ለመመልመል በተንቀሳቀሱ የክልሉ አስተዳደር እና የጸጥታ መዋቅር ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ላይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ከክልሉ ጋር በጋራ እንዲሠራ ኢሰመኮ ያሳስባል።

የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ “በዚህ ሂደት ሕፃናትን እና ሌሎች ሰዎችን በግዳጅ ለመመልመል በሚል የያዙ፣ ከእስር ለመልቀቅ ገንዘብ የጠየቁ እና የተቀበሉ የጸጥታ እና የአስተዳደር አካላት በአፋጣኝ ተጠያቂ ሊደረጉ ይገባል” ብለዋል። አክለውም “በቀጣይ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ክልሎች የሚካሔዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች ሰራዊቱ ባስቀመጠው አሠራር እና መስፈርት መሠረት በፈቃደኛነት ላይ ብቻ ተመሥርተው መከናወናቸውን ሊያረጋገጥ ይገባል” ብለዋል።