ሰብአዊ መብቶች ተኮር የበጀት አመዳደብ (Human Rights–Based Budgeting) ምን ማለት ነው?
መንግሥት በሕጎች፣ ፖሊሲዎች፣ ዕቅዶች እና ፕሮግራሞች የተቀረጹ ሊያሳካ የሚፈልጋቸውን ዓላማዎች ከሚያስፈጽምበት አንዱ እና ዋነኛው መንገድ በጀት ነው።
በበጀት አመዳደብ ሂደት ሰብአዊ መብቶች ተኮር መሆን ማለት ሀብትን የሰው ልጆችን ባስቀደመ መልኩ ወይም ሰዎችን ማዕከል በሚያደርግ መንገድ መመደብ ነው። ይህ ዐይነቱ የበጀት አመዳደብ ሂደት ገንዘብ የሚመነጭበት፣ የሚከፋፈልበት እና ሥራ ላይ የሚውልበት ሂደት በሰዎች የሰብአዊ መብቶች ላይ የሚኖረውን አንድምታ ከግምት ውስጥ ማስገባትን ይጠይቃል።
በተለይም የበጀት ውሳኔዎች የሰብአዊ መብቶች መርሖችን ሊያንጸባርቁ፣ እንዲሁም በጀት የማዘጋጀት፣ የማጽደቅ፣ የመፈጸም እና በጀቱን ኦዲት የማድረግ ሂደቱ በሰብአዊ መብቶች መርሖች ሊመራ ያስፈልጋል። የበጀት አወሳሰን ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ መሆኑን ማረጋገጥ የመብት ተኮር በጀት አመዳደብ ወሳኝ ገጽታ ነው። ስለሆነም መብት ተኮር የበጀት አመዳደብ የዚህ ሁሉ ሂደት አካል ሊሆን ይገባል። በተለይም የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ፖሊሲ በመቅረጽ እና ዕቅድ በማውጣት የሚሠሩ አካላት ከበጀት አመዳደብ ጋር ግንኙነት ካላቸው አካላት ጋር በቅርበት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
መንግሥታት ገንዘብ የሚያመነጩበት፣ የሚያከፋፍሉበት እና ሥራ ላይ የሚያውሉበት ሂደት የመንግሥት ሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ኃላፊነት ላይ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ስለሆነም፡-
- የበጀት አመዳደብ ሂደት መንግሥት ለመብቶች ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይበት አንዱ መንገድ በመሆኑ የሰብአዊ መብቶች መርሖች በበጀት አመዳደብ ሂደቱ ላይ ሊንጸባረቁ ይገባል፣
- መብት ተኮር የበጀት አመዳደብ፣ በጀት በሚመደብበት ጊዜ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት የሚያስገነዝብ ሲሆን፣ ሰብአዊ መብቶች ተኮር የበጀት አመዳደብ ሰፊ የሆነ የፖሊሲ ሂደት ነው።
መብት ተኮር የበጀት አመዳደብን ለመከተል የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ግዴታዎችን መለየት፣ በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ቡድኖች የሚገጥሟቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምን እንደሆኑ መተንተን፣ ለምሳሌ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የትምህርት፣ የጤና እና የመጠለያ ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ መገንዘብ፣ እነዚህን የተለዩ የመብት ጥሰቶች ለማረም የሚበጅ ፖሊሲ መቅረጽ፣ የተቀረጸው ፖሊሲ ሥራ ላይ እንዲውል የሚያስችል በቂ በጀት መመደብ፣ የተመደበው በጀት ለታሰበለት ዓላማ መዋሉን መቆጣጠር፣ እንዲሁም ፖሊሲው መፈጸሙን እና ያመጣውን ውጤት (impact) መገምገም አስፈላጊ ነው።
ሰብአዊ መብቶች ተኮር በጀት አመዳደብን በተመለከተ ያሉ የሕግ ድንጋጌዎች ምንድን ናቸው?
በፌዴራል ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 9(4) መሠረት ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የሀገሪቱ የሕግ አካል ናቸው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ በምዕራፍ 3 ስር የተካተቱትን የሰብአዊ መብቶችን የማሟላት፣ የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነት በየደረጃው ባሉ የፌዴራል እና የክልል የመንግሥት አካላት ላይ ይጥላል። ግለሰቦች እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትም ሰብአዊ መብቶችን የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው።
በተጨማሪም በሕገ-መንግሥቱ የተዘረዘሩ የሰብአዊ መብቶች ከዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች አንጻር መተርጎም እንዳለባቸው ሕገ መንግሥቱ በግልጽ በመደንገግ የሰብአዊ መብቶችን ሕገ መንግሥታዊና ዓለም አቀፋዊ የሕግ መሠረት ከፍ አድርጎታል። ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች፣ ስምምነቱን በተቀበሉ አባል ሀገራት ላይ ሁሉ የተለያዩ ኃላፊነቶችን እና ግዴታዎችን ይጥላሉ። ከእነዚህ ግዴታዎች ውስጥ አንዱ በእነዚህ ስምምነቶች ውስጥ የተዘረዘሩ የሰብአዊ መብቶችን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ተገቢውን ሀብት ወይም በጀት በመመደብ መብቶቹ እንዲሟሉ፣ እንዲጠበቁና ተፈጻሚ እንዲሆኑ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው።
ከበጀት አመዳደብ ጋር በተገናኘ ሀብት (resource) የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ጨምሮ ሁሉንም መብቶች ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ያለው ነው፡፡ ዓለም አቀፉን የሕጻናት መብቶች ስምምነትን አፈጻጸም የሚከታተለው ኮሚቴ ሀብት የሚለው ፅንሰ-ሐሳብ ሰፊ እንደሆነና የሰው ሀብትን (human resource)፣ የቴክኒክ ሀብትን (technical resource)፣ ተቋማዊ ሀብትን (organizational resource)፣ የተፈጥሮ ሀብትን (natural resource) እና የመረጃ ሀብትን (information resources) እንደሚያካትት ያስረዳል።
የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን በአንቀጽ 2(1) ስር ማንኛውም የቃልኪዳኑ አባል ሀገር በግሉ እና በተለይ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ በታከለበት ዓለም አቀፍ እርዳታ እና ትብብር አማካኝነት በእጁ የሚገኙትን ሀብቶች አሟጦ በመጠቀም በቃልኪዳኑ ዕውቅና ያገኙት መብቶች በሂደት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ሕግ ማውጣትን ጨምሮ ማናቸውንም ተገቢ እርምጃዎች መውሰድ እንዳለበት ይደነግጋል። በዚህም መሠረት ሀብት ማለት በሀገር ውስጥ የሚገኘውን ብቻ ሳይሆን ከላይ እንደተጠቀሰው ከዓለም አቀፍ ትብብር እና እርዳታ የሚገኘውንም ሀብት ጭምር ያካትታል። በተጨማሪም የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶችን በተመለከተ የሚያብራራው መመሪያ (Maastricht Guidelines) አንድ ሀገር ለሰብአዊ መብቶች መከበር እንዲረዳ ያለውን ሀብት አሟጦ መመደብ ካልቻለ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን ሊያስከትል እንደሚችል ይገልጻል።
ስለሆነም ከመንግሥት የሰብአዊ መብቶች ግዴታዎች ጋር የሚጣጣም በጀት ለመመደብ በእጅ ላይ ያለውን ሀብት ውጤታማ እና ከአድሎ በጸዳ መልኩ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ሀብትን ለማመንጨት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ተኮር የበጀት አመዳደብ የሰብአዊ መብቶችን ለማረጋገጥ እንዲያስችል መንግሥታት የሚችሉትን ዐቅም ሁሉ ተጠቅመው በሀገር ውስጥ ሀብትን ማመንጨት (mobilize resources) እና ከውጭ የሚገኝ ሀብትንም ማሰባሰብ ይኖርባቸዋል።
የመንግሥት ሀብትን የማመንጨት እና የተገኘውን ሀብት ሥራ ላይ የማዋል ሂደት ውጤታማ (efficient) መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም ሙስናን አለመከላከል ሀብትን በአግባቡ የሰብአዊ መብቶችን ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ ሥራ ላይ የማዋል ከሰብአዊ መብት ስምምነቶች የሚመነጭ ግዴታን የሚጥስ ነው። በዚህ ረገድ አባል ሀገራት ሙስናን ለመከላከል በሕዝብ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን ሊያሰፍኑ እንደሚገባ ሙስናን ለመከላከል እና ለመዋጋት የተደረገ የአፍሪካ ሕብረት ስምምነት ይገልጻል።
በተጨማሪም መንግሥታት መብቶችን ወደኋላ ሊወስድ የሚችል እርምጃዎችን (retrogressive measures) ከመውሰድ መቆጠብ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ከዚህ ቀደም ይመደብ የነበረው በጀት ላይ ቅናሽ የማድረግ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት በእጃቸው ላይ ያለውን ሀብት አሟጠው መጠቀማቸውን ማስረዳት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ያለው ሀብት የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ለማረጋገጥ በቂ ካልሆነ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትብብር እና ድጋፍ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
መብቶች ተኮር የበጀት አመዳደብ ሊከተላቸው የሚገቡ መርሖች ምንድን ናቸው?
ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ የበጀት አመዳደብ ሲባል በአጠቃላይ የበጀት ሂደቱ በሰብአዊ መብቶች መርሖች ሊመራ ይገባል ማለት ነው። ይህም የበጀት አመዳደብ ሂደቱ አሳታፊ እና የመረጃ ተደራሽነትን ከግምት ያስገባ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ ውጤታማ መፍትሔ ሊሰጡ የሚችሉ አካላት ያሉት፣ ከአድሎ የጸዳ፣ ሰዎችን በማብቃት ላይ የተመሠረተ እና ሕጋዊ ሊሆን ይገባል።
የአሳታፊነት መርሕ (Principle of Participation)
ይህ መርሕ ሁሉም ሰዎች በበጀት ሂደቱ ውስጥ ንቁ እና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያብራራ መርሕ ነው። ሁሉም ሰው የሰብአዊ መብቶቹን ሊነካ በሚችል ማንኛውም የውሳኔ ሂደት ተሳታፊ ሊሆን ይገባዋል። ግለሰቦች የነቃ፣ ትርጉም ያለው እና ነጻ ተሳትፎ ማድረግ እንዲችሉ ተደራሽ የሆነ የመረጃ እና የተግባቦት ሥርዓት መፍጠር አስፈላጊ ነው። ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጨምሮ በበጀት ሂደቱ እንዲሳተፉ ማድረግን ያካትታል።
የተጠያቂነት እና ግልጽነት መርሕ (Principle of Accountability and Transparency)
ይህ መርሕ የበጀት አመዳደብ ሂደት ላይ ተሳታፊ የሆኑ የመንግሥት አካላት በጀቱን በተመለከተ ተጠያቂነት እንዳለባቸው የሚገልጽ ነው። ምክንያቱም ሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ የተጣለበት አካል ስለሆነ እና ግዴታን አለመወጣት ደግሞ ተጠያቂ ስለሚያደርግ ነው። ስለሆነም በጀቱን የተመለከተ በቂ መረጃ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ እና ግልጽነት የተሞላበት የበጀት አመዳደብ ሥርዓት ሊኖር ይገባል። ይህ ሳይሆን ሲቀር የሚመለከታቸው አካላት ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ተገቢነት ላለው የሕግ አካል ጉዳያቸውን በማቅረብ ተገቢውን ሕጋዊ መፍትሔ የማግኘት መብት አላቸው። ተጠያቂነትን ለማስፈን የተለያዩ እርምጃዎች መወሰድ ያለባቸው ሲሆን፣ ለምሳሌ ግልጽነት የተሞላበት የበጀት ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ እና የበጀት ትንተና ዐቅምን ማሳደግ ነው። የሰብአዊ መብቶችን ተግባራዊነት ለመከታተል የሚረዱ መረጃዎች ተደራሽ እንዲሆኑ መወትወት፣ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እንዲኖር ማበረታታት እና ባለመብቶች መብቶቻቸውን መጠየቅ እንዲችሉ ዐቅም መገንባትን ይጨምራል፡፡
እኩልነት እና ከአድሎአዊ ልዩነት የመጠበቅ መርሕ(Equality and Non-Discrimination)
ይህ መርሕ ሁሉም ሰዎች ያለምንም ልዩነት እና አድሎአዊነት ሁሉም የሰብአዊ መብቶች ለሁሉም በእኩልነት ተፈጻሚ መሆን እንዳለባቸው ይገልጻል። በተጨማሪም በበጀት አመዳደብ ሂደት፣ ለተገለሉና ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን ከሌሎች እኩል መጠቀም እንዲችሉ ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ያስገነዝባል።
የማብቃት መርሕ (Empowerment)
ማብቃት ወይም የሰዎችን ዐቅም ማጎልበት ሌላው መርሕ ነው። ማንኛውም ሰው በዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ሕጎች ዕውቅና የተሰጣቸውን የሰብአዊ መብቶች እና ነጻነቶች እንዲከበሩለት የመጠየቅ እና መብቶቹንም የመጠቀም መብት አለው። ስለሆነም ግለሰቦች እና ማኅበረሰቡ መብቶቻቸውን ማወቅ እንዲሁም መብቶቻቸው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ፖሊሲዎች እና የበጀት አመዳደብ ሂደት ላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም፣ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች መብቶቻቸውን እንዲገነዘቡ እና በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንዲችሉ አስፈላጊውን ዐቅም መፍጠር ወይም ማብቃት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
የሕጋዊነት መርሕ (Legality)
ይህ መርሕ የበጀት አመዳደብ ሂደት ሕጋዊነት መከተል እንዳለበት ያሳስባል። በዚህም የበጀት አመዳደብ ሂደቱ በሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሕጎች ዕውቅና የተሰጣቸውን መሠረታዊ መብቶች እና ነጻነቶችን መሠረት ያደረገ፣ አግባብነት ያላቸውን የአገሪቱን ሕጎች ያከበረ፣ እንዲሁም ከሰብአዊ መብቶች መርሖች ጋር የተጣጣመ የበጀት አመዳደብ ሊኖር ይገባል።