የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች ያለው ተደራሽነት ላይ ያተኮረ ባለ 30 ገጽ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። በሪፖርቱ የተስተዋሉ መልካም ጅማሮዎች፣ አሳሳቢ ጉዳዮች፣ የአካል ጉዳተኛ መንገደኞች ተሞክሮ፣ ዝርዝር ምክረ ሐሳቦች እና ክትትሉ ከተከናወነ በኋላ የተስተዋሉ ለውጦች እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጠውን ምክረ ሐሳብ ለመተግበር የሰጠው የጽሑፍ ምላሽ ተካተዋል።
ኢሰመኮ በተለያዩ ጊዜያት ከአካል ጉዳተኛ መንገደኞች የደረሱትን መረጃዎች መነሻ በማድረግ ክትትሉን ከከባቢያዊ፣ ከተቋማዊ፣ ከመረጃና ተግባቦት እንዲሁም ከአመለካከት ተደራሽነት አንጻር በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ በባሕር ዳር፣ በጅማ እንዲሁም በሃዋሳ አየር ማረፊያዎች በጥር እና በየካቲት ወራት 2016 ዓ.ም. አካሄዷል። በዚህም 1 ሴት አካል ጉዳተኛ እና 3 ወንድ ባለሙያዎችን ያካተተ ቡድን በማሠማራት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ ከሲቪል አቪዬሽን ሠራተኞች እንዲሁም የአየር መንገዱ ደንበኛ ከሆኑ አካል ጉዳተኞች ጋር በተደረገ ቃለ መጠይቅ፣ የአካል ምልከታ እና ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሠነዶች በማመሳከር መረጃና ማስረጃዎች ተሰብስቧል። በክትትሉ በአጠቃላይ ከ26 ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቅ የተደረገ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 10 አካል ጉዳተኞች በቃለ መጠይቁ ተሳትፈዋል።
ኢሰመኮ መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተወካዮች ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት ግኝቶቹን እና ያቀረባቸውን ምክረ ሐሳቦች በማጋራት ተጨማሪ ግብአቶችን አሰባስቧል። በተጨማሪም ለአየር መንገዱ የሪፖርቱን ዋና ዋና ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች በጽሑፍ በመላክ እንዲሁም ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ከአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት በማካሄድ የውትወታ ሥራ አከናውኗል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢሰመኮ የተሰጡትን ምክረ ሐሳቦች መሠረት በማድረግ ተደራሽነቱን ለማስፋት ተጨባጭ ሥራዎችን ማከናወን የጀመረ ሲሆን ለአብነትም በበይነ መረብ ትኬት የሚቆረጥበትን እና ለዐይነ ስውራን ተደራሽ ያልነበረውን የሞባይል መተግበሪያ (application) ምቹ እና ተደራሽ ማድረጉ እንዲሁም የጅማ አባ ጅፋር አየር ማረፊያን ከባቢያዊ ተደራሽነት ለማሳለጥ የዲዛይን ሥራ ተጠናቆ ግንባታ መጀመሩ ከተስተዋሉ መልካም ለውጦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። አየር መንገዱ በተጨባጭ ማከናወን ከጀመረው የማሻሻያ ተግባር በተጨማሪ በክትትል ሪፖርቱ የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ተፈጻሚ ለማድረግ የጊዜ ሰሌዳ ያካተተ ዝርዝር ዕቅድ መላኩ የሚበረታታ እርምጃ ነው።
ክፍተቶቹን ለመቅረፍ የተወሰዱ እና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች እንዳሉ ሆነው ሪፖርቱ በክትትሉ የአየር ትራንስፖርትን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እና ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የታዩ ክፍተቶችንም በዝርዝር አካቷል። በዚህም መሠረት ክትትሉ በተከናወነባቸው አየር ማረፊያዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ለመጓጓዝ ረዳት እና ተሽከርካሪ ወንበሮች በበቂ ሁኔታ እንደማይቀርብ እና ብሬስ (የአካል ድጋፍ) እና ዊልቼር (ተሽከርካሪ ወንበር) ለሚጠቀሙ አካል ጉዳተኛ መንገደኞች የተዘጋጁ ምቹ የግል መፈተሻ ክፍሎች (private rooms) በተለይ በክልል በሚገኙ አየር ማረፊያዎች አለመኖሩ ተመላክቷል። በክልል በሚገኙ አየር ማረፊያ ተርሚናሎች ወደ አውሮፕላን ለመግባትም ሆነ ከአውሮፕላን ወጥቶ ለመሄድ የመጓጓዣ አገልግሎት የማይሰጥ በመሆኑ በተለይ በዝናብ ወቅት እና በረሃማ በሆኑ አካባቢዎች አካል ጉዳተኞች ለተጨማሪ እንግልት መዳረጋቸው፤ የአውሮፕላን በሮች ላይ የሚገጠም ተሻጋሪ ድልድይ እንዲሁም የአውሮፕላን ደረጃዎች የሚያሻግር መኪና (wheelchair assisting tracks) በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸው እና በተለይም በሀገር ውስጥ በረራ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ጥቅም ላይ የማይውሉ መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ የዐይነ ስውራን አቅጣጫ መጠቆሚያ ነጭ በትር እና የእግር ጉዳተኞች የሚጠቀሙባቸው ክራንቾች ካርጎ እንዲገቡ የሚጠየቅበት ሁኔታ መኖሩ፤ መስማት ለተሳናቸው እና ለዐይነ ስውራን መንገደኞች በአየር መንገዱ ውስጥ ሲስተናገዱም ሆነ በረራ ላይ ሳሉ መረጃ በተገቢው እና በተሟላ መልኩ እንደማይደርስ እንዲሁም በአጠቃላይ ከዓለም አቀፍ በረራዎች አንጻር ሲታይ የሀገር ውስጥ በረራ የአካል ጉዳተኞችን መብቶች በማክበር ረገድ ክፍተት መኖሩ በክትትሉ ከተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የክትትል ግኝቶቹ እና ምክረ ሐሳቦቹ ከደረሱት ጊዜ ጀምሮ አፋጣኝ እርምጃዎች በመውሰድ ተጨባጭ ለውጦች ማድረጉን እና ጊዜ ለሚፈልጉ የተደራሽነት ጥያቄዎች መፍትሔ ለመስጠት ዝርዘር ዕቅድ በማውጣት የጽሑፍ ምላሽ መስጠቱን አስታውሰው፤ “አየር መንገዱ ምክረ ሐሳቦቹን ለመተግበር ያሳየው ተነሳሽነት የሚደነቅ እና በሌሎች ባለድርሻ አካላትም ትምህርት ሊወሰድበት የሚገባ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም የአካል ጉዳተኛ መንገደኞችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ምቹ፣ ተደራሽ እና አካታች ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው፤ አየር መንገዱ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች የአካል ጉዳተኞችን ከባቢያዊ፣ ተቋማዊ፣ የመረጃና ተግባቦት እና የአመለካከት ተደራሽነትን በተሟላ ሁኔታ እንዲያረጋግጥ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።