የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ደቡብ ኦሞ ዞን የኦሞ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላቱ እና መደበኛ የመፍሰሻ መስመሩን ለቆ በመውጣቱ ምክንያት በጎርፍ ከተጥለቀለቁ የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ አካባቢዎች በተለይም ከዳሰነች ወረዳ የተፈናቀሉ ሰዎችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አስመልክቶ ከጥቅምት 5 እስከ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ክትትል በማከናወን የሰብአዊ መብቶች ክትትል ግኝቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን የያዘ ባለ 26 ገጽ ሪፖርት ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማስተባበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ኢሰመኮ ምክረ ሐሳብ በማቅረብ እንዲፈጸም የተለያዩ የውትወታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በተጨማሪም ከነሐሴ 17 እስከ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ኢሰመኮ የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትል እንዲሁም የኦሞ ወንዝ መሙላትን ተከትሎ የቱርካና ሐይቅ መደበኛ ይዞታውን በማስፋት በኦሞራቴ ከተማ እና በተፈናቃዮች ማቆያ ጣቢያዎች ላይ የጋረጠውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ሥጋትን በተመለከተ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል አከናውኗል።
በምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትሉ በዳሰነች ወረዳ በሚገኙ 12 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ 79,073 ለሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ የሆነ የምግብ ድጋፍ በመንግሥት እና በግብረ ሰናይ ድርጀቶች ሲቀርብ የቆየ መሆኑን ኢሰመኮ በበጎ ተመልክቷል። ነገር ግን በኦሞ ወንዝ የላይኛው ተፋሰስ አካባቢዎች ከነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም. የመጀመሪያ ቀናት ጀምሮ በጣለው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ምክንያት የኦሞ ወንዝ ሞልቶ መደበኛ የመፍሰሻ መስመሩን ለቆ በመውጣቱ እና የቱርካና ሐይቅ መደበኛ ይዞታው ሰፍቶ ወደኋላ በመመለሱ (back-flow) ምክንያት የዳሰነች ወረዳ ዋና ከተማ በሆነው የኦሞራቴ ከተማ እንዲሁም በሲየስ፣ ልበሙቀት እና ቻይና ካምፕ በተባሉ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ በውሃ የመጥለቅለቅ ሥጋት ተጋርጦባቸዋል። በባዩ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ 2,744 የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በአካባቢው በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ለዳግም መፈናቀል መዳረጋቸውን ኢሰመኮ በክትትሉ ለመረዳት ችሏል፡፡ በተጨማሪም በስፍራው በተከሰተው የውሃ መጥለቅለቅ ከኦሞራቴ ወደ ነብረሙስ የሚወስደው የአስፋልት መንገድ በመሰንጠቁ ምክንያት ለከባድ ጭነት ተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ሥጋት በመፍጠሩ እና ለተፈናቃዮች በሚደረገው የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ላይ መስተጓጎልን ማስከተሉ የተፈናቃዮቹን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አሳሳቢ አድርጎታል።
በሌላ በኩል ለተፈናቃዮች ሲቀርብ የነበረው የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በመቋረጡ ተፈናቃዮች ንጽሕናው ያልተጠበቀ ውሃ ከኦሞ ወንዝ በመቅዳት እየተጠቀሙ መሆኑን፣ ተፈናቃዮች የሚኖሩባቸው መጠለያ ጣቢያዎች በጎርፍ ውሃ የተከበቡ በመሆናቸው ለወባ በሽታ መጋለጣቸውን፤ የንጹሕ ውሃ አቅርቦት እና በቂ የመጸዳጃ አገልግሎት ባለመኖሩ በአካባቢው የኮሌራ በሽታ ሥጋት ቢኖርም የወባ በሽታ መድኃኒት እና የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር አቅርቦት እጥረት መኖሩን ኢሰመኮ ተመልክቷል። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ሰዎች ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በመፈናቀል ሁኔታ ውስጥ ሲኖሩ የነበረ ቢሆንም ተፈናቃዮቹን በቋሚነት የማቋቋም ሥራዎች ከዕቅድ በዘለለ ወደ ትግበራ አልተገባም።
ስለሆነም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት አካላት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፦
- በኦሞራቴ ከተማ እና በአካባቢው በሚገኙ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ላይ የተጋረጠውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል በወረዳው መንግሥት እና በግብረሰናይ ድርጅቶች የተጀመሩ የመከላከል ሥራዎችን በማጠናከር ተጨማሪ መፈናቀል እንዳይከሰት አፋጣኝ ርብርብ እንዲያደርጉ፤
- ከደቡብ ኦሞ ዞን እና የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት አፋጣኝ እርምጃ የሚፈልጉ ሁኔታዎች ማለትም፤ የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት፣ የወባ በሽታ መድኃኒት፣ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር እና ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽ እንዲያደርጉ፤ እንዲሁም
- ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ባወጣው የክትትል ሪፖርት የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት፤ ከኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች የፌዴራል መንግሥት አካላት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር በዳሰነች ወረዳ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በቋሚነት የማቋቋም ሥራዎች ሊተገብሩ ይገባል።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የሚደርስ መፈናቀል እየተስፋፋ መምጣቱን በቅርብ ጊዜያት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ እና በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ፤ በመሬት መንሸራተት እንዲሁም በማእከላዊ ኢትዮጵያ በስልጤ ዞን በምሥራቅ ስልጢ ወረዳ በጎርፍ ምክንያት የደረሱትን ጉዳቶች አስታውሰው፤ “በመሰል አደጋዎች መፈናቀልን ጨምሮ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ የተፈጥሮ አደጋ ሥጋት ያለባቸውን አካባቢዎች ለይቶ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ከመከላከል አንስቶ በጉዳቱ ልክ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ አስፈላጊ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች መውሰድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል’’ ብለዋል። በተጨማሪም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ተገቢውን ጥበቃ እና ድጋፍ በወቅቱ እንዲያገኙ ርብርብ ሊደረግ የሚገባ ሲሆን በሚወሰዱ እርምጃዎችም ለሴቶች፣ ለሕፃናት፣ ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞች እንዲሁም ተጓዳኝ ሕመም ላለባቸው ሰዎች ትኩረት እንዲሰጥ ኢሰመኮ ጥሪውን ያቀርባል።