የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)  4ውን ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ-ችሎት (4th National High Schools Human Rights Moot Court Competition) ፍጻሜ ውድድር ግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሄደ፡፡ ውድድሩ ከየካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በክልል እና ሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በ12 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የሚገኙ 81 ትምህርት ቤቶች እና 162 ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል።

በክልል እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ በተካሄደው የምስለ ችሎት ውድድር ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ 8 ቡድኖች ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት የሩብ እና የግማሽ ፍጻሜ ሀገር አቀፍ የቃል ክርክር ውድድር ከግንቦት 19 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲያደርጉ ቆይተው በዛሬው ዕለት የፍጻሜ ውድድር አድርገዋል፡፡

በፍጻሜ ውድድሩ ከአዲስ አበባ ከተማ እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡት ተማሪ ተማሪ ስምረት ግርማ እና ተማሪ ሩት ፀጋዬ፤ እንዲሁም ከባሕር ዳር ከተማ ሪስፒንስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የመጡት ተማሪ ስምረተትዕይንት ሚሊዮን እና አማሃሥላሴ ሳልለው የቃል ክርክራቸውን በምስለ ችሎቱ ግራና ቀኝ ቆመው አመልካችና ተጠሪን ወክለው አካሂደዋል። በዚሁ መሠረት ተማሪ ተማሪ ስምረት ግርማ እና ተማሪ ሩት ፀጋዬ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፍጻሜ ውድድሩ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ተማሪ ስምረተትዕይንት ሚሊዮን ከባሕር ዳር ከተማ ሪስፒንስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የውድድሩ ምርጥ የቃል ተከራካሪ በመሆን ያሸነፈች ሲሆን ከአሶሳ ከተማ አሶሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡት ተማሪ ሃይሌ አዳነ አሰፋ እና ተማሪ እየሩሳሌም ከተማ ደግሞ በምርጥ የጽሑፍ ክርክር አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡

የዘንድሮው ውድድር ምናባዊ ጉዳይ ትኩረቱን ያደረገው በሽግግር ፍትሕ ላይ ሲሆን በውስጡ የሽግግር ፍትሕ ዋና አዕማድ በሆኑት እውነትን ማፈላለግ፣ የወንጀል ተጠያቂነት፣ ማካካሻ እንዲሁም የተቋማት እና የሕግ ማሻሻያን የተመለከቱ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ላይ ተመሥርቷል።  ይህም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎች በሽግግር ፍትሕ ሂደቶች ላይ የመካተት እና የመሳተፍ መብትን፣ ነጻና ገለልተኛ በሆነ የዳኝነት አካል አማካኝነት ፍትሕ የማግኘት መብትን፣ ጾታዊ እና ሥርዓተ-ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ሰለባዎች እና የተፈናቃዮች ውጤታማና በቂ የሆነ ማካካሻ የማግኘት መብትን፣ እንዲሁም ጠቅላላ ምሕረትን (blanket amnesty) የተመለከቱ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎችን በማንሳት ተወዳዳሪ ተማሪዎች በመብቶቹ ዙሪያ ጥናት እንዲያደርጉ እና ዕውቀት እንዲያካብቱ አጋጣሚን ፈጥሯል።

የምስለ ችሎት ውድድሩ በሕግና ሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች የተዳኘ እና ከሞላ ጎደል የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የተከተለ አስተማሪ የውድድር ዐይነት ነው። ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተገቢው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ምናባዊ በሆነ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (hypothetical case) ላይ ተመሥርተው አመልካች እና ተጠሪን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር ያደረጉበትም ነው።

በዚህ የፍጻሜ ውድድር ላይ የኢሰመኮ ኮሚሽነሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የክልል ትምህርት ቢሮዎች ተወካዮች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የተወዳዳሪ ተማሪዎች ቤተሰቦች እንዲሁም ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በውድድሩ መክፈቻ ላይ ኢሰመኮ የወጣቶችን የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤን ለማሰደግ ከሚጠቀምባቸው ስልቶች መካከል የምስለ ችሎት ውድድር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተማሪዎች የውድድራቸው ምናብ ያደረጉት የሽግግር ፍትሕ ፅንሰ ሐሳብና ሂደት ሀገራት ከገቡበት ሁለንተናዊ የሰብአዊ መብቶች ቀውስ ሊወጡ የሚችሉበት የተሻለ አማራጭ መሆኑን ተረድተው፣ ይህንኑ በውድድሩ የተለያዩ ዙሮች ላይ ለተሳተፉ ተማሪዎች፣ የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ አባላት፣ ወላጆች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ማስገንዘብ እንደቻሉ አስረድተዋል። አክለውም “የዘንድሮው 4ኛው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር ወቅታዊ እና ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳዎችን ተገንዘቦ አስተዋጽዖ የማድረግ ዐቅም ያለው ትውልድ በማፍራት ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንድንችል ዕድል የሠጠን ነው” ብለዋል።

በአዲሰ አበባ በተካሄዱት የግማሽ እና የሩብ ፍጻሜ ውድድሮች፡-

  1. ተማሪ ስምረት ግርማ ተፈራ እና ተማሪ ሩት ፀጋዬ ሸርታ ከአዲስ አበባ ከተማ እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
  2. ተማሪ ሃይሌ አዳነ አሰፋ እና ተማሪ እየሩሳሌም ከተማ ካሳ ከአሶሳ ከተማ አሶሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
  3. ተማሪ ስምረተትዕይንት ሚሊዮን በላይ እና አማሃሥላሴ ሳልለው ከባሕር ዳር ከተማ ሪስፒንስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት፣
  4. ተማሪ ፎዚያ ቶፊቅ ኤልዳ እና ተማሪ አፈወርቅ ብርሃኔ አስገዶም ከድሬዳዋ ከተማ ሳቢያን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
  5. ተማሪ ኪሩቤል ወንድሙ ተድላ እና ተማሪ ቤተልሔም አድማሱ አመኖ ከጋምቤላ ከተማ ኤላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣
  6. ተማሪ አይሻ ረመዳን እድሪስ እና ተማሪ አሊና መሀዲ አዱስ ከሐረር ከተማ ማሪፍ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት፣
  7. ተማሪ ሮቤል ኢያሱ ኤርሚያስ እና ተማሪ ቤተልሔም ወ/ሚካኤል ላምበሶ ከሆሳዕና ከተማ ሊች ጎጎ ልህቀት አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና
  8. ተማሪ ባዜን ተስፋይ አብርሃ እና ተማሪ ሉላ ኑርሁሴን መሃመድ ኑር ከመቀለ ከተማ ዳዕሮ አካዳሚ በተውዳዳሪነት ተሳትፈዋል።