በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት እ.ኤ.አ. በየዓመቱ ታኅሣሥ 10 ቀን የሚውለውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀን ለማሰብ የተጀመረው ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል 4ኛ ዙር፣ ታኅሣሥ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በይፋ ከተጀመረ በኋላ በሌሎች የክልል ከተሞች መካሄዱን ቀጥሏል።
በሃዋሳ ከተማ ታኅሣሥ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. እንዲሁም በአርባምንጭ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም. የተካሄደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሉ በኢሰመኮ 2016 ዓ.ም. ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት አሳሳቢ ተብለው ከተለዩት ጉዳዮች መካከል “በቂ ምግብ እና በቂ ውሃ የማግኘት መብቶች” ላይ አተኩሯል። በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ የፌስቲቫሉ የሃዋሳና የአርባምንጭ ከተማ ተወዳዳሪዎች፣ የኢሰመኮ የሃዋሳ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች፣ የአርባምንጭ ዩንቨርሲቲ የሕግ ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች የተሳተፉ ሲሆን፣ “አፊኒ” የተሰኘ በታሪኩ መኮንን (ዘታሪያን) ተጽፎ የተዘጋጀ እና ግሩም ኤርሚያስን ጨምሮ በርካታ ስመጥር ተዋንያን የተሳተፉበት ፊልም ለዕይታ ቀርቧል።
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2024/12/Event-update-4%E1%8A%9B%E1%8B%8D-%E1%8B%93%E1%88%98%E1%89%B3%E1%8B%8A-%E1%8B%A8%E1%88%B0%E1%89%A5%E1%8A%A0%E1%8B%8A-%E1%88%98%E1%89%A5%E1%89%B6%E1%89%BD-%E1%8D%8A%E1%88%8D%E1%88%9D-%E1%8D%8C%E1%88%B5%E1%89%B2%E1%89%AB%E1%88%8D-%E1%89%A0%E1%88%83%E1%8B%8B%E1%88%B3-%E1%8A%A5%E1%8A%93-%E1%8A%A0%E1%88%AD%E1%89%A3%E1%88%9D%E1%8A%95%E1%8C%AD-%E1%8A%A8%E1%89%B0%E1%88%9E%E1%89%BD-%E1%89%B0%E1%8A%AB%E1%88%84%E1%8B%B0.jpeg?resize=1024%2C768&ssl=1)
“አፊኒ” ፊልም በቀልን እና ለደረሰባቸው ጥፋት መፍትሔን የሚፈልጉ ሁለት ባላንጣ ቤተሰቦችን ምናባዊ ታሪክ የሚያሳይ ሲሆን፣ በሲዳማ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ ያተኮረ ነው። ፊልሙ፣ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ምንም እንኳን ውስንነቶች ቢኖሩባቸውም አሁንም በኢትዮጵያ በበርካታ አካባቢዎችና ማኅበረሰቦች የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ የሚጫወቱትን ትልቅ ሚና እያስቃኘ እነዚህን ዘዴዎች ከሰብአዊ መብቶች አንጻር ለመገምገም ይጋብዛል።
በየዓመቱ የሚካሄደው የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ዋነኛ ዓላማ ዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብቶች ቀን ከማሰብ ጎን ለጎን የኪነ ጥበብን እና የሰብአዊ መብቶችን ትስስር ማጠናከር፣ በሁለቱ ዘርፎች መካከል ያለውን ጥምረት በተመለከተ ግንዛቤ ማስፋፋት፣ እንዲሁም “ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት” የሚለውን የኢሰመኮ ራዕይ ለማሳካት ኪነጥበብ ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማስታወስ ነው።
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2024/12/Event-update-4%E1%8A%9B%E1%8B%8D-%E1%8B%93%E1%88%98%E1%89%B3%E1%8B%8A-%E1%8B%A8%E1%88%B0%E1%89%A5%E1%8A%A0%E1%8B%8A-%E1%88%98%E1%89%A5%E1%89%B6%E1%89%BD-%E1%8D%8A%E1%88%8D%E1%88%9D-%E1%8D%8C%E1%88%B5%E1%89%B2%E1%89%AB%E1%88%8D-%E1%89%A0%E1%88%83%E1%8B%8B%E1%88%B3-%E1%8A%A5%E1%8A%93-%E1%8A%A0%E1%88%AD%E1%89%A3%E1%88%9D%E1%8A%95%E1%8C%AD-%E1%8A%A8%E1%89%B0%E1%88%9E%E1%89%BD-%E1%89%B0%E1%8A%AB%E1%88%84%E1%8B%B0-3.jpeg?resize=1024%2C768&ssl=1)
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2024/12/Event-update-4%E1%8A%9B%E1%8B%8D-%E1%8B%93%E1%88%98%E1%89%B3%E1%8B%8A-%E1%8B%A8%E1%88%B0%E1%89%A5%E1%8A%A0%E1%8B%8A-%E1%88%98%E1%89%A5%E1%89%B6%E1%89%BD-%E1%8D%8A%E1%88%8D%E1%88%9D-%E1%8D%8C%E1%88%B5%E1%89%B2%E1%89%AB%E1%88%8D-%E1%89%A0%E1%88%83%E1%8B%8B%E1%88%B3-%E1%8A%A5%E1%8A%93-%E1%8A%A0%E1%88%AD%E1%89%A3%E1%88%9D%E1%8A%95%E1%8C%AD-%E1%8A%A8%E1%89%B0%E1%88%9E%E1%89%BD-%E1%89%B0%E1%8A%AB%E1%88%84%E1%8B%B0-4.jpeg?resize=1024%2C768&ssl=1)
![](https://i0.wp.com/ehrc.org/wp-content/uploads/2024/12/Event-update-4%E1%8A%9B%E1%8B%8D-%E1%8B%93%E1%88%98%E1%89%B3%E1%8B%8A-%E1%8B%A8%E1%88%B0%E1%89%A5%E1%8A%A0%E1%8B%8A-%E1%88%98%E1%89%A5%E1%89%B6%E1%89%BD-%E1%8D%8A%E1%88%8D%E1%88%9D-%E1%8D%8C%E1%88%B5%E1%89%B2%E1%89%AB%E1%88%8D-%E1%89%A0%E1%88%83%E1%8B%8B%E1%88%B3-%E1%8A%A5%E1%8A%93-%E1%8A%A0%E1%88%AD%E1%89%A3%E1%88%9D%E1%8A%95%E1%8C%AD-%E1%8A%A8%E1%89%B0%E1%88%9E%E1%89%BD-%E1%89%B0%E1%8A%AB%E1%88%84%E1%8B%B0-2.jpeg?resize=1024%2C768&ssl=1)
ኢሰመኮ በዘንድሮው 4ኛ ዙር ፌስቲቫል ውድድር የሚካሄድባቸውን የኪነጥበብ ዘርፎች በማስፋት፣ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ይዘት ጥራት ለማሳደግ የሚረዱ ውድድሮችና መሰል አሳታፊ ዝግጅቶችን በማካተት፣ የሚሳተፉ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን እንዲሁም ዝግጅቶቹ የሚካሄዱባቸውን ከተሞች ብዛት በመጨመር የፎቶግራፍ፣ የአጫጭር ሥነ ጽሑፍ ሥራዎች እና የሥዕል ውድድሮችን አካሂዷል።
በሁለቱም ከተሞች ትኩረቱን በቂ ምግብና ውሃ በማግኘት መብቶች ላይ ያተኮረ የፎቶግራፍ ውድድር ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በይፋ ተጀምሮ እስከ ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ለተወዳዳሪዎች ክፍት ሆኖ ቆይቷል። በውድድሩ ከ50 በላይ ፎቶግራፎች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን በዝግጅቶቹ ወቅት አሸናፊዎች ይፋ ተደርገዋል። በዚህም መሠረት፦
በሃዋሳ ፎቶግራፍ ውድድር:-
1ኛ. ሢፈን መርጋ ገመቹ (ውሃ ለሕይወት)
2ኛ. አወቀ አበበ (ሰውና ተፈጥሮ)
3ኛ. ወንጌል ዮሐንስ (ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ማግኘት መብቴ ነው)
በአርባምንጭ ፎቶግራፍ ውድድር፦
1ኛ. ፋሲል ኃይሉ ግብሩ (ለመኖር)
2ኛ. ይዲዲያ አዲሱ (ማጣት ክፉ)
3ኛ. ቤተልሔም አበራ (የዘገየ ተስፋ)
በፌስቲቫሉ ለውድድሩ ተሳታፊዎችም የዕውቅና ሰርተፊኬት የተበረከተ ሲሆን ለዕይታ በቀረበው ፊልም ላይ የተንጸባረቁ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል።
የኢሰመኮ የሃዋሳ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በጋሻው እሸቱ “ኪነጥበብ እውነታዎችን ለማሳየት፣ ታሪክን ለማስታወስ፣ የቁጭት እና ንዴት ስሜቶችን ለመግለጽ፣ ሰዎችን እና ማኅበረሰቦችን ለለውጥ ለማነሳሳት እና ብዙ ጊዜ የማይሰሙ ድምፆችን ለማጉላት ትልቅ ኃይል አለው” ብለዋል። አያይዘውም፣ ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ዕውን በማድረግ ረገድ በኪነጥበብ እና የፈጠራ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች አስተዋጽዖ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው፣ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫሉን ቀጣይነት አስረድተዋል።