የባለሞያ አስተያየት ከኢሰመኮ
ጥበቡ ኃይሉ
ተባባሪ የሰብአዊ መብቶች ኦፊሰር
የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል
በኢትዮጵያ ምን ያህል መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንዳሉ ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፤ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ ከመስማት ጋር የተገናኘ ጉዳት ያለባቸው ሰዎች እንደሚኖሩ ይገመታል።
ከኢትዮጵያ የብሔር ብዝኃነት አንጻር ተጨማሪ ቋንቋዎችን በሥራ ቋንቋነት ለማካተት የሚያስችል የቋንቋ ፖሊሲ በቀረጻ ሂደት ላይ መሆኑ ቢታወቅም፤ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የግድ አስፈላጊ የሆነውን የምልክት ቋንቋን የሥራ ቋንቋ ለማድረግ በቂ ትኩረት አላገኘም፡፡
ለዚህ ክፍተት በርካታ ምክንያቶች ውስጥ፤ መስማት የተሳናቸው ዜጎች በሀገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መድረኮች ያላቸው ተሳትፎ ውስን መሆንና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት አነስተኛ መሆንን ይጨምራል፡፡ መስማት የተሳናቸው ዜጎች ከማኅበራዊ ግንኙነቶች መገለልን ጨምሮ ለመሰረታዊ አገልግሎቶችና ለሥራ ዕድሎች ውስን ተደራሽነት እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸውና ከማኅበረሰባቸው ጋር ለመግባባት መቸገርን ከመሳሰሉ ተግዳሮቶች ጋር ለመኖር ተገድደዋል፡፡
የምልክት ቋንቋ በዓይን የሚታይ፣ በእጅ፣ በፊትና በሰውነት እንቅስቃሴ የሚገለጽ ምስላዊ ቋንቋ ነው፡፡ የምልክት ቋንቋዎች የራሳቸው ሰዋሰው፣ መዝገበ ቃላት እና ዘዬ ያላቸው የተሟሉ፣ ቋንቋዎች ሲሆኑ፤ ከውልደት ጀምሮ መስማት ለተሳናቸው ሕጻናት ደግሞ ብቸኛ የመጀመሪያ ቋንቋቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋን (EthSL) ጨምሮ በመላው ዓለም ከ140 በላይ የተመዘገቡ የምልክት ቋንቋዎች ይገኛሉ።
ከአፍሪካ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኡጋንዳ እና ዙምባቡዌን ጨምሮ ከ70 በላይ ሀገራት የምልክት ቋንቋን በተለያየ ዓይነት መንገድ የሕግ እውቅና በመስጠት በሥራ ቋንቋነት ይጠቀሙበታል፡፡ በዚህም መሰረት የምልክት ቋንቋ ከሕግ ማውጫ ምክር ቤት (ፓርላማ) ጀምሮ በልዩ ልዩ መስሪያ ቤቶችና አገልግሎት መስጫ ቦታዎች በጥቅም ላይ እንዲውል፣ በምልክት ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ፣ ይፋዊ ሰነዶችና ግንኙነቶች በምልክት ቋንቋም እንዲቀርቡ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነትን በአዋጅ ቁጥር 676/2002 አጽድቃ ተቀብላለች። በዚህ ስምምነት መሰረት፡-
[መስማት የተሳናቸው ሰዎች] የሕይወትና የማኅበራዊ እድገት ክህሎት እንዲያገኙ ብሎም በማኅበረሰባቸው ውስጥ ሙሉና ውጤታማ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል ፈራሚ ሀገራት የምልክት ቋንቋ ትምህርትን የማመቻቸትና የማበረታታት ግዴታ አለባቸው፡፡ (አንቀጽ 24፣ 3/ለ)
በተጨማሪም፤
ፈራሚ ሀገራት [መስማት የተሳናቸው ሰዎች] በሁሉም የሕግ አሠራር ሂደቶች ከሌሎች ጋር በእኩልነት አስተማማኝ የፍትሕ ተደራሽነት ማግኘታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ (አንቀጽ 13)
የስምምነቱ ፈራሚ ሀገራት መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር በእኩልነት ሙሉና አስተማማኝ ተሳትፎ ከማድረግ ሊያደናቅፏቸው የሚችሉ የአመለካከት፣ ከባቢያዊ፣ የተግባቦት እና ተቋማዊ መሰናክሎችን ለማስወገድ የሚረዱ እርምጃዎችን የመውሰድ ግዴታ አለባቸው፡፡ የአፍሪካ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ፕሮቶኮልም ተመሳሳይ ግዴታን የያዘ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ልታጸድቀው የሚገባ አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ሰነድ ነው፡፡
የዓለም አቀፉ ስምምነት መሰረታዊ መርሆዎች መካከል “ልዩነትን ማክበርና አካል ጉዳተኞች የሰው ልጅ የልዩነት ብዛኃነትና ሰብአዊነት አካል መሆናቸውን መቀበል” የሚለው መርህ ለዚህ ጉዳይ አግባብነት አለው፡፡ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በምልክት ቋንቋ የመማር መብትን ጨምሮ በእኩልነት የፍትሕ ተደራሽነት፣ መረጃ የማግኘት፣ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች የተሟላ ተሳትፎ የማድረግ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማግኘት መብቶች አሏቸው፡፡ በስምምነቱ አንቀጽ 9 የተጠቀሱት የመረጃ ተደራሽነትና የግንኙነት መብቶች ደግሞ ለእነዚህ መብቶች መሟላት መሰረታዊ መሆናቸውን ልብ ማለት አስፈላጊ ነው፡፡ በተጨማሪም፤ ለምልክት ቋንቋ እውቅና በመስጠት ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ፖሊሲ መቅረጽ አካል ጉዳተኞችን አካታች የሆነ አሰራር አንዱ አካል መሆኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአካል ጉዳተኞች መብቶች ልዩ መልዕክተኛ/ዘጋቢ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡
በኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋን የመጠቀም ልምድ በተወሰኑ ስብሰባዎች፣ ሕዝባዊ ዝግጅቶች እና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ቀስ በቀስ እየታየ የመጣ ቢሆንም፤ አስፈላጊው የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ሊያድግና ሊስፋፋ አልቻለም፡፡
የምልክት ቋንቋ ትምህርትም እምብዛም እድገት ሳያሳይ የቆየ ሲሆን፤ ትምህርቱ በኢትዮጵያ መሰጠት ከጀመረበት ከ1970ዎቹ አንስቶ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ብቻ በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ የሚሰጠውን ፕሮግራም ጨምሮ በጥቂት ትምህርት ቤቶች ብቻ ይሰጣል፡፡ ይህም ከሀገሪቱ ስፋትና መስማት ከተሳናቸው ዜጎች ቁጥር አንጻር የምልክት ቋንቋ ትምህርት ተደራሽነት አነስተኛ መሆኑና የቋንቋው ዕድገትም ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት መስማት የተሳናቸው ሰዎችን በምልክት ቋንቋ ማስተማር ጥሩ ተግባቦት እንዲኖራቸው ማድረግን ጨምሮ ከተሳትፎ፣ ከሕይወት ክህሎት እንዲሁም ከሥነ-ቋንቋና ፔዳጎጂ ጋር የተያያዙ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ትምህርት አሰጣጥና አተገባበርን በተመለከተ የትምህርት ሥርዓት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ገና ብዙ እርምጃዎች ይጠበቅበታል፡፡ ለምሳሌ ትግበራው እ.ኤ.አ በ2026 የሚጠናቀቀው የኢትዮጵያ የልዩ ፍላጎት (አካቶ) ትምህርት መሪ ዕቅድ ላይ ከተቀመጡ የውጤት መስኮች መካከል በተለይም በምልክት ቋንቋ ማስተማርን የሚደነግግ አስገዳጅ የትምህርት ሕግ ማውጣት የሚለው የውጤት መስክ 1 አሁን ድረስ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች ገና ተፈጻሚ አልሆነም፡፡ (ሆኖም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደረጃ በአዋጅ ቁጥር 1152/2011 መሰረት አስገዳጅ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡
በሌላ በኩል በቅርቡ የወጣው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ በየደረጃው ያሉ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የምልክት ቋንቋን ለሚጠቀሙ ሰዎች የምልክት ቋንቋ ችሎታ ያለው ባለሙያ የመመደብ እና የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የአስተርጓሚ ቢሮ የማደራጀት ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ (አዋጅ ቁ.1234/2013፣ አንቀጽ 31 ንዑስ 3 እና 4)
ይሁንና፤ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርቡ ይፋ ያደረገው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተገልጋዮች የእርካታ ዳሰሳ ጥናት፤ የምልክት ቋንቋ ትርጉም አገልግሎት ተገልጋዮች የእርካታ መጠን ዝቅተኛ መሆኑን አመላክቷል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ካስቀመጣቸው ቁልፍ የውጤት መስኮች መካከል የፍርድ ቤቶች አሠራርና አገልግሎትን መስማት ለተሳናቸው ጨምሮ ልዩ ፍላጎት ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ ይገኝበታል። ከዚህ አንጻር የምልክት ቋንቋ ትርጉምን በማሳደግ ብሎም የሕግ እውቅና በመስጠት እና አገልግሎቱን ወደ ሁሉም ክልሎች ፍርድ ቤቶችም በማስፋፋት መስማት የተሳናቸው ሰዎችን ፍትሕ የማግኘት መብት ማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
የምልክት ቋንቋን ይፋዊ የሥራ ቋንቋ ማድረግ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች መረጃ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ፣ በማኅበረሰብ ውስጥ በሁሉም ዘርፍ የሚኖራቸውን የተሳትፎ መጠንና የአገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ ብሎም ሰብአዊ መብቶቻቸው ሙሉና ውጤታማ በሆነ ደረጃ እንዲረጋገጡ ለማስቻል አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡
ስለሆነም የምልክት ቋንቋን የሥራ ቋንቋ መሆኑን የሚደነግግና የሚያስተገብር የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ እና የአፈጻጸም ስትራቴጂዎች በተጨማሪ የምልክት ቋንቋን ከሕግ አውጪ ምክር ቤቶች ጀምሮ በልዩ ልዩ ሕዝባዊ አገልግሎት መስጫዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመገናኛ ብዙኃንና በሌሎችም ዘርፎች እንዲስፋፋ ማድረግ አስፈላጊ እርምጃዎች ናቸው፡፡