የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ‘የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች እና ሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ’ በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ የሠራተኛ ማኅበራት አባላት፣ የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ተሳታፊዎች እንዲሁም የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ተወካዮች በተገኙበት ባሳለፍነው አርብ ሰኔ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አዘጋጅቷል፡፡
የውይይት መድረኩ ላይ የኢሰመኮ የሲቪል፣ ፖለቲካዊ እና የማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ሀገሪቱ የሠራተኞች መብቶችን በሚመለከት በሕገ-መንግሥቱ ካሉ ጉዳዩን ከሚመለከቱ ድንጋጌዎች በተጨማሪ የኢኮኖሚያዊ፣ የማኅበራዊና ባሕላዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን፣ አግባብነት ያላቸው የዓለም ሥራ ድርጅት ስምምነቶችን እና የመሳሰሉ የተለያዩ የሠራተኞች መብቶችን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብላ ማፅደቋን በማብራራት ጀምረዋል። በመሆኑም “መንግሥት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በእነዚህና መሰል ድንጋጌዎች ውስጥ ለተዘረዘሩ መብቶች መከበር መሥራት አለባቸው” ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ ዶ/ር አብዲ አክለውም መድረኩ የተዘጋጀው ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የሠራተኞች የመብት ሁኔታ በምን መልኩ ለማሻሻል እንዲሁም አሁን ያሉ የመብቶች ጥሰቶችን በምን መልኩ ለማስቆም እንደሚቻል ግብዓት ለመሰብሰብ እና ለመመካከር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በስብሰባው በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውንና የኤጀንሲ ሠራተኞች መብቶችን በተመለከተ ያለውን የሕግ ማዕቀፍ የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያ ገልጻ ያደረጉ ሲሆን፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ ተሳታፊዎች በሠራተኞች ላይ የሚስተዋለው ስለ ሕጎቹ እና ስለመብቶቻችው ያለው የመረጃ እና የፋይናንስ አቅም ማነስ የሕጎቹ አፈጻጸም ላይ እክል ሲፈጥር እንደሚታይ ጠቁመዋል፡፡
የኤጀንሲ ሠራተኞች መብቶች አተገባበርን በሚመለከት በኢሰመኮ የተደረገ የክትትል ሪፖርት ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ-ሃሳቦችም በምክክር መድረኩ ቀርበዋል፡፡ የክትትሉ ግኝቶች የኤጀንሲ ሠራተኞች መብቶች በተለይም ምቹ የሥራ ሁኔታዎችን የማግኘት፣ የእኩልነትና ከአድልዎ ነፃ የመሆን እንዲሁም የሥራ ዋስትና የማግኘት መብቶች እየተጣሱ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
እነዚህ ጉዳዮች ላይ በመመርኮዝ ተሳታፊዎች የቡድን ውይይት በማድረግ የሚስተዋሉ ችግሮችን እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል፣ ከሚወክሏቸው ተቋማት በኩልም ችግሮቹን ከመቅረፍ አንጻር ምን እንደሚጠበቅ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም የኢሰመኮ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ ጉዳዩ ሁሉንም ባለድርሻዎች የሚመለከት መሆኑን በመግለጽ ውይይቱ ተገቢውን ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንጻር መልካም ጅማሮ እንደሆነና ከባለድርሻ አካላቱ ጋር የሚኖረው ሥራ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል፡፡