የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ፤ እንዲሁም ምርጫ ማድረግ ባልተቻለባቸው ቦታዎች እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. በተደረገው የምርጫ ሂደት ዙሪያ ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ክትትል ረቂቅ ሪፖርት ላይ የተለዩ የአፈጻጸም ክፍተቶች ዙሪያ ኅዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች እና የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል፡፡ ኮሚሽኑ የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተገኙበት በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ ጥቅምት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት በማካሄድ ሃሳቦች እና ግብአቶች መወሰዳቸው ይታወሳል።
ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በምርጫው ከነበራቸው ተሳትፎ እና አጠቃላይ የምርጫው ሂደት የነበረው ተደራሽነት እና አካታችነት አንጻር የተስተዋሉ ክፍተቶች ለውይይቱ በመነሻነት ቀርበዋል።
በውይይቱ ላይ ከተነሱ አንኳር ሃሳቦች እና ግብአቶች መካከል የምርጫ ነክ ቅሬታዎችን የሚመለከት የቅሬታ ማቅረቢያ ሥርዓት በሁሉም የምርጫ ክልሎች በተገቢው ሁኔታ ተደራጅተው አለመቋቋማቸው፣ በፍርድ ቤቶች በኩል የምርጫ ነክ ክርክሮችን የሚዳኙ ችሎቶች ያልተደራጁባቸው አካባቢዎች መኖራቸው እንዲሁም ምርጫ ያልተከናወነባቸው ቦታዎችን በተመለከተ ያሉበት ሁኔታ ግልፅ ሆኖ አለመቀመጡ በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡
የኮሚሽኑ ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች ከምርጫ ቦርድ በተጨማሪ በተለያየ መዋቅር የሚገኙ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ፣ የሰላም እና የጸጥታ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የሚመለከት በመሆኑ ኮሚሽኑን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡ በተለይ ኮሚሽኑ እና የምርጫ ቦርዱ በመተባበር እና በጋራ ሊሠሯቸው የሚገቡ ጉዳዮች በውይይቱ ተለይተዋል፡፡
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ላይ የታዩትን መልካም ጎኖች እና ቦርዱ እያደረገ ያለውን ጥረት ማበረታታት እና እውቅና መስጠት እንደሚያስፈግ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ወደፊት መሻሻል የሚገባቸው በሪፖርቱ የተለዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል በትብብር መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ምርጫን በተመለከተ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታን መከታተል፣ ጥሰቶችን መለየት እና ግኝቶችን መሰረት አድርጎ የእርምት እና የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ምክረ ሃሳብ በመስጠት የጉትጎታ ሥራ እንደሚሠራ አስታውሰዋል። አክለውም በሀገሪቱ የተሻለ የምርጫ ዑደት እንዲኖር መልካም አሠራሮችን ተቋማዊ ማድረግ እና ክፍተቶችን በጋራ ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡