የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ያዘጋጀውን ይህን ሁለተኛውን ዓመታዊ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት (Ethiopia Annual Human Rights Situation Report) ይፋ ሲያደርግ፣ ሪፖርቱ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ያለውን ፋይዳ እና ምክረ ሐሳቦቹ ሥራ ላይ እንዲውሉ ኮሚሽኑ የዛሬ ዓመት በ2014 ዓ.ም. ሪፖርቱ ያቀረበውን ጥሪ በድጋሚ በማስታወስ ነው። ይህ ሪፖርት በቀዳሚነት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰብአዊ መብቶችን ሁኔታ ለውጥና አፈጻጸም በተመለከተ በአስፈጻሚው አካል ላይ የሚያደርገውን ክትትል የሚያግዝ ቢሆንም፣ የቀረቡት ምክረ ሐሳቦችን የማስፈጸም ኃላፊነት ካለባቸው መንግሥታዊ ተቋማት በተጨማሪ የሲቪክ ማኅበራት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማትና አጋሮች ሀገራዊውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል ለሚያካሄዷቸው ጥናቶች እና ለሚያከናውኗቸው ሌሎች ተግባራት መነሻና ግብዓት እንዲሆን የታለመ ነው። ስለሆነም ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታውን ለማሻሻል የሁሉም ባለድርሻዎች አስተዋጽዖ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት ሪፖርቱ በእርግጥም ለሁሉም ባለድርሻዎች ውጤታማ የሆነ ጠቀሜታ እንዲኖረው ኮሚሽኑ የሚያደርገውን ጥረት የሚቀጥል ይሆናል።
ይህ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ሁለተኛው እንደመሆኑ መጠን ከአምናው በጀት ዓመት ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አንጻር በዘንድሮ በጀት ዓመት የታዩ መሻሻሎችን፣ እንዲሁም ለውጥ ያላገኙ እና ወደ ኋላ የተመለሱ ጉዳዮችንም ይጠቁማል፡፡ በ2014 ዓ.ም. በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በርካታ አካባቢዎች ሲካሄድ የነበረውን እና እጅግ በርካታ ሰዎችን ለተለያዩ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ለሞት፣ ለአካልና ለሥነ-ልቦና ጉዳት፣ ለጾታዊና ወሲባዊ ጥቃት፣ ለመፈናቀልና፣ ለንብረት ውድመት የዳረገው ጦርነትን የሚያስቆም ዘላቂ የተኩስ አቁምና የሰላም ስምምነት መደረጉ በዘንድሮ በጀት ዓመት ከተመዘገቡት መልካም እመርታዎች ዋነኛው እና በአንጻራዊ መልኩ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታውን በማሻሻል ረገድ ሰፊውን ድርሻ የሚይዝ ነው።
ሆኖም በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች እልባት ያላገኙ፣ በተለያየ ጊዜ የሚያገረሹ ወይም በአዲስ መልኩ የሚከሰቱ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃቶች እና የትጥቅ ግጭቶች አሁንም ዘላቂ ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ መፍትሔ ያልተሰጣቸው በመሆኑ፣ ቀዳሚ የሆነውን የሰዎች በሕይወት የመኖር መብት፣ ሰላም እና ደኅንነት ላይ ትርጉም ያለው መሻሻል አልታየም። በየአካባቢዎቹ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ሳቢያ፣ በመንግሥት እና በታጣቂ ኃይሎች መካከል ወይም በተለያዩ የታጣቂ ኃይሎች መካከል በሚደረጉ ውጊያዎች ሳቢያ በርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሰዎች እና ለመደበኛ እንቅስቃሴ ተደራሽ አለመሆናቸው ከግንዛቤ ውስጥ ሲገባ፣ መሠረታዊ የሆነውን የሰዎች በሕይወት የመኖር መብት፣ ሰላም እና ደኅንነት እንዳልተረጋገጠ የሚያሳይ ነው።
በመሆኑም በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ መልካም ጅማሮዎችን እና እመርታዎችን መሠረታዊ ከሆነው ከሰዎች በሕይወት የመኖር መብት ሁኔታ አንጻር የሚገመገሙ ናቸው። ሰዎች በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ ከቦታ ቦታ በነጻነት የመንቀሳቀስ እና የመሥራት መብቶቻቸው ባልተከበረበት ሁኔታ የተመዘገቡ መልካም ለውጦች ዘላቂነት አይኖራቸውም።
በዘንድሮው የበጀት ዓመት የተጀመረውና በ2016 በጀት ዓመት ኢሰመኮ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ ከሚከታተላቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነው የሽግግር ፍትሕ ሂደት/ሥርዓት የመዘርጋት ሂደትን በተመለከተ የታዩ ጅማሮዎች አበረታች ቢሆኑም፤ለሽግግር ፍትሕ ሂደቱ አመቺ ሁኔታን መፍጠርም በመንግሥት በኩል ከፍተኛ እና ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ “የሽግግር ፍትሕ ማሕበረሰቦች ያለፉበትን መጠነ ሰፊ ጉዳቶችን፣ ጥሰቶች፣ ክፍፍሎችን፣ እና አለመመጣጠኖችን ለማስተካከል እና መፍትሔ/እልባት ለመስጠት፤ ፍትሕን ለማስፈን እና እርቅን ለማውረድ፤ ለደኅንነትም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሥርዓት ግንባታ፤ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ መደበኛ እና ባህላዊ/መደበኛ ያልሆኑ ሂደቶች፣ መዋቅሮች፣ እና ተቋማዊ አሠራሮችን በመጠቀም የሚተገበር ሁሉን አቀፍ የፍትሕ ሂደት ነው”። የሽግግር ፍትሕ እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉና የሚዛመዱ እውነትን የመፈለግ፣ የማረጋገጥና ይፋ የማድረግ፣ ተጠያቂነትን የማስፈን፣ ለተጎጂዎች ምሉዕ ማካካሻ የማግኘት እንዲሁም፣ ጥሰቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማድረግን የሚያካትቱ አራት ዋና ዋና ግቦችና ሂደቶችን የያዘ ነው።
ሆኖም የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ተዓማኒነት መንግሥት በሕብረተሰቡ ዘንድ አስፈላጊውን እምነት የመገንባት እርምጃዎችን በመውሰድ አቅም ላይ ሙሉ በሙሉ የተመሠረተ ነው። ስለሆነም አሁንም ለቀጠሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተገቢውን ምላሽ መስጠት እና ለዘላቂ መፍትሔም ተጨባጭ ጥረት ማድረግና ተገቢውን እርምጃዎች መውሰድ ለውጤታማ የሽግግር ፍትሕ አስተዳደር መታለፍ የማይችል ቅድመ ሁኔታ ነው።
ኮሚሽኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት ይፋ ባደረጋቸው ሪፖርቶች እና ልዩ ልዩ መልዕክቶች በተደጋጋሚ እንዳመላከተው፣ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዋነኛው የሥር መንስዔዎች ውስጥ የሕግ የበላይነት እና ተጠያቂነት ማስፈን አለመቻል እና ለፖለቲካዊ ቀውሶች ፖለቲካዊ መፍትሔ ማግኘት አለመቻል ናቸው። የሕግ የበላይነት መኖር ወይም አለመኖር በእያንዳንዱ ሰው እና የማኅበረሰብ ክፍል የዕለት ተዕለት ሕይወት ቀጥተኛና ፈጣን የሆነ ተጽዕኖ የሚያሳድር እና ለማኅበረሰቡ ደግሞ “የፍትሕ መኖር ወይም አለመኖር” ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ወይም በዛ የሚመሰል ነው።
የሕግ የበላይነት ላለመኖሩ እርስ በእርሳቸው ተመጋጋቢ የሆኑ ምክንያቶች እና አመላካቾች ደግሞ፡ 1/ በሕግ የተደነገገውን አሠራር በቂ ባልሆነ ምክንያት ወደ ጎን በመተው ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ አሠራሮች፣ ድርጊቶች ወይም ሂደቶች፣ 2/ በሕግ የተደነገገውን በማስፈጸም ሂደት ተገቢውን የተሳትፎ፣ የምክክር እና የጥሞና ጊዜ ሳይወስዱ ለማስፈጸም መሞከር፣ 3/ ተቋማት በሕግ ከተሰጣቸው ሥልጣን ወሰን ውጪ/በመተላለፍ አልያም ከወሰኑ በታች/ሥልጣን እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት እንዲሁም 4/ የተጠያቂነት አለመኖር (impunity) ናቸው።
በዚህ ሪፖርት ውስጥ በዋና ዋና አሳሳቢነት የተመላከቱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዋነኛ የሥር ምክንያቶች ውስጥ የሕግ የበላይነት እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ መላላት ነው፡ የዘፈቀደ እስር፣ አስሮ የመመርመር፣ ተዓማኒ ክስ ያለማቅረብ ጀምሮ እስከ ኢሰብአዊ እና ጭካኔ የተሞላበት አያያዝ እና አስገድዶ መሰወር ያሉ ጥሰቶች ሥር መሠረታቸው የሕግ በላይነት አለመከበር ነው።
በግጭት እና በጦርነት ዐውድ ውስጥ ለተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂነት ማረጋገጥ ረዥም ጊዜ የሚፈልግ፣ ከፍተኛ የሰው ኃይል እና የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ እና ውስብስብ ሂደት ነው። ሆኖም በወቅታዊው የሀገሪቱ አቅም እና ባሉት የፍትሕ እና የአስፈጻሚ አካላት ተቋማት ቁርጠኝነት ብቻ ሊፈቱ የሚችሉ የአሠራር እና የፖሊሲ ክፍተቶችን በመሸፈን በአሁኑ ወቅት ያለውን ከፍተኛ የሕግ የበላይነት አለመከበር ችግር በእጅጉ ማሻሻል ይቻላል፣ ይገባል።
በተጨማሪም ኢሰመኮ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም እንደመሆኑ መጠን በኮሚሽኑ ተደራሽነት ላይ ሊኖሩ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ወይም እንቅፋቶችን መከላከል ይገባል። ይልቁንም በኢሰመኮ ላይም ሆነ ሚድያን ጨምሮ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተደራሽነት ላይ የሚደረጉ እንቅፋቶች በአካባቢው ወይም በሀገሪቱ ስላለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ትክክለኛ መረጃዎች እንዳይወጡ ወይም እውነተኛ ሁኔታውን የማያመላክቱ እና ማኅበረሰቡን ይበልጡን እምነት የሚያሳጡ መረጃዎች እንዲስፋፉ ምክንያት ይሆናሉ።
ይሁንና በዘንድሮ በጀት ዓመት ከዘላቂ የተኩስ አቁም እና ሰላም ስምምነቱ እና ከሽግግር ፍትሕ ሂደቱ በተጨማሪ ሀገራዊውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሰፋ ባለ መልኩ የሚያሻሽል ለውጥ እምብዛም አለመኖሩና አልፎ አልፎም ከሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ አንጻር ወደ ኋላ የመንሸራተት አደጋ ምልክቶች መታየታቸው ለተስፋ መቁረጥ እና ከሚደረጉ ጥረቶች ለመገለል ምክንያት ሊሆኑ አይገባም። ይልቁንም ለሰላም፣ ለመግባባት፣ መተማመንን ለማስፋፋት፣ በልዩ ልዩ አካባቢዎች ተቋርጠው የቆዩ የትምህርት፣ የጤና እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩና እንዲስፋፉ፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን አመቺ የሆኑ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ድጋፍ እንዲያገኙ፣ ሴቶች እና ሕፃናት ከጾታዊ ጥቃት እንዲጠበቁ፣ የጥላቻ እና የሐሰት ንግግሮች እንዲጠፉና የፖለቲካ እና የሃይማኖት መካረር እንዲወገድ፣ ሰዎች ሁሉ በሀገሪቱ በነጻነትና በሰላም እንዲንቀሳቀሱና ከማናቸውም ዓይነት ጥቃት እንዲጠበቁ የሚያደርጉ ማናቸውም ዓይነት አስተዋጽዖች በእጅጉ የሚያስፈልጉበት ወቅት አሁን ነው።
ስለሆነም በሁሉም የኮሚሽናችን ባልደረቦች እና በእራሴ ስም “ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን” ለማየት የሚደረገው ጉዞ እያንዳንዳችን እራሳችን የምናደርገውን አስተዋጽዖ ከማጤን እና ከማጠናከር እንዲጀመር ጥሪ በማስተላለፍ ነው።