የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ሁለተኛውን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ባለ 60 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ሁለተኛው የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ በተጨማሪነት ኮሚሽኑ የተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ የለያቸውን መልካም ጅማሮዎች፣ አሳሳቢ ሁኔታዎችንና ምክረ ሐሳቦችን አካቷል።
ኢሰመኮ በአፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሶማሊ ክልሎች በግጭት እና ሌሎች ሰው ሠራሽ መንሥዔዎች የተፈናቀሉ ከ369 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን፣ ተመላሾችን እና ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ የተደረጉ ተፈናቃዮችን የሚያስጠልሉ 62 መጠለያዎችን፣ ጣቢያዎችን እና ተቀባይ ማኅበረሰቦችን በመድረስ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አያያዝ ላይ ክትትሎች እና ምርመራዎችን በማካሄድ ሪፖርቱን አጠናቅሯል። ሪፖርቱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ምዝገባ እና ሰነድ የማግኘት መብት፣ የጸጥታና ደኅንነት፣ የመንቀሳቀስ መብት፣ የሰብአዊ ድጋፍ የማግኘት መብት እንዲሁም ለሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኛ ተፈናቃዮች የሚደረግ ልዩ ድጋፍ እና በአጠቃላይ የዘላቂ መፍትሔዎች አተገባበር ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና እገዛን አስመልክቶ የተደረገው የአፍሪካ ሕብረት ስምምነት (ካምፓላ ስምምነት) ካጸደቁ 33 የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ስትሆን፣ ስምምነቱ ብሔራዊ ሕግ እና ተቋማዊ መዋቅር እንዲኖር ማስቻልን ዋነኛ የመንግሥት ኃላፊነት በማድረግ በደነገገው መሠረት ስምምነቱን ማስፈጸሚያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች የተደረጉ መሆኑን በሪፖርቱ እንደ አንድ ቁልፍ እመርታ ተካቷል።
በተጨማሪም በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት በሕወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል በተደረገው የሰላም ስምምነት መሠረት መቆሙን ተከትሎ በጦርነቱ ተፈናቅለው የነበሩ በርካታ ሰዎች ወደቀያቸው የተመለሱ መሆኑ በሪፖርቱ በመልካም እርምጃነት ተጠቅሷል። ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ክልሎች በተቀባይ ማኅበረሰብ፣ በመንግሥት እንዲሁም መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት የሰብአዊ ድጋፍ በተለይ የምግብ ድጋፍ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት፤ በተወሰኑ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች በየጊዜው ወቅታዊ የሚደረግ የተሰባጠረ የተፈናቃዮች የመረጃ አያያዝ ሥርዓት መኖሩ፤ የኮሚሽኑን የክትትል ግኝቶችና ምክረ ሐሳብ ተቀብለው የተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ለማሻሻል አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጡ የወረዳ፣ የክልል እንዲሁም የፌዴራል አመራርና ተቋማት መኖራቸው በሪፖርቱ በቁልፍ እመርታነት ተጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የካምፓላ ስምምነትን ለማስፈጸም የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ጸድቆ ሥራ ላይ ባለመዋሉ እና የተፈናቃዮችን ጉዳይ በባለቤትነት የሚያስተዳድር ተቋማዊ አደረጃጀት አለመኖሩ፤ መፈናቀልን ለመከላከል፣ ለተፈናቃዮች የሚደረጉ የጥበቃ እና ድጋፍ ሥራዎች እንዲሁም የዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ ሂደቶች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች አሁንም አሳሳቢነታቸው መቀጠላቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል። በተመሳሳይ የተፈናቃዮች ምዝገባ እና ሰነድ የማግኘት ሥርዓቱ ላይ ያለው ክፍተት መቀጠሉ፤ ለተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ በአግባቡ እንዳይከናወን አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩ በተጨማሪ ተፈናቃዮች ሌሎች የመንቀሳቀስ እና የማኅበራዊ አገልግሎት የማግኘት መብቶቻቸውን ለመጠቀም እንዳይችሉ እንቅፋት መፍጠሩ በአሳሳቢነት ተጠቅሷል።
ወቅቱን የጠበቀ፣ በቂ፣ ያልተቆራረጠ እንዲሁም ልዩ ፍላጎቶች ያሏቸውን ተፈናቃዮች መሠረት ያደረገ የሰብአዊ ድጋፍ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች አቅርቦት አለመኖሩ፤ ተፈናቃዮች ይህንን ክፍተት ለመሙላት እና ያሉበትን ሁኔታ ለመቋቋም አሉታዊ ውጤት ያላቸው አማራጮችን (Negative Coping Mechanisms) እንዲወስዱ መገደዳቸው፤ በተጣበበ የመጠለያ ሸራ ውስጥ ከአንድ በላይ ቤተሰቦች ወይም የሥጋ ዝምድና የሌላቸው ሰዎች በጋራ እንዲኖሩ መደረጉ፣ ይህም ሴቶችን እና ሕፃናትን ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ እንዳደረገ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነው መፈናቀል ኃይል በተቀላቀለባቸው ግጭቶች ምክንያት የሚከሰት በመሆኑ መፈናቀልን ለመከላከል እና በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት፤ በዋናነት ግጭቶችን ወቅታዊ በሆነ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አክለውም “የተፈናቃዮችን ሰብአዊ መብቶች በአግባቡ ለማክበር፣ ለማስከበር እና ለማሟላት መንግሥት የካምፓላ ስምምነት ማስፈጸሚያ ብሔራዊ ረቂቅ ሕግ በተፋጠነ ሁኔታ ማጽደቅና ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም ለተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ የሚሰጥና የሚያስተባብር በግልጽ ሥልጣን የተሰጠው ተቋም በመሰየም ወይም በማቋቋም ወደ ሥራ ማስገባት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው” ብለዋል። “መፈናቀልን መከላከል፣ ለተፈናቃዮች ምላሽ መስጠት እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔን ማመቻቸት በዋናነት የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ ድርጅቶች እና የልማት አጋሮች መንግሥትን በዚህ ረገድ ሊያግዙ ይገባል” ሲሉ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡