የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከ2014 ዓ.ም. እስከ 2015 ዓ.ም. የበጀት ዓመት ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የመጀመሪያውን የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ የተመለከተ ባለ 47 ገጽ የዘርፍ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ የመጀመሪያው የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ በተጨማሪነት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ የለያቸውን መልካም ጅማሮዎች፣ አሳሳቢ ሁኔታዎችን እና ምክረ ሐሳቦችን በዝርዝር አካቷል።
ኢሰመኮ በአፋር፣ በአማራ፣ በጋምቤላ እና በሶማሌ ክልሎች በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ እና መቀበያ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የከተማ ስደተኞችን ጨምሮ ከ650 ሺህ በላይ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን የሚያስጠልሉ 17 መጠለያዎችን፣ ሳይቶችን እና መቀበያ ጣቢያዎችን በመድረስ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ ክትትሎች እና ምርመራዎችን በማካሄድ ሪፖርቱን አጠናቅሯል። ሪፖርቱ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ምዝገባ እና ሰነድ የማግኘት መብት፣ የጸጥታና ደኅንነት፣ ፍትሕ የማግኘት መብት፣ የመንቀሳቀስ መብት፣ የሰብአዊ ድጋፍ የማግኘት መብት እንዲሁም ለሕፃናት፣ ለሴቶች፣ ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኛ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚደረግ ልዩ ድጋፍ እና በአጠቃላይ የዘላቂ መፍትሔዎች አተገባበር ላይ ትኩረት የሚያደርግ ነው።
ኢትዮጵያ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መብቶችን በተመለከተ በዓለም እና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን ያጸደቀች መሆኑ፤ በሀገር ውስጥ የስደተኞችን መብቶች በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ እና ለስደተኞች ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ የሚያስችል አጠቃላይ የሕግ ማዕቀፍ መኖሩ በሪፖርቱ እንደ አንድ ቁልፍ እመርታ ተካቷል።
በተጨማሪ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥበቃ እና ድጋፍ ለመስጠት እንዲሁም ለማስተባበር የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ተቋም መኖሩ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና ሀገር በቀል የተራድዖ ድርጅቶች መንግሥት ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚያደርገው ጥበቃ እና ድጋፍ የተሟላ እንዲሆን ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑ በመልካም እመርታነት የሚጠቀሱ ናቸው። በተመሳሳይ መንግሥት በተለይ በሱዳን እንዲሁም በሱማሊያ ላስአኖድ የተቀሰቀሱትን ግጭቶች ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞችን ተቀብሎ እያስተናገደ መሆኑ፤ ከአፋር ክልል በራሃሌ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ወደ ተለያዩ ስፍራዎች ሸሽተው የነበሩ ስደተኞች ወደ መጠለያቸው እንዲመለሱ መደረጉ፤ የትምህርትና የጤና አገልግሎት አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች ለስደተኞች የሚደረጉ መሆኑ በሪፖርቱ የተካተቱ ዋና ዋና ቁልፍ እመርታዎች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል የስደተኞች ምዝገባ እና ሰነድ የማግኘት ሥርዓት ላይ ክፍተት መኖሩ፤ ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚደረገው ድጋፍ በአግባቡ እንዳይከናወን አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩ ባሻገር ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሌሎች የመንቀሳቀስ እና የማኅበራዊ አገልግሎት የማግኘት መብቶቻቸውን ለመጠቀም እንዳይችሉ ተግዳሮት መሆኑ በአሳሳቢነት ተጠቅሷል። መንግሥት የስደተኞችን መታወቂያ ወደ ዲጂታል ለመቀየርና ለማዘመን እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ሲሆን፤ ሥራው ተጠናክሮ የስደተኞች የመረጃ አያያዝን፣ የመታወቂያ አሰጣጥን እና የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በማሻሻል እና በማዘመን በሥርዓቱ ላይ ያለውን ክፍተት መቅረፍ እንደሚገባ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ወቅቱን የጠበቀ፣ በቂ፣ ያልተቆራረጠ እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ያሏቸውን የማኅበረሰቡ ክፍሎች መሠረት ያደረገ የሰብአዊ ድጋፍ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች አቅርቦት አለመኖሩ፤ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚደረገው ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ፤ ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚደረግ የምግብ ድጋፍ አቅርቦት ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ በቆየባቸው ወራት አቅርቦቱ እስከቀጠለበት ጊዜ ድረስ ስደተኞች ለከፋ የሰብአዊ ቀውስ መዳረጋቸውን፤ አብዛኛው የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የመድኃኒት፣ የሕክምና መሣሪያዎች፣ የላብራቶሪ እና የመታከሚያ አልጋዎች እጥረት መኖሩ ስደተኞች የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረጉ በሪፖርቱ በአሳሳቢነት ተጠቅሷል፡፡
የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ተገቢውን ጥበቃ እና ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት፤ በስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት በተወሰነ መልኩ የተጀመረው የስደተኞች መታወቂያ እድሳት አገልግሎት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው “ይሁንና ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ለሦስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ምዝገባ አገልግሎቱን በአፋጣኝ እንዲቀጥል ማስቻል ነው ብለዋል”። አክለውም “የስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ሰብአዊ መብቶች በአግባቡ ለማክበር፣ ለማስከበር እና ለማሟላት መንግሥት ዓለም አቀፍ እና ብሔራዊ ሕጎችን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ፤ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዲከበር አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎችን ጸጥታ እና ደኅንነት ማረጋገጥ፣ እንዲሁም የተሟላ የሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ እና ዘላቂነት ያለው መፍትሔ መስጠት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው” ብለዋል። “ለስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚደረግ ጥበቃ፣ ድጋፍ እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔን ማመቻቸት በዋናነት የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም የተ.መ.ድ. የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ ድርጅቶች እና የልማት አጋሮች መንግሥትን በዚህ ረገድ እንዲያግዙ” ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡