የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሃዲያ ዞን በሻሸጎ፣ ሶሮና ምዕራብ ሶሮ ወረዳዎች በሴቶች ላይ በሚፈጸም ግርዛት ዙሪያ ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ከመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር ታኅሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በሆሳዕና ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የፌዴራል ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና ፖሊስ ኮሚሽን፣ የዞን እና የወረዳዎች ጤና ቢሮ፣ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ እና የፖሊስ ቢሮ ተወካዮች፣ የወረዳ እና የቀበሌ አስተዳዳሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ተጎጂዎች ተሳትፈዋል፡፡
በውይይት መድረኩ በሃዲያ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል የተለዩ ግኝቶች በተለይም በዞኑ የሚፈጸመው የሴት ልጅ ግርዛት ስርጭት፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ በእናቶችና አረጋውያን ላይ የመፈጸሙ አሳሳቢነት እና በሴቶች ሰብአዊ መብቶች ላይ ስላለው ተጽዕኖ ለተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡ ተጎጂዎች ለሚያጋጥማቸው የጤና እክል እየተሰጠ ያለው ድጋፍና ክትትል አጥጋቢ አለመሆን ሴቶች ከዘመናዊ ሕክምና ይልቅ ወደ ጎጂ ልማዳዊ አማራጮች እንዲያዘነብሉ ምክንያት እንደሆናቸው ተብራርቷል፡፡ በተመሳሳይ በሻሸጎ ወረዳ በማኅበረሰቡ ዘንድ ‘ጨበላ’ በመባል የሚታወቅ የተደጋጋሚ ግርዛት ጎጂ ልማድ በአካባቢው በበጋ ወራት በሁሉም ዕድሜ ክልል በሚገኙ ሴቶች ላይ በስፋት እንደሚፈጸም እንዲሁም ሴቶችና ሴት ሕፃናት መራቢያ አካላቸው አካባቢ ለሚያጋጥማቸው የጤና እክል እንደመፍትሔ የሚወሰድ መሆኑ ተገልጿል። በዚህ ጎጂ ልማድ የሚያልፉ ሴቶች ከጤና እክል ጀምሮ እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት የሚደርስባቸው መሆኑ በክትትሉ ከተለዩ ግኝቶቹ መካከል ተጠቅሷል።
በክትትሉ የሴትን ልጅ ግርዛት በዞኑ ለማስቆም በተግዳሮትነት ከተነሱት መካከል ድርጊቱ በድብቅ መፈጸሙ፣ ማኅበረሰቡ ሴትን ልጅ የሚገርዙ ግለሰቦችን መደበቁ፣ በአካባቢው በቂና ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት አለመኖሩ፣ የሚመለከታቸው የፍትሕና የአስፈጻሚ አካላት ተቀናጅቶ አለመሥራት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ሲቪል ማኅበራት ትኩረት ማነስ ይገኙበታል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በዞኑ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ተጀምረው የነበሩ የመከላከልና የንቅናቄ ሥራዎች መቀነስ አሁን ለሚስተዋለው የሴት ልጅ ግርዛት ስርጭት መጨመር አስተዋጽዖ ማድረጉን እና ኢሰመኮ ያከናወነው ክትትል የጉዳዩን አሳሳቢነት ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም እንደየኃላፊነታቸው በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች እየተፈጸሙ ያሉ የሴት ልጅ ግርዛትና ተደጋጋሚ ግርዛትን ለማስቆም ሕግ ማስከበርና የታቀዱ ግርዛቶችን ማስቆምን ጨምሮ የወሰዷቸውን እርምጃዎች እንዲሁም ወደፊት ለመሥራት ያቀዷቸውን ሥራዎች አቅርበዋል፡፡
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም በሀገር አቀፍ ደረጃ እየሠራ ያለውን ሥራ እንዲሁም ይህን ጉዳይ በሚመለከት አፋጣኝ እርምጃዎችን እንደሚወስድ በተለይም ከዞን እስከ ወረዳ በተቋቋሙ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መዋቅሮች ምላሽ እንደሚሰጥ አብራርቷል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ “በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት የሴቶችን ክብር የሚነካ፤ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት የሚፈጥር እንዲሁም ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የመሳተፍ ዐቅማቸውን የሚገድብ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም ባለድርሻ አካላት እንደየድርሻቸው ማኅበረሰቡን በማስተማር፣ የወንጀል ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ ለተጎጂዎች አስፈላጊውን የጤና፣ የማኅበረ ሥነ-ልቦና እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ እና በቅንጅት በመሥራት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡