የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በፌዴራል ሕገ-መንግሥቱ መሠረት ነጻ ፌዴራላዊ መንግሥት አካል ሆኖ የተቋቋመና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነ ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ የሚሠራ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ነው። (የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55/14 እና አዋጅ ቁጥር 210/1992 በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) የኮሚሽኑን አቋም በሚደነግገው በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 8 መሠረት፣ ኢሰመኮ የልዩ ልዩ ሰብአዊ መብቶች ዘርፍ ጉዳዮችን የሚመሩ ኮሚሽነሮች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ጉዳዮች ዘርፍ ነው፡፡ ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2016 ዓ.ም. ድረስ ይህ ዘርፍ በኮሚሽነር መስከረም ገስጥ ተጫኔ ሲመራ የነበረ ሲሆን፣ ኮሚሽነር መስከረም በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን ከለቀቁበት ጊዜ ጀምሮ ምትክ ኮሚሽነር እስከሚሾም ድረስ ላለፉት ስድስት ወራት የሴቶች እና ሕፃናት መብቶችን ዘርፍ ሥራ ደርበው ሲሠሩ የቆዩት፤ በተቋሙ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ ናቸው።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሚያቋቁሙና ተቋሙን የሚመሩ አባላትን እንዲመርጥና እንዲሰይም በተደነገገው መሠረት፣ ምክር ቤቱ በሚያዝያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር ለመሰየም የምልመላ መስፈርትና የውስጥ አሠራር መምሪያ፣ እንዲሁም ዕጩዎች ተወዳድረው ለምክር ቤቱ እንዲቀርቡ በተዘጋጁ መስፈርቶች ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን ገልጾ፣ የእጩዎች ጥቆማ ጊዜ ገደብ ከሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደሚሆን ይፋ አድርጓል።
በዚሁ መሠረት እና በኢሰመኮ ማቋቋምያ አዋጅ አንቀጽ 11(3) መሠረት እጩዎች የሚከተሉትን መስፈርቶች ሊያሟሉ ይገባል፦
- ጾታ፡- ሴት፣ ዕድሜ፡- ከ35 ዓመት በላይ፣ ዜግነት፡- ኢትዮጵያዊት
- የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪነት ልምድ
- በሕግ ወይም አግባብ ባለው ሌላ ሙያ የሰለጠነች፣ በልምድ ሰፊ ዕውቀት ያካበተች
- በታታሪነቷ፣ በታማኝነቷ እና በሥነ ምግባሯ መልካም ስም ያተረፈች
- ከደንብ መተላለፍ ውጪ ባለ በሌላ ወንጀል ጥፋት ተከሳ ያልተፈረደባት
- የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆነች እንዲሁም
- የሚሰጠውን ከፍተኛ ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስችል ከፍተኛ የአመራር ብቃት ያላት እና ሥራውን ለመሥራት የሚያስችል ጤንነት ያላት
በተጨማሪም ለአካል ጉዳተኛ ባለሙያዎች ኢሰመኮ የተመጣጣኝ ማመቻቸት የሚያዘጋጅ በመሆኑ ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የሚያሟሉ አካል ጉዳተኛ ባለሙያዎች እንዲያመለክቱ ወይም እንዲጠቆሙ ይበረታታል።
ስለሆነም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፌስቡክ ገጽ ላይ በተገለጸው መሠረት፣ እስከ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟሉ ባለሙያዎችን ከዚህ በታች በተዘረዘሩት መንገዶች በመጠቆም ወይም በማመልከት ሁሉም ባለድርሻዎች እንዲሳተፉ ኢሰመኮ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።
ይህንን የተያያዘውን ቅጽ በመሙላት https://shorturl.at/deruM
- በኢሜል አድራሻ፦ HumanrightNC@hopr.gov.et
- ቅጹን ሞልቶ ወደ ምክር ቤቱ በአካል በመቅረብ፣ ወይም
- በቴሌግራምና በዋትስ-አፕ ስልክ ቁጥር፡- 09-69-27-43-43
- በምክር ቤቱ መዝገብ ቤት በኩል ለኢሰመኮ የሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር እጩ አቅራቢ ኮሚቴ በሚል አድራሻ በመላክ በፖስታ፡ መልዕክት ሳጥን ቁጥር 80001
- በአካል ማቅረብ ለሚፈልጉ፦ አራት ኪሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የእንግዳ መቀበያ ቢሮ በተዘጋጀው ዝግ ሳጥን ውስጥ የጥቆማ ወረቀታቸውን ማስገባት ይችላሉ።
ከእጩ አቅራቢ የበለጠ መረጃ ለማግኘት፡- ስልክ +251 111 13 49 99 | +251 969 27 43 43