የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኞች መብቶች አተገባበር የክትትል ሪፖርት ላይ ያቀረባቸውን ምክረ ሐሳቦች ተፈጻሚነት አስመልክቶ ከመስከረም 6 እስከ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. የትግበራ ክትትል በማከናወን ያዘጋጀውን ባለ 12 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡
ኢሰመኮ በዚህ የትግበራ ክትትል በዋናው የክትትል ሪፖርት የተጠቆሙ ምክረ ሐሳቦች ያሉበትን የአተገባበር ሁኔታ ለመገምገም እንዲሁም ከክትትሉ በኋላ የተፈጠሩ ክፍተቶች ለመለየት ገላጭ የክትትል ዘዴን (qualitative follow-up methodology) ተጠቅሟል። በአዲስ አበባ፣ በሃዋሳ እና ጅማ ከተሞች ከሚገኙ የኤጀንሲ ሠራተኞች፣ የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች፣ ተጠቃሚ ድርጅቶች፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት እና ሌሎች ባላድርሻ አካላት በአጠቃላይ ከ57 ተሳታፊዎች ጋር በተደረጉ ቃለ መጠይቆች፣ በአካል ምልከታ እና በሰነዶች ትንተና መረጃዎች እና ማስረጃዎችን አሰባስቧል።
ኢሰመኮ በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ዋናው የክትትል ሪፖርት በግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች መብቶች በተለይም ምቹ የሥራ ሁኔታዎችን የማግኘት፣ የእኩልነትና ከአድልዎ ነጻ የመሆን፣ የሥራ ዋስትና የማግኘት፣ ማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት፣ የመደራጀት፣ ቅሬታ የማሰማት እንዲሁም ፍትሕ የማግኘት መብቶች አተገባበር ላይ ከፍተኛ ክፍተቶች የሚስተዋሉ መሆኑን አመላክቷል። ለእነዚህም ክፍተቶች አስተዋጽዖ ያደረጉትን ምክንያቶች የለየ ሲሆን፣ በተለይም የኤጀንሲ ሠራተኞችን በተመለከተ ተፈጻሚነት ያለው ዋና የሕግ ማዕቀፍ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በግል ሥራና እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በኩል ቀጥሮ ማሠራትን ዕውቅና ቢሰጥም የሁለትዮሽ የሥራ ግንኙነትን ብቻ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተቀረጸ ነው። በመሆኑም የሦስትዮሽ የሥራ ግንኙነትን ሙሉ በሙሉ በሚሸፍን እና በዚህ ዐይነት የሥራ ግንኙነት ውስጥ የሚሳተፉትን አካላት ኃላፊነቶች እና የመንግሥትን ግዴታዎች በአግባቡ በሚደነግግ መልኩ እንዲሻሻል ወይም ለዚሁ ዓላማ ራሱን የቻለ አዲስ ሕግ እንዲወጣ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል። ኢሰመኮ በዋናው የክትትል ሪፖርት ከሕግ ማዕቀፍ ጋር ከተያያዙ ምክረ ሐሳቦች ባሻገር ሌሎች ከትግበራ፣ ከቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም ከግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ጋር የተገናኙ ዝርዝር የመፍትሔ ሐሳቦችንም ሰጥቷል።
የትግበራ ክትትል ሪፖርቱ በዋናው የክትትል ሪፖርት የተሰጡትን ምክረ ሐሳቦች ተከትሎ በመንግሥት የቁጥጥር እና ክትትል አካላት እንዲሁም በአንዳንድ ተጠቃሚ ድርጅቶች እና የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በኩል የሠራተኞችን መብቶች ሊያስጠብቁ የሚችሉ የተወሰኑ አወንታዊ እርምጃዎች ቢወሰዱም አብዛኛዎቹ ምክረ ሐሳቦች እየተተገበሩ አለመሆናቸውን ያመለክታል። በተለይም በዋናው የክትትል ሪፖርት በተመለከተው መሠረት የሕግ ማሻሻያ እርምጃዎች አለመወሰዳቸው፣ የኤጀንሲ ሠራተኞችን መብቶች፣ ደኅንነት እና ጥቅማጥቅም ለማስጠበቅ ጠቀሜታ ያለው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መመሪያ ቁጥር 45/2013 ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አለመደረጉ፣ እንዲሁም የኤጀንሲ ሠራተኞች የሥራ ዋስትና ማጣት ሪፖርቱ ካመላከታቸው ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው። ለምሳሌ ከ3000 በላይ የሚሆኑ የአንድ ኤጀንሲ ሠራተኞች የሥራ መቋረጥ ሥጋት ያለባቸው መሆኑ ተጠቃሽ ነው።
ኢሰመኮ የትግበራ ክትትሉን ግኝቶች መሠረት በማድረግ መንግሥት፣ ተጠቃሚ ድርጅቶች እና ኤጀንሲዎች በዋናው የክትትል ሪፖርት የተካተቱትን ሁሉንም ምክረ ሐሳቦች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲያደርጉ፤ በተለይም የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁ የሦስትዮሽ የሥራ ግንኙነቶችን ሙሉ በሙሉ በሚሸፍን እና በዚህ ዐይነት የሥራ ግንኙነት ውስጥ የሚሳተፉትን አካላት ኃላፊነቶች እና የመንግሥትን ግዴታዎች በግልጽ በሚያስቀምጥ መልኩ እንዲሻሻል ወይም ለዘርፉ ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ እንዲፈጠር ምክረ ሐሳብ አቅርቧል። ይህ እርምጃ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኤጀንሲ ሠራተኞችን የሥራ ውል በሚሰማሩበት ሥራ ቀጣይነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ እንዲያወጣ መክሯል።
የኢሰመኮ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ብራይትማን ገብረ ሚካኤል ኢሰመኮ የምርመራና ክትትል ሥራዎቹን ተመርኩዞ የሚያቀርባቸውን ምክረ ሐሳቦች በአግባቡ መተግበር በኢትዮጵያ የተሻለ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለመፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰው፣ “የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኞችን መብት አተገባበር ለማሻሻል መንግሥትን፣ ተጠቃሚ ድርጅቶችን እና ኤጀንሲዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር መሥራት ይገባቸዋል። በተለይም ከሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ የተነሱት ምክረ ሐሳቦች ፈጣን ምላሽ የሚፈልጉ ናቸው” ብለዋል።