የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ 20 ፖሊስ ጣቢያዎች እና 6 ማረሚያ ቤቶች ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች ክትትል በለያቸው ግኝቶችና ባቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች ላይ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በጅማ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይት መድረኩ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊዎችን ጨምሮ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የጸጥታና አስተዳደር ቢሮዎች እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፍትሕ ቢሮ እና የዞን ፖሊስ መምሪያዎችና ማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
በውይይቱ የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በፖሊስ ጣቢያዎች በወንጀል ተጠርጥረው የሚያዙ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የሚስተናገዱ መሆኑ፣ የተጠርጣሪዎች መረጃ በባሕር መዝገብ መያዙ፣ ስልታዊ የሆነ አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት አለመኖሩ፣ የተጠርጣሪዎች በቤተሰብ የመጎብኘት መብት መከበሩ እንዲሁም በተጠርጣሪዎች እና በሌሎች ሰዎች ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በፈጸሙ የፖሊስ አባላት ላይ የወንጀል ተጠያቂነት እና የአስተዳደር እርምጃዎች መወሰድ መጀመሩ በአበረታች ግኝትነት ተጠቅሰዋል፡፡ በሌላ በኩል ተጠርጣሪዎች ሲያዙ የተያዙበት ምክንያት የማይነገራቸው መሆኑ፣ አልፎ አልፎ ተጠርጣሪዎች በሚያዙበት ጊዜ እና ፖሊስ ጣቢያ ከገቡ በኋላ በፖሊስ አባላት ድብደባ የሚፈጸምባቸው መሆኑ፣ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የማይቀርቡ መሆናቸው እና በፍርድ ቤት እና በፖሊስ የተፈቀዱ የዋስትና መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የቀበሌ ማረጋገጫ ድጋፍ ደብዳቤ መጠየቁ አሳሳቢ ተብለው ከተለዩ ችግሮች መካከል ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ በተጠርጣሪዎች ማቆያ ስፍራዎች የንጽሕና ጉድለት መኖሩ፣ ለተጠርጣሪዎች የምግብ፣ የውሃ እና የሕክምና አገልግሎት የማይቀርብ ወይም የሚቀርበውም እጅግ ውስን በመሆኑ ከቤተሰብ ርቀው የሚታሰሩ ተጠርጣሪዎች ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸው ተገልጿል፡፡
በማረሚያ ቤቶች ላይ በተደረገው ክትትል የታራሚዎች መረጃ አያያዝ በባሕር መዝገብ እና በተወሰነ መልኩ በዲጂታል ቅጂ የተደራጀ መሆኑ፣ ታራሚዎችን በየፈርጁ ለይቶ ለመያዝ ጥረት መደረጉ፣ ከትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር የቀለም ትምህርት ማስተማር መቻሉ፣ በአብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶች በታራሚዎችና በማረሚያ ቤቶች አስተዳደር መካከል ያለው ግንኙነት መልካም መሆኑ እና ድብደባ እና ተያያዥ ኢሰብአዊ አያያዞች በከፍተኛ ደረጃ መቀነሳቸው፣ ማረሚያ ቤቶች በፍርድ ቤት ትእዛዝ ብቻ ታራሚዎችን መቀበላቸው፣ በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች በቂ ውሃ ለማቅረብ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸው እና በማረሚያ ቤቶች የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ውስንነቶችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የትብብር ግንኙነት መጀመራቸው በክትትሉ ከተለዩ አበረታች ጉዳዮች መካከል መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በሚገኙ ጤና ተቋማት በቂ የሰው ኃይል፣ የቁሳቁስ እና የመድኃኒት አቅርቦት አለመኖር፣ የታራሚዎች የቀን ፍጆታ በጀት አነስተኛ በመሆኑ የምግብ አቅርቦት ጥራት እና መጠን መቀነሱ፣ የማደሪያ ክፍሎች መጨናነቅ እና የንጽሕና መጓደል መሻሻል የሚያስፈልጋቸው ክፍተቶች መሆናቸው በቀረበው ማብራሪያ ተገልጿል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰብስቤ ሸዋኖ በፖሊስ ጣቢያዎች የሚስተዋሉትን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክፍተቶች ለማሻሻል ከኢሰመኮ በየጊዜው የሚቀርቡ ምክረ ሐሳቦችን መነሻ በማድረግ በርካታ የእርምት እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳዊት ጢሞትዮስ በበኩላቸው ኢሰመኮ በክትትል ሂደቱ ለይቶ ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ እንዲከበሩ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፉ መሆናቸውን ጠቅሰው ክፍተቶችን በሕግ፣ በአሠራር እንዲሁም ሀብትና ጊዜ የሚጠይቁትን በሂደት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጥምረት በመሥራት መፍትሔ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ይበቃል ግዛው ለሰብአዊ መብቶች መከበር የፖሊስ እና የማረሚያ ቤቶች ሚና እንዲሁም የባለድርሻ አካላት አጋርነት ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳለው አብራርተዋል፡፡ አክለውም ኢሰመኮ የሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች እና በውይይቱ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮችን በተቀመጠው የትግበራ መርኃ ግብር መሠረት በመፈጸም በተጠርጣሪዎች እና በታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ አወንታዊ ለውጥ ማሳየት ይገባል ብለዋል፡፡