የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ሦስተኛውን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ባለ 52 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ሦስተኛው የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተጨማሪነት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ የለያቸውን መልካም ጅማሮዎች፣ አሳሳቢ ሁኔታዎችን እና ምክረ ሐሳቦችን አካቷል።
ኢሰመኮ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በትግራይ ክልሎች በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋ መንስኤዎች የተፈናቀሉ ከ333 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን፣ ተመላሾችን እና ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ የተደረጉ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል እና ምርመራ በማካሄድ ሪፖርቱን አዘጋጅቷል። የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ምዝገባ እና ሰነድ የማግኘት፣ የጸጥታና ደኅንነት፣ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ የሰብአዊ ድጋፍ የማግኘት መብት፣ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ ተፈናቃዮች የሚደረግ የልዩ ድጋፍ ሁኔታ እንዲሁም የዘላቂ መፍትሔዎች አተገባበር ሪፖርቱ ትኩረት ያደረገባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ናቸው።
በሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መጽደቁ እና የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ መጀመሩ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ከመስጠት አንጻር የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በአዎንታዊ መልኩ በሪፖርቱ ተካቷል። በተለይ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው የእውነት ማውጣት ሂደቱ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ሌሎች ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ባካተተ መልኩ እንደሚተገበር እንደ አንድ የፖሊሲ አቅጣጫ ማስቀመጡ በመልካም ጅማሮ ተጠቅሷል።
በተጨማሪ በተራዘመ የመፈናቀል ሁኔታ (Protracted Displacement) ውስጥ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ ተለያዩ ቦታዎች በማስፈር እና ወደ ቀድሞ ቀያቸው በመመለስ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በመንግሥት የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸው፣ በብሔራዊ ደረጃ በተጀመረው የዲጂታል መታወቂያ መርኃ ግብር የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር መኖሩ፣ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው መጠለያ/ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያዎች እና ቦታዎች በተቀባይ ማኅበረሰብ፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት እንዲሁም በተራድዖ ድርጅቶች የሰብአዊ ድጋፍ የማቅረብ ጥረት መኖሩ፣ በተለይም ተቋርጦ የነበረው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (USAID) እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) የሰብአዊ ድጋፍ መልሶ እንዲጀመር መደረጉ በሪፖርቱ በቁልፍ እመርታነት ተጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ያጸደቀችው በአፍሪካ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃና ድጋፍን አስመልክቶ የተደረገ የአፍሪካ ኅብረት ስምምነት (የካምፓላ ስምምነት) የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተገቢው ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲደረግላቸው እና ሰብአዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው የሚያስገድድ ቢሆንም ስምምነቱን ለማስፈጸም የሚያስችል ብሔራዊ ሕግ ጸድቆ ተግባራዊ አለመደረጉ፤ በኃይል በማፈናቀል ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ የሚያደርግ እና ተጎጂዎችን ለመካስ የሚያስችል የተደራጀ የአሠራር ሥርዓት አለመኖሩ በአሳሳቢነት ተገልጿል። በተመሳሳይ ለተፈናቃዮች የሚቀርበው የምግብ እና ምግብ-ነክ ያልሆነ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠንም ሆነ በዐይነት እየቀነሰ መምጣቱ፤ ተከታታይነት ያለው የመጠለያ ድጋፍ ባለመኖሩ ተፈናቃዮች በተጣበበ ሁኔታ በትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ለተለያዩ አገልግሎት በተዘጋጁ ንጽሕና በጎደላቸው መጋዘኖች እና ጅምር ሕንፃዎች ውስጥ ለመኖር በመገደዳቸው እንዲሁም ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች፣ ለደኅንነት ሥጋት፣ በተለይም ሴቶች እና ሕፃናት ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸው በሪፖርቱ በአሳሳቢነት ተመላክቷል።
በመንግሥት እየተተገበሩ ያሉ የዘላቂ መፍትሔ አማራጮች የሰብአዊ መብቶች መርሖችን በተከተለ በተለይም የመፈናቀል ምክንያት የሆኑትን የደኅንነት ሥጋቶች ባስወገደ፤ የተፈናቃዮችን ፍላጎትና ፈቃድ ባገናዘበ፤ በዕቅድ እና በበጀት በተደገፈ፤ እንዲሁም የተፈናቃዮችን የቤት፣ የመሬት እና የንብረት መብቶችን ከግምት ባስገባ መልኩ አለመሆኑ በዚህ የሪፖርት ዘመንም ከተነሱ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ነው።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ መፈናቀል በአብዛኛው እየተከሰተ ያለው በግጭቶች ምክንያት በመሆኑ ግጭቶችን በአፋጣኝ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ መፍታት እና እንዳይባባሱ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ፤ መፈናቀልን ለመከላከል እና በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት ወሳኝ በመሆናቸው ትኩረት ሰጥቶ መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በተፈጥሮ አደጋም የሚከሰት መፈናቀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ በመምጣቱ ለቅድመ አደጋ መከላከል እና ለአደጋ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል። አክለውም የሰብአዊ መብቶች መርሖችን መሠረት ያደረገ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ እና የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን መብቶችና ተሳትፎ በሚያረጋገጥ ሁኔታ እንዲተገበሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።