የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር ክልል ረቂቅ የቤተሰብ ሕግ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል። ውይይቱ የሴቶችንና የሕፃናትን ሰብአዊ መብቶች ለማስጠበቅ መሻሻል ስለሚገባቸው የረቂቅ ሕጉ አንቀጾች እና በቀጣይ በጋራ ሊከናወኑ ስለሚገባቸው ተግባራት ለመወያየት ያለመ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ የአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የሴቶችና የማኀበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ፣ የክልሉ ምክር ቤት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የሸሪዓ ፍርድ ቤት፣ እና የፍትሕ ቢሮ ተወካዮች ተሳትፈዋል። በተጨማሪም የፍትሕ ሚኒስቴር እና የሴቶችና የማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የሰብአዊ መብቶች መርሖችን መሠረት ያደረገ የቤተሰብ ሕግ አስፈላጊነት እንዲሁም አበረታችና ሊሻሻሉ የሚገባቸው የረቂቅ ሕጉ ክፍሎችን ከሴቶችና ከሕፃናት መብቶች አንጻር የሚዳስሱ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሕጉ ከተረቀቀ ጊዜ አንስቶ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት እዚህ መድረሱን በመግለጽ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ተብለው በቀረቡ የረቂቅ ሕጉ ጉዳዮች በተለይም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ ከጋብቻ ውጪ ስለተወለዱ ልጆች፣ አባትነትን በፍርድ ቤት ማወቅ እና ጉዲፈቻ የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ዕይታ አጋርተዋል። በረቂቅ ሕጉ ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም ሊሻሻሉ በሚገባቸው የረቂቅ ሕጉ ክፍሎች ላይ ምክረ ሐሳቦችን ለማቅረብ እና አስፈላጊ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ከፌዴራል እና ከአፋር ክልል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጣ ግብረ-ኃይል (Task Force) ተዋቅሯል፡፡
የአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር ሙሳ አብዶ ረቂቅ ሕጉ ያሉበትን ክፍተቶች ለመሙላት፣ የማኅበረሰቡን ሃይማኖት እና ባህል ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ከሰብአዊ መብቶች ጋር የተጣጣመ እንዲሁም የብዙኃኑን ፍላጎት ሊያስከብር የሚችል የቤተሰብ ሕግ እንዲኖር በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ በበኩላቸው ሕጎች ሲወጡ ኢትዮጵያ የሴቶችን እና የሕፃናትን መብቶች ለማስከበር ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚገባ መሆኑን አብራርተዋል። አክለውም “ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ አሠራሮች ከሰብአዊ መብቶች ጋር የሚቃረኑ መሆን ስለሌለባቸው እነዚህ የሚወጡ ሕጎች በምንከተላቸው ሃይማኖቶችና ባህሎች ያሉትን መልካም ጎኖች የሚያጠናክሩ፣ መሻሻል ያለባቸውን ደግሞ የሚያሻሻሉ ሊሆኑ ይገባል” ብለዋል።