የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በኢሰመኮ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) አንቀጽ 19 በተደነገገው መሠረት በዋና ኮሚሽነር ሥልጣንና ኃላፊነት ሥር የሚወድቁ ሥራዎችን ከምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ተረክበዋል። በመርኃ ግብሩ ዶ/ር አብዲ ጅብሪል የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር እንዲሁም ርግበ ገብረሐዋሪያ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ተገኝተዋል።
በርክክብ መርኃ ግብሩ ኢሰመኮን ላለፉት ስድስት ወራት በተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነርነት ከመሩት ምክትል ዋና ኮሚሽነር የተከናወኑ፣ በመከናወን ላይ ያሉ እና ወደፊት ለማከናወን በዕቅድ ስለተያዙ ተግባራት ማብራሪያ ተሰጥቷል። በተመሳሳይ ኮሚሽነር አብዲ ጅብሪል እና ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ በየዘርፋቸው ማብራሪያ ሰተዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ የሰብአዊ መብቶች ሥራ የኢሰመኮ ሠራተኞችን እና የሁሉም ባለድርሻ አካላትን ትብብርና ቅንጅታዊ ሥራን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመው ዋና ኮሚሽነር የሰብአዊ መብቶችን በማስፋፋት፣ በማስጠበቅ እና በማስከበር ረገድ ለሚሠሩት ሥራዎች የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለማድረግ ከጎናቸው መሆናቸውን ገልጸዋል። በድጋሚ መልካም የሥራ ዘመንም ተመኝተውላቸዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ለተደረገላቸው ገለጻ እና ለመልካም ምኞት ምሥጋና አቅርበው ኢሰመኮ በአዋጅ የተጣለበትን ሰብአዊ መብቶችን የማስፋፋት፣ የመጠበቅና እንዲከበሩ የመወትወት ሥራዎች በከፍተኛ ኃላፊነት ለመፈጸም እንደሚተጉ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ ብርሃኑ አዴሎ ኢሰመኮን በዋና ኮሚሽነርነት እንዲመሩ የሾማቸው መሆኑ ይታወሳል።