የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለ5ኛ ጊዜ የሚያካሂደው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ምስለ ችሎት ውድድር የመጀመሪያው ምዕራፍ በክልል ደረጃ በተካሄደ ውድድር ተጠናቋል። ውድድሩ በ12 ክልሎች እና በ2 ከተማ አስተዳደሮች የተካሄደ ሲሆን ከ77 ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 154 ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል። እንዲሁም መምህራን፣ የትምህርት ቤቶች ዳይሬክተሮች፣ የትምህርት ቢሮዎች ተጠሪዎች፣ ተማሪዎች እና የተማሪዎች ወላጆች በታዳሚነት ተገኝተዋል።

የዚህ ዓመት የምስለ ችሎት ውድድር ለልማት ሲባል በግዳጅ ከመፈናቀል ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች (Development-based Forced Eviction and Human Rights) ላይ የሚያተኩር ነው። ውድድሩም ተማሪዎች ምናባዊ በሆነ ጉዳይ (Hypothetical Case) ላይ በመመርኮዝ የአመልካች እና የተጠሪ ወገንን ወክለው የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሚያደርጉበት ነው። የመደበኛ ፍርድ ቤት የክርክር ሥርዓትን የሚከተለው ይህ ውድድር በተወዳዳሪ ተማሪዎች እና በትምህርት ቤቶች ማኅበረሰብ ዘንድ የሰብአዊ መብቶች ዕውቀትንና ክህሎትን ለመገንባት ያለመ ነው፡፡

ተወዳዳሪ ተማሪዎቹ የውድድሩን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም በአመልካች እና ተጠሪ በኩል በመሆን ያዘጋጁትን የመከራከሪያ ጽሑፍ በማጠናቀቅ ለክልላዊ የቃል ክርክሩ የደረሱ ሲሆን፤ የቃል ክርክሩም ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በተመረጡ ከተሞች እና የከተማ አስተዳደሮች የሕግ እና ሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎችን በዳኝነት በማሳተፍ ተካሂዷል።

በዚህም መሠረት 14 ትምህርት ቤቶች ማለትም፦ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሳይ የሕዝብ ትምህርት ቤት፣ ከአፋር ሰመራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከአማራ የይሁኔ ወልዱ መታሰቢያ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማንቡክ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከማእከላዊ ኢትዮጵያ አበሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር አዲስ ሕይወት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከጋምቤላ የትንሹ ሜጢ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከሐረሪ ሐረር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከኦሮሚያ ቢሾፍቱ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ ከሲዳማ ወንዶ ገነት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከሶማሊ ኡመር ኢብኑል ኸጣብ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ዲላ ዶንቦስኮ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች አቡነ ተክለሐይማኖት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ከትግራይ ቀለሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አሸናፊ ሆነዋል።

ውድድሩን በበላይነት ካጠናቀቁት 14 ትምህርት ቤቶች መካከል በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚያደርጉት የጽሑፍ ክርክር የላቀ ነጥብ የሚያስመዘግቡ 8 ቡድኖች በግንቦት ወር በአዲስ አበባ ከተማ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ።

ውድድሩ በክልል ደረጃ በስኬት እንዲጠናቀቅ የተማሪዎች ወላጆች፣ የሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ትምህርት ቢሮዎች እና ባለድርሻ አካላት ጉልህ አስተዋጽዖ አድርገዋል።