የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚፈጸም የሴት ልጅ ግርዛት ላይ ያተኮረ ሕዝባዊ መሰማት ወይም ግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ በሰኔ 18 እና 19 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። በአቤቱታ መቀበያ መድረኩ ጥቃት የደረሰባቸው ተጎጂዎች፣ ምስክሮች፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

መድረኩ ከአፋር እና ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጡ 10 ተጎጂዎች ያቀረቡትን አቤቱታ እና ደርሶብናል ያሉትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ እንዲሁም የ2 ባለሙያዎችን እና የ3 ምስክሮችን ቃል አዳምጧል። በአፋር ክልል 3 የግርዛት ዓይነቶች የሚፈጸሙ መሆኑን ምስክሮች አብራርተዋል። እነዚህ የግርዛት ዓይነቶች የተፈጸሙባቸው ተጎጂዎች በመድረኩ ላይ ተገኝተው ግርዛቱ ትዳራቸው ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው፣ በግንኙነት እና በወር አበባ ጊዜ ሕመም እና ሥቃይ እንደሚሰማቸው እና የሥነ ልቦና ጉዳት እንዳስከተለባቸው አስረድተዋል። ሴትን ልጅ ማስገረዝ የሴቶች ወይም የእናቶች ኃላፊነት መሆኑን፣ እንዲሁም ግርዛቱ የሚፈጸመው በድብቅ መሆኑን በመድረኩ መስክረዋል። በግርዛት ምክንያት በቅድመ ወሊድና በወሊድ ወቅት ለረጅም ሰዓታት ለሚቆይ ምጥ እና ሕመም ከመጋለጣቸው የተነሳ በቀዶ ሕክምና ለመውለድ እንደተገደዱም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአፋር ክልል በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ አዋላጅ ሐኪም በበኩላቸው በሚሠሩበት ሆስፒታል በሰባት ቀናቸው ተገርዘው የመራቢያ አካላቸው የተጣበቀ ሕፃናት ለሕክምና እንደሚመጡ እና በከፍተኛ ደም መፍሰስ ምክንያት ለከፍተኛ ሕመም እና ሞት እንደሚዳረጉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በመድረኩ Gender and Adolescence: Global Evidence (GAGE) በመባል የሚታወቀው ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም በአፋር ክልል የሴት ልጅ ግርዛት ሁኔታ ላይ በአካሄደው ጥናት የሴት ልጅ ግርዛት እየተስፋፋ መሆኑን፣ ግርዛት በአፋር ጎሳ መሪዎች ዘንድ እንደ አንድ የባህል መገለጫ ተደርጎ የሚታይ በመሆኑ እናቶች ሴት ልጆቻቸውን ካላስገረዙ ማኅበራዊ መገለል እንደሚገጥማቸው እና የአፋር ወንዶችም ያልተገረዘች ሴት ለማግባት ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን በመድረኩ ይፋ አድርጓል።

ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጡ ተጎጂዎች ደግሞ በሕፃንነት ዕድሜያቸው ከተፈጸመባቸው ግርዛት በተጨማሪ አብዛኞቹ በአካባቢው “ጨበላ” ተብሎ በሚጠራው የግርዛት ዓይነት በማኅበረሰቡ ግፊት 3 እና 4 ተደጋጋሚ ግርዛት እንደተፈጸመባቸው፣ ግርዛቱ ባስከተለባቸው ሥቃይ እና የደም መፍሰስ ራሳቸውን ስተው እስከመውደቅ የሚደርስ ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ እንዲሁም በወር አበባ ወቅት ለሚከሰት ከባድ ሕመም እና ለተለያዩ የሥነ ልቦና ጫናዎች እንደተጋለጡ መስክረዋል።

በግልጽ የአቤቱታ መቀበያ መድረኩ የተሳተፉ የሀገር ሽማሌዎች እና የኃይማኖት አባቶች መድረኩ በድብቅ እና ሥልታዊ በሆነ መልኩ የሚፈጸመውን የሴት ልጅ ግርዛት ለመከላከል የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዳልተወጡ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል። ሁኔታው አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ ወደፊት የሴት ልጅ ግርዛት እንዲቀር በትጋት እንደሚሠሩ እና ኢሰመኮ በጉዳዩ ዙሪያ የሚያከናውነውን ሥራ ለማገዝም ቃል ገብተዋል።

የፌዴራል እና ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች እና ኃላፊዎች በበኩላቸው ተጎጂዎች የሰጧቸው ምስክርነቶች እና የጥናት ግኝቶች ነባራዊ ሁኔታውን የገለጡ እና ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል። የሕግ ንቃተ-ሕሊና ዝቅተኛ መሆን፣ ግርዛትን ከእምነትና ባህል ጋር ማስተሳሰር፣ የመግረዝ ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ አለማድረግ፣ የወንጀል ሕጉ ያስቀመጠው ቅጣት እጅግ አነስተኛ እና አስተማሪ አለመሆን፣ የፍትሕ አካላት ወደ ማኅበረሰቡ ወርደው አለመሥራታቸው እና መሰል ችግሮች የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢሰመኮ የሕግና ፖሊሲ ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ቃልኪዳን ደረጄ (በግራ)፣ የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ (መሃል) እና የኢሰመኮ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር መሐመድ አህመድ

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ የሕዝብ አቤቱታ መቀበያ መድረኩ በሴት ልጅ ግርዛት ምክንያት በተጎጂዎች ላይ የደረሰውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና የባለድርሻ አካላትን ምላሽ በመስማት መፍትሔ ማፈላለግ ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል። ኢሰመኮ የሕዝባዊ መሰማቱን ግኝቶች የያዘ ሪፖርት ይፋ እንደሚያደርግ፣ ለመንግሥት አካላት የተሰጡትን ምክረ-ሐሳቦች አፈጻጸም እንደሚከታተልም ገልጸዋል። በተጨማሪም ኢሰመኮ በሥልታዊ የምርመራ ሥራ የምስክሮች ጥበቃ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር በመሆኑ ምስክርነታቸውን ለሰጡ ግለሰቦች አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለመንግሥት የሕግ አስከባሪ አካላት አሳስበዋል።