የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለያዩ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ለሚሠሩ አካል ጉዳተኛ ሠራተኞች የሚቀርበውን ተመጣጣኝ ማመቻቸት አስመልክቶ ባከናወነው ጥናት የተለዩ ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ምክክር አካሂዷል። ጥናቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ትግራይ ክልሎች እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት በተመረጡ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ላይ የተካሄደ ነው።

በምክክሩ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከኦሮሚያ ክልል እና ከፌዴራል መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም ከኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን እና ከኦሮሚያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በምክክር መድረኩ ተመጣጣኝ ማመቻቸትን በተመለከተ በፌዴራል ተቋማት እና በክልሎች የተደነገጉ የሕግ ማዕቀፎች ያለባቸው ክፍተት፣ በየተቋማቱ በሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች እና የሰው ሃብት ባለሙያዎች ዘንድ የሚታይ የግንዛቤ እና የአመለካከት ክፍተት፣ ተመጣጣኝ ማመቻቸትን የተመለከተ የኦዲት ሥራ፣ መመሪያዎች እና ፎርማቶች አለመኖር፣ ዝቅተኛ የአካል ጉዳተኛ ሠራተኞች ተሳትፎና ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘት እና ሌሎች ኢሰመኮ ባከናወነው ጥናት የተለዩ ግኝቶች ቀርበው ከተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተደርጎባቸዋል።


የውይይቱ ተሳታፊዎችም የቀረቡት ግኝቶች በተጨባጭ የሚስተዋሉ እና በታችኛው የመንግሥት መዋቅሮች በአሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በመጥቀስ አገልግሎት ፈልገው ወደ መንግሥት ተቋማት የሚሄዱ አካል ጉዳተኞች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ጨምሮ ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ኢሰመኮ ሊሠራባቸው እና ጥናት ሊያደርግባቸው እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ የአካል ጉዳተኛ ሠራተኞችን ተመጣጣኝ ማመቻቸት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ መልካም ሥራዎችን በማስቀጠል ክፍተቶች ላይ በጋራ መሥራት ለአካል ጉዳተኛ ሠራተኞች የሥራ ላይ ውጤታማነት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። አክለውም የምክክሩ ተሳታፊዎች ወደየተቋሞቻቸው ሲመለሱ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበው፤ ኢሰመኮ ተከታታይነት ያለው የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸዋል።