የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2017 በጀት ዓመት በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥር በሚገኙ በተመረጡ 49 ፖሊስ ጣቢያዎች እና በ7 ማረሚያ ቤቶች በሕግ ጥበቃ ሥር የሚገኙ ሰዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ባደረገው ክትትል ግኝቶች ላይ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በሻሸመኔ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል። በምክክር መድረኩ ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት፣ ከክልሉ ምክር ቤት፣ ከጤና ቢሮ፣ ከፖሊስ እና ማረሚያ ኮሚሽን፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከወረዳና ዞን የተወከሉ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
በወይይት መድረኩ ላይ ኢሰመኮ ክትትል ባደረገባቸው የፖሊስ እና የማረሚያ ቤት ተቋማት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እና ጥበቃ ሁኔታ ላይ የታዩ መልካም እመርታዎች፣ መሻሻል የሚያስፈልጋቸው አሳሳቢ ጉዳዮች እና ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አተገባበርን ለመከታተል የሚያስችል የድርጊት መርኃ ግብር በኮሚሽኑ በኩል ተዘጋጅቶ ለተሳታፊዎች ቀርቧል።

ኢሰመኮ ክትትል ባደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች ከለያቸው አዎንታዊ መሻሻሎች መካከል በታራሚዎች ላይ የሚፈጸም ድብደባ እና ሌሎች ኢ-ሰብአዊ አያያዝና ቅጣት አለመኖሩ፣ ከቤተሰብ በኩል በሚቀርብ ምግብ ላይ ምንም ዓይነት ክልከላ አለመደረጉ፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ለታራሚዎች በተያዘው የቀለብ እና የሕክምና በጀት ላይ ማሻሻያ መደረጉ፣ በሕጉ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ተጠርጣሪዎችን ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ መቻሉ እና ቃላቸውን ያለምንም ጫናና ማስገደድ መስጠታቸው እንዲሁም በፍርድ ቤት የሚሠጡ ትዕዛዞች እና ውሳኔዎች በፖሊስ ኃላፊዎች መከበራቸው የሚጠቀሱ ናቸው።
በሌላ በኩል ኢሰመኮ በክትትሉ ከለያቸው አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች አልፎ አልፎ በተጠርጣሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙ፣ በፖሊስ ጣቢያዎች የፍራሽ እና የአልባሳት አቅርቦት እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት ያለመኖር፣ በአብዛኞቹ ፖሊስ ጣቢያዎች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ወጣት ተጠርጣሪዎች ለብቻ የተዘጋጀ ማቆያ/ማደሪያ ክፍል አለመኖር እንዲሁም ለተጠርጣሪዎች ይፋዊ የቅሬታ ማቅረቢያ አሠራር ሥርዓት አለመኖር የሚሉት ይገኙበታል። በሌላ በኩል በማረሚያ ቤቶች ዘመናዊ የታራሚዎች የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመኖር፣ በአብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች በፈርጅ ተለይተው ያለመያዛቸው፣ በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ለታራሚዎች የሚሆን በቂ የአልጋ፣ የፍራሽ እና የአልባሳት እንዲሁም የመጠጥና የመታጠቢያ ውሃ አቅርቦት ያለመኖር፣ የምግብ አቅርቦት መጠን ከታራሚዎች ቁጥር ጋር የተመጣጠነ ያለመሆን፣ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች እንዲሁም መዝናኛና ስፖርታዊ ማዘውተሪያ ቦታዎች ለሴት ታራሚዎች በበቂ መልኩ ተደራሽ ያለመሆን እና ልዩ ትኩረት ለሚያስፈልጋቸው ታራሚዎች የሚደረገው ድጋፍ ውስን መሆኑ ኢሰመኮ በማረሚያ ቤቶች ባደረገው ክትትል ከለያቸው ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱት ናቸው።

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በኢሰመኮ የቀረቡ የክትትል ግኝቶችን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበሉ እና በግኝቶቹ መሠረት በፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በታዩ ክፍተቶች ላይ የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ሪጅናል ዳይሬክተር ዮናስ ሙሉጌታ ኢሰመኮ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሂደት ውስጥ በሕገ-መንግሥቱ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ እና ኢትዮጵያ ፈርማ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ላይ በግልጽ የተቀመጡ በሕግ ጥበቃ ሥር የሚገኙ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አስታውሰዋል። አክለውም በክትትል ወቅት የተለዩ አዎንታዊ ጉዳዮችን ለማስቀጠል እንዲሁም አሳሳቢና መሻሻል የሚገባቸው ግኝቶችን ለማረም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እና በኃላፊነት ስሜት መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።