ኢሰመኮ በ2018 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጣቢያዎች ባከናወነው የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ምክክር አካሂዷል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ጥናት ኮሚሽነር በዳሳ ለሜሳን ጨምሮ የኢሰመኮ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከኦሮሚያ ፖሊስ፣ ከዞን፣ ከከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያዎች እንዲሁም ከዐቃቤ ሕግ ቢሮ፣ ከጤና ቢሮ እና ከትምህርት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመድረኩ ተገኝተዋል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ጥናት ኮሚሽነር በዳሳ ለሜሳ መድረኩን በንግግር የከፈቱ ሲሆን፤ ‘’መሠል ምክክሮች ኢሰመኮ እና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በክልሉ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ለማሻሻል፣ በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ለመተባበር፣ በጋራ ዓላማችን ላይ በመምከር ከዚህ በፊት የነበረውን ትብብር ይበለጥ ለማጠናከር እድል ይፈጥራሉ’’ ብለዋል።

ኮሚሽነር በዳሳ አክለውም በምክክሩ የቀረቡ የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ግኝቶች እና ምክረ ሐሳቦች ላይ በመወያየት አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ለማሻሻል የሚያግዝ ስምምነት ላይ መድረስ እና በተዘጋጀው የምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም የትግበራ እቅድ መሠረት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በምክክር መድረኩ ኢሰመኮ በ2018 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጣቢያዎች የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን አስመልክቶ ባካሄደው ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ለተሳታፊዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።

ተወያዮችም በየፖሊስ ጣቢያዎች የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ አስመልክተው የበኩላቸውን ሐሳቦች አቅርበዋል። እስካሁን ባለው ሂደት ተግዳሮት ሆነው የቀጠሉ ችግሮችን፣ እንዲሁም በፖሊስ ተቋማት ዐቅም ሊፈቱ የማይችሉ ጉዳዮች ላይ ኢሰመኮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውትወታ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። በክልሉ ያለው የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ይበልጥ እንዲሻሻል መሥራት እና ምክረ ሐሳቦችንም ተግባር ላይ ማዋል ከባለድርሻዎች እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

ኢሰመኮ ነጻነቱን አስጠብቆ በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ከለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይሠራል።