ኢሰመኮ በ2018 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ባከናወነው የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ምክክር አካሂዷል።

በምክክር መድረኩ የኢሰመኮ የትምህርት እና ምርምር ኮሚሽነር በዳሳ ለሜሳ፣ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር አሸነፈች አበበን ጨምሮ የኢሰመኮ የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዋጋሪ ጨላ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት፣ ከጤና ቢሮ፣ ከትምህርት ቢሮ፣ ከዞን፣ ከወረዳ፣ ከከተማ አስተዳደር ማረሚያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ምርምር ኮሚሽነር በዳሳ ለሜሳ ኢሰመኮ በታራሚዎች መብቶች ዙሪያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት፣ ያስገኛቸውን ስኬቶች እና የገጠሙትን ተግዳሮቶች አብራርተዋል።

አክለውም ኢሰመኮ እና የኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ባከናወኗቸው ተግባራት በታራሚዎች መብቶች አያያዝ ዙሪያ መሻሻሎች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

ኢሰመኮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በፈጠረው ትብብር እና በማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በኩል እየታየ ከመጣው መነሳሳት ጋር ተዳምሮ አሁንም በየማረሚያ ቤቶች የሚታዩ የታራሚዎች መብቶችን አያያዝ ጉድለቶችን ለመቅረፍ በትብብር መሥራት እንደሚገባ ኮሚሽነር በዳሳ አመላክተዋል።

በውይይቱ በ2018 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን አስመልክቶ ባካሄደው ክትትል የተለዩ ግኝቶች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ለተሳታፊዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።

ተወያዮችም በየማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን እና እየገጠሟቸው ያሉ ተግዳሮቶችን በስፋት አንስተዋል።

ውይይቱን የመሩት በኢሰመኮ የሴቶች እና ሕፃናት ኮሚሽነር አሸነፈች አበበ፣ ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንዲስተካከል በትብብር መሥራቱን እንደሚቀጥል ገልጸው ፣ ምክረ ሐሳቦቹን ተግባር ላይ ማዋል በእጅጉ ከባለድርሻዎች እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

በምክክሩ ማጠቃለያ ላይ ባለድርሻ አካላቱ ኢሰመኮ ያስቀመጣቸውን ምክረ ሐሳቦች በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ ለመተግበር የሚረዳ የድርጊት መርኃ ግብር አዘጋጅተዋል።