የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚደረጉ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች እንቅስቃሴዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ያደረገውን የክትትል ግኝቶች መሠረት በማድረግ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ወቅት በኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር መሀመድ አህመድ እንደገለጹት፤ ፖሊስ የስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሁኔታ በሚከታተልበትና በሚቆጣጠርበት ወቅት የሁሉንም ወገኖች ሰብአዊ መብት ባከበረ መልኩ መሆን ይኖርበታል።
አክለውም ፖሊስ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚረከባቸውን ተጎጂዎች ደህንነት እንዲጠብቅ፣ በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ ሕጋዊ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ፣ እንዲሁም ለሕጻናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በሚያዙበት ወቅት ጉዳያቸውን ለሚመለከተው ሕጋዊ አካል በማስረከብ ደህንነታቸውን በቅርበት መከታተል እንደሚገባ ተገልጿል።
ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ከመነሻው ለመግታት ከፌደራል እና ከሌሎች ክልል ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት፣ እንዲሁም ለምርመራ ባለሙያዎችና ለማህበረሰቡ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መብትና የግንዛቤ ማስረጽ ስልጠናዎችን መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ተመልክቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ደግፌ ደበላ፣ ችግሩ በግኝቱ በተመላከተው ልክ መሆኑን ገልፀው የተሰጡ ምክረሃሳቦችን በመተግበር ለማስተካከል እና ከምንጩ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተሳታፊዎችን ለይቶ ለህግ በማቅረብ ውጤት ለማምጣት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች (ነብረ ሙስ) የሚገኘውን የኢትዮ-ኬንያ ድንበር በተገቢው መንገድ እንዲቆጣጠርና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በሚስተዋልባቸው ቦታዎች ላይ ተጨማሪ የፌደራል ኬላዎችን በማቋቋም ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግ ጥሪ ቀርቧል።