የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ላይ ክትትል እና ድጋፍ ለማድረግ የተዘጋጀውን ረቂቅ መምሪያ ለመገምገም የሚያስችል የምክክር መድረክ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ጥቅምት 20 ቀን 2019 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። በመድረኩ የኢሰመኮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት፣ ከጠበቃ ቢሮ ተወካይ፣ ከዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤቶችና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ከሚሰጡ ሲቪል ማኅበራት የተውጣጡ ብሔራዊ የባለሙያዎች ኮሚቴ አባላት እና አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡

ኮሚሽኑ የፍትሕ ተደራሽነትን፣ የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ጥራትን እንዲሁም ሰብአዊ መብቶችን ያማከለ አገልግሎትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ተከታታይ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህ መድረክ ባለፉት ዓመታት በኮሚሽኑ ከተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በተጨማሪ፣ በወቅቱ እየተተገበረ ባለው የአምስት ዓመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲስፋፋና ጥራቱ እንዲጠበቅ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚስራተገልጿል።

በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶች ነባራዊ ሁኔታና መሠረታዊ ክፍተቶችን ለመለየት የተደረገ ጥናት እንዲሁም ኢሰመኮ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ለመከታተልና አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማትን ለመደገፍ የተዘጋጀው ረቂቅ መምሪያም ለተሳታፊዎች ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። በተጨማሪም ተሳታፊዎቹ የተዘጋጀው መምሪያ በሀገሪቱ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ የሚመራባቸውን መርሖዎች፣ የጥራት ደረጃዎችና ዝቅተኛ መስፈርቶችን በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑን ገልጸው፣ ከተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች በፍትሕ አስተዳደር ሂደት ውስጥ ሊያገኟቸው የሚገቡ አገልግሎቶችንና ድጋፎችን፤ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት እና ከሌሎች የሀገር ውስጥ ሕጎች ጋር በማጣቀስ በሰፊው ማካተቱ ለአገልግሎቱ ጥራት መሻሻል ትልቅ አስተዋፆ እንዳለው አስረድተዋል። በአንጻሩም በመምሪያው አቀራረብ፣ አደረጃጀት፣ ይዘቶች፣ የቃላት ወጥነት፣ ትርጉምና ሌሎች መመሪያውን ሊያዳብሩ የሚችሉ ገንቢ አስተያየቶች ከተሳታፊዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደር የኢትዮጵያ ተወካይ አቻምየለሽ ተፈሪ ፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሕፃናትን፣ ከእንክብካቤ ማእከላት የሚወጡ ወጣቶችና ሌሎች ለጥቃት ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መብቶች ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፣ ድርጅቱ የፍትሕ ተደራሽነትንና የሕፃናት ጥበቃ ሥርዓቶችን ለማጠናከር ለረጅም ጊዜ ሲሠራ መቆየቱን ያስረዱት ተወካይ ኃላፊዋ ረቂቅ መመሪያው ወቅታዊና ጠቃሚ መሣሪያ መሆኑን፣ በተለይም ለሕፃናት በሚሰጥ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ጥራትን፣ ወጥነትንና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንዳለበት አመልክተዋል። ውጤታማ ትግበራ እንዲኖር በመንግሥት ተቋማት፣ በኢሰመኮ እና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ኤስ ኦ ኤስ ሂደቱን ለመደገፍና የሕፃናትን የፍትሕ ተደራሽነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሻሻል ከሁሉም አጋሮች ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ሚዛኔ አባተ በበኩላቸው፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ጥራት፣ ወጥነትና የቁጥጥር ሥርዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ይህ ረቂቅ መምሪያም ወጥ ሀገር አቀፍ ሥርዓት ለመፍጠር፣ ዝቅተኛ የጥራት ደረጃዎችን ለማስቀመጥ እንዲሁም የውስጥ ክትትልንና የውጫዊ ቁጥጥርን ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል። አክለውም፣ ኮሚሽኑ በአዲሱ ስትራቴጂክ ዕቅዱ መሠረት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሰብአዊ መብቶችን ያማከለ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ለማስፋፋት ቁርጠኛ መሆኑን እንዲሁም መምሪያው ሲጸድቅ ኮሚሽኑ ሰፊ የስርጸት ሥራ እንደሚያከናውንና ተቋማት በአግባቡ እንዲተገብሩት አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።