የኢሰመኮ 3ኛ ዙር የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል የፎቶግራፎች እና የአጫጭር ፊልሞች ውድድር
Thank you for your interest in EHRC’s photography and short film competition. We would like to inform you that the application deadline has now passed. Our panel of judges thoroughly reviewed all submissions—the entries that have been shortlisted are listed here. We truly value your involvement and hope you will consider participating in our future competitions.
በ2016 ዓ.ም. በኅዳር 30 ቀን የሚውለው ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ቀን (December 10) የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ (Universal Declaration of Human Rights) 75ኛ ዓመት የሚታሰብበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል። ይህንንም በማስመልከት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ3ኛው ዙር የፊልም ፌስቲቫል ለዕይታ የሚቀርቡ የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ቪዲዮዎች ውድድሮች ያዘጋጀ ሲሆን፣ በውድድሩ ለመሳተፍ እና ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ዝርዝሩን ይመልከቱ
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄደው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በኢሰመኮ የ2015 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ በመሆን ከተለዩት መብቶች መካከል በሕይወት የመኖር መብት እና በቂ የሆነ መኖሪያ ቦታ/ቤት የማግኘት መብት ዙሪያ የሚያተኩር ይሆናል።
በሕይወት የመኖር መብት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ተብለው ከሚመደቡት መብቶች አንዱ ሲሆን፣ በሕይወት የመኖር መብት ስለሚያካትታቸው ጉዳዮች እና መብቱ የሚጣስባቸውን ሁኔታዎች በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ እዚህ ተያይዟል።
ማንኛውም ሰው በቂ መኖሪያ ቦታ/ቤት የማግኘት መብት ያለው ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የባህል መብቶች በመባል ከተለዩት መብቶች መካከል አንዱ ነው። መብቱ ሰዎች ከመኖሪያ ቦታቸው በግዳጅ ያለመፈናቀል እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የሚያጠቃልል ነው። ይህንን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያዎች እዚህ ተያይዘዋል።
የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን ለማሰብ የሚዘጋጀው የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ዓመታዊ ፊልም ፌስቲቫል በኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፣ በዝግጅቱ ከሚቀርቡ የተለያዩ የኪነጥበብ ሥራዎች መካከል የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን እና አጫጭር ፊልሞች ይገኙበታል። በዚህ ለሦስተኛ ጊዜ በሚዘጋጀው ፌስቲቫል ለዕይታ የሚቀርቡ ፎቶግራፎች እና አጫጭር ፊልሞች የተለያዩ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች በሚሳተፉበት ውድድር ከዝግጅቱ ቀን አስቀድ የሚመረጡ ናቸው።
የውድድር ጊዜው ከመስከረም 22 ቀን 2016 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. (እኩለ ለሊት ወይም በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከለሊቱ 6፡00 ሰዓት) ድረስ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች በእነዚህ ቀናት ውስጥ የፎቶግራፍ ወይም የአጭር ፊልም የጥበብ ሥራቸውን ከስር በተመለከተው አድራሻ፣ እዚህ ከተያያዘው ቅጽ ጋር መላክ ይችላሉ። ለውድድር የተላኩ የኪነጥበብ ሥራዎች በሁለት ዙር የሚገመገሙ ይሆናሉ።
- በመጀመሪያ ዙር፡ በኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሚውለው የኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ዝግጅት ለዕይታ የሚቀርቡ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ይመረጣሉ፣
- በሁለተኛ ዙር፡ በኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሚውለው ዝግጅት ለዕይታ እንዲቀርቡ ከተመረጡ ሥራዎች መካከል ከአንደኛ እስከ አስረኛ ደረጃ የወጣላቸው የጥበብ ሥራዎች እጩ የሚደረጉበት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ የሚመደቡ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ይመረጣሉ።
ከአንድ እስከ አስረኛ የወጡ የኪነጥበብ ሥራዎች ሙሉ ዝርዝር፣ እንዲሁም ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የተመደቡ የጥበብ ሥራዎች በይፋ በዝግጅቱ ላይ የሚገለጹ ሲሆን፣ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የተመደቡ የኪነጥበብ ሥራዎች እያንዳንዳቸው በመድረኩ ላይ በመቅረብ ይሸለማሉ።
ከአንድ እስከ አስረኛ ያልተመደቡ ሥራዎች ውጤት፣ የተሳትፎ እውቅና እንዲሁም ተጨማሪ ተያያዥ ማበረታቻዎች እንደ አግባብነቱ ለተሳታፊዎች ይገለጻል። ሆኖም ከኢሰመኮ እሴቶች እና መርሖች አንዱ ግልጽነት በመሆኑ በውድድሩ የተሳተፉ ግለሰቦች እና ተቋማት፣ እንዲሁም የቀረቡት የጥበብ ሥራዎች በሙሉ በኢሰመኮ ድረገጽ እና ማኅበራዊ ትስስር/ገጾች እንዲሁም በተለያዩ አመቺ መንገዶች የሚገለጹ ይሆናሉ።
ከመስከረም 22 ቀን 2016 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. (እኩለ ለሊት ወይም በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከለሊቱ 6፡00 ሰዓት) ድረስ ለውድድር የሚቀርበውን የኪነጥበብ ሥራ እንዲሁም የተሞላ እና የተፈረመበት የተሳትፎ ቅጽ ⬇️ (የውድድሩ አጠቃላይ መመሪያዎች እና ደንቦች ⬇️) በማያያዝ ከዚህ በታች በተመለከተው መልኩ መላክ ይችላሉ።
በኢሜል | filmfest@ehrc.org |
በሚከተሉት አድራሻዎች በሚገኙት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ቢሮዎች በአካል በመገኘት | |
የኪነጥበብ ሥራውን በሲዲ (CD) ወይም በፍላሽ ዲስክ (USB) በፖስታ የታሸገ | |
አዲስ አበባ | Sunshine Tower No. 5, Meskel Square, on Bole Road next to Hyatt Regency Hotel, Addis Ababa, Ethiopia ሰንሻይን ታወር ቁጥር 5፣ መስቀል አደባባይ አለፍ ብሎ ቦሌ መንገድ፣ ሀያት ሬጀንሲ ሆቴል አጠገብ፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ |
አሶሳ | Asosa | Woreda: 1- Across the Electric Corporation Branch Office | Tel: 0577750850/0577750055/0577750690 | Fax፡ 0577750720 ወረዳ 1 – መብራት ኃይል ቢሮ ፊት ለፊት፣ ወደ አሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል በሚያቋርጠው መንገድ፣ አሶሳ፣ ኢትዮጵያ |
ባሕር ዳር | Bahir Dar | Sub-city: Dagmawi Menelik | Kebele: Fenote | Aregawyan Building | P.O.Box: 160 | Tel: 0582262471 ዳግማዊ ምኒሊክ ክፍለ ከተማ ፍኖተ ቀበሌ፣ አረጋውያን ሕንጻ፣ ባሕር ዳር፣ ኢትዮጵያ |
ጋምቤላ | Across Mobil or next to Wibur Primary and Secondary School | Tel፡ 0475511376/0475512206 | P.O.Box፡ 107 ከሞቢል ፊት ለፊት/ከዊቡር የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጎን፣ ጋምቤላ፣ ኢትዮጵያ |
ሃዋሳ | Hawassa | Kebele: Menaheria- Millennium Street- on the road to Referral Hospital- Kidus Gabriel Bldg- 3rd Floor | Tel፡ 046220597 | Fax፡ 0462214368 | P.O.Box፡ 1627 መናኧሪያ – ሚለንየም መንገድ፣ ወደ ሪፈራል ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ፣ ቅዱስ ገብርኤል ሕንጻ፣ 3ኛ ፎቅ ሃዋሳ፣ ኢትዮጵያ |
ጅግጅጋ | Woreda: Jigjiga | Kebele: 10- Next to Kebele 10, Across Farah Megol School | Tel: 0252784214/0252781684 | Fax: 0257752496 | P.O.Box: 1007 ከቀበሌ 10 ጽሕፈት ቤት አጠገብ፣ ከፋራህ መጎል ትምህርት ቤት ፊት ለፊት፣ ጅግጅጋ፣ ኢትዮጵያ |
ጅማ | Jimma | Kebele: Awetu Mendara- Next to Jimma Zone High Court, on Abune Estifanos Building | Tel: 047 111 4043/0471116440 | Fax:- 0471117961 | P.O. Box:- 951 አወቱ መንደራ ቀበሌ፣ ጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አጠገብ አቡነ እስጢፋኖስ ሕንጻ ላይ፣ ጅማ፣ ኢትዮጵያ |
መቐለ | |
ሰመራ | በሰመራ ሎጊያ መንገድ፣ ወደ ሰመራ አየር መንገድ መገንጠያ በአድሱ ሕንጻ ላይ፣ ሰመራ፣ ኢትዮጵያ |
ከዚህ በላይ በተገለጹት የኢሰመኮ ቢሮዎች በአካል ተገኝተው የኪነጥበብ ሥራቸውን ለሚያቀርቡ ተሳታፊዎች የሚሞላው የተሳትፎ ቅጽ እና ፖስታ ይዘጋጃል።
በኢሰመኮ ድረገጽ አልያም በማኅበራዊ ሚድያ አድራሻዎች፣ አልያም በሌላ መንገድ የሚላኩ የኪነጥበብ ሥራዎች በውድድሩ አይካተቱም ወይም ከውድድሩ ውጪ ይሆናሉ። የተሟላ የተሳትፎ ቅጽ ያላያያዙ የኪነጥበብ ሥራዎች ወይም መረጃው በተሟላ መልኩ ያልቀረቡ የኪነጥበብ ሥራዎች በውድድሩ አይካተቱም ወይም ከውድድሩ ውጪ ይሆናሉ። በሲዲው ወይም በፍላሽ ዲስኩ ለውድድር ከሚቀርበው የኪነጥበብ ሥራ ውጪ ሌላ ምንም ዐይነት ይዘት ሊኖር አይገባም። ግልጽ ያልሆነ፣ የማይነበብ ወይም ሌሎች የቴክኒክ ግድፈቶች ያሉበት ፋይል አልያም ከሌሎች ይዘቶች ጋር የሚላኩ የኪነጥበብ ሥራዎች ከውድድር ውጪ የሚደረጉ ሲሆን፣ ይህም የኢሰመኮ ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል።
የዓመታዊው የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ዋነኛ ዓላማ የኪነጥበብን እና የሰብአዊ መብቶችን ትስስር ለማጠናከር እና በሁለቱ ዘርፎች መካከል ያለውን ጥምረት በተመለከተ ግንዛቤ ለማስፋፋት፣ እንዲሁም ኪነጥበብ “ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆኑባት ኢትዮጵያን ማየት” የሚለውን የኢሰመኮን ራዕይ መሳካት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለማስታወስ ነው። በተጨማሪም የፊልም ፌስቲቫሉ የኪነጥበብ ሥራዎችን በውድድር መልኩ ሲጋብዝ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን፣ የዚህ ዙር ዓላማ በርካታ ተወዳዳሪዎችን መጋበዝ እና እንዲሳተፉ ማበረታታት ነው።
በመሆኑም ለውድድሩ የሚቀርቡ የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልሞች ሥራዎች የቴክኒክ መስፈርቶች በዚህ የመጀመሪያ ዙር ቀለል ያሉ እና በአብዛኛው በተለይም ትኩረት ከተደረገባቸው በሕይወት የመኖር መብት እና በቂ የሆነ መኖሪያ ቦታ/ቤት የማግኘት መብት ጋር ባላቸው ተያያዥነት የሚገመገሙ ይሆናሉ።
ለዚህ ሂደት የጥበብ ሥራዎቹን የቴክኒክ መስፈርት የሚገመግም አንድ ባለሞያ፣ እንዲሁም በተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ዘርፎች (በሲቪል እና ፖለቲካ፣ በኢክኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንዲሁም በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞች፣ በአረጋውያን፣ እንዲሁም በስደተኞች፣ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና በፍልሰተኞች መብቶች) የሚሠሩ የኢሰመኮ እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሞያዎች እንዲሁም የኢሰመኮ የሚድያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራ ክፍል ባለሞያዎችን እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው የሥራ ክፍሎች ባለሞያዎች የተካተቱበት፣ ለመጀመሪያ ዙር ግምገማ የ5 ገምጋሚዎች ፓነል፣ ለሁለተኛ ዙር ግምገማ የ7 ገምጋሚዎች ፓነል ይቋቋማሉ። ገምጋሚዎች ከዚህ በታች በተዘረዘሩት የማወዳደሪያ መስፈርቶች ለኪነጥበብ ሥራዎቹ ነጥብ የሚሰጡ ሲሆን፣ ሁሉም ገምጋሚዎች የሰጡት ነጥቦች ድምር አማካይ የኪነጥበብ ሥራው የመጨረሻ ውጤት ይሆናል። ሁለት የኪነጥበብ ሥራዎች ተመሳሳይ ውጤት በሚያገኙበት ጊዜ በገምጋሚ ፓነሉ አብላጫ ድምጽ የሚወሰን ይሆናል። የገምጋሚ ፓነሉ ውሳኔ የመጨረሻ ነው።
- በሕይወት የመኖር መብትም ሆነ በቂ የሆነ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ዘርፍ፣ እንዲሁም በአጫጭር ፊልም ወይም በፎቶግራፍ ዘርፍ ለውድድር በሚቀርቡ ሥራዎች በሚከተሉት የማኅበረሰብ ክፍሎች (ልዩ ትኩረት የማኅበረሰብ ክፍሎች) ላይ ለሚያተኩሩ የኪነጥበብ ሥራዎች ለውድድሩ መስፈርቶች ከሚሰጡ ነጥቦች በተጨማሪ የማበረታቻ (ቦነስ) ነጥቦች ያገኛሉ፦
- በሕፃናት እና ታዳጊዎች (ዕድሜያቸው ከ18 ያልበለጡ)
- በሴቶች
- በአረጋውያን
- በአካል ጉዳተኞች
- በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወይም በስደተኞች
- በፎቶግራፍም ሆነ በአጫጭር ፊልም ዘርፍ ማንኛውም ግለሰብ፣ ማናቸውም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የሚድያ እና የኮሙኒኬሽን ድርጅት፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን ወይም የስልጠናና ትምህርት ሰጪ ተቋማት ወይም በተዘረዘሩት ተቋማት የሚሠሩ፣ የሚሰለጥኑ፣ የሚማሩ እና የሚያስተምሩ ግለሰቦች እራሳቸውን ወክለው/በግል መሳተፍ ይችላሉ።
- በውድድሩ ለመሳተፍ ኢትዮጵያዊ መሆን ያስፈልጋል። ውድድሩ የሀገር ውስጥ ባለሞያዎችን እና ተቋማትን ለማበረታታት እና ዐቅም ለመገንባት ያለመ እንደመሆኑ በሀገር ውስጥ የተመዘገቡ ቢሆኑም አልያም ተቀማጭነታቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ ቢሆኑም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ለሆኑ የሲቪክ ማኅበረሰብም ሆኑ ሌሎች ተቋማት ክፍት አይደለም።
- በፎቶግራፍ ውድድርም ሆነ በአጫጭር ፊልሞች ውድድር ለመሳተፍ ምንም ዐይነት ክፍያ አይጠየቅም።
- የኢሰመኮ ሠራተኞች በሁለቱም ዘርፎች የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልሞች ውድድሮች መሳተፍ የሚችሉ ሲሆን፣ የጥበብ ሥራዎቹ ለዕይታ ለመቅረብ ብቁ ሆነው ከተገኙ ሊመረጡ ይችላሉ። ሆኖም በውድድሩ ለሽልማት እጩ ከሚሆኑ የጥበብ ሥራዎች መካከል አይካተቱም።
- በፎቶግራፍ ዘርፍ የኪነጥበብ ሥራውን ያቀረበ ተሳታፊ በአጫጭር ፊልሞች ዘርፍ ተጨማሪ የጥበብ ሥራ ለውድድር ማቅረብ አይችልም። እንዲሁም በአጫጭር ፊልሞች ዘርፍ የጥበብ ሥራውን ለውድድር ያቀረበ ተሳታፊ በፎቶግራፍ ዘርፍም ለውድድር አይቀርብም። ስለሆነም ተሳታፊዎች በአንድ ዘርፍ ብቻ የሚወዳደሩ ይሆናል።
- በተጨማሪም አንድ ተሳታፊ በሚወዳደርበት ዘርፍ ከአንድ በላይ የኪነጥበብ ሥራ ማወዳደር አይችልም።
- ተሳታፊዎች ለሌሎች ውድድሮች ያቀረቧቸውን የኪነጥበብ ሥራዎች ለዚህ ውድድር ማቅረብ ይችላሉ። ሆኖም የፎቶግራፍ ዘርፍ ተሳታፊዎች ለዚህ ውድድር የሚያቀርቧቸውን የኪነጥበብ ሥራዎች ለውድድሩ አዘጋጆች ከላኩ በኋላ በመገናኛ ብዙኃን አልያም በማንኛውም ማኅበራዊ ሚድያ ሊያሰራጩት አይገባም።
- የውድድሩ አዘጋጆች ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም መረጃ አልያም ከውድድሩ ጋር በተያያዘ ሌላ ምክንያት ተሳታፊዎች በተሳትፎ ቅጹ ባስቀመጡት አድራሻ ለማግኘት ሞክረው፣ ተሳታፊዎች በተገለጸው አድራሻ በተገቢው ጊዜ በማይገኙበት ወይም ምላሽ በማይሰጡበት ወቅት የውድድሩ አዘጋጆች የኪነጥበብ ሥራዎን ከውድድሩ ውጪ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህም የኢሰመኮ ውሳኔ የመጨረሻ ነው።
- ተሳታፊዎች ከሚወክሉት ተቋም ወይም ከእራሳቸው ውጪ (የሦስተኛ ወገንን) ያሉ የኪነጥበብ ሥራዎችን ለውድድሩ ማቅረብ አይችሉም። የኢሰመኮ ይህንን የማረጋገጥ ሙሉ መብት የተጠበቀ ነው።
- በአንድ የውድድር ዘርፍ በብዛት እና በብቁነት በቂ ተወዳዳሪ አለመኖሩ ከድምዳሜ ላይ ከተደረሰ፣ የውድድሩ አዘጋጆች የውድድር ዘርፉን ሊሰርዙ ይችላሉ። ይህም ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል። ሆኖም ኢሰመኮ በተሰረዘው የውድድር ዘርፍ የተላኩ የኪነጥበብ ሥራዎችን ለተሳታፊዎች የመመለስ ግዴታ ያለበት ሲሆን፣ በተሳትፎ መመሪያ እና ደንቦች አንቀጽ (2) እና (8) መሠረት ጥቅም ላይ ማዋል አይችልም።
- የውድድሩ ተሳታፊዎች በሙሉ የተሳትፎ ዕውቅና ሰርትፍኬት የሚያገኙ ይሆናል፤
- ለውድድሩ የቀረቡ የኪነጥበብ ሥራዎች በሙሉ እንደ አግባብነታቸው ለተለያዩ የኢሰመኮ እና የአጋር ድርጅቶች የሰብአዊ መብቶች መረጃዎች፣ ሪፖርቶች፣ የማስተማርያ እና የኮሙኒኬሽን ሰነዶች ወይም የኦድዮ ቪዥዋል ሥራዎች የሚውሉ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት የኪነጥበብ ሥራ አቅራቢው ሙሉ ዕውቅና ይሰጣል፤
- ከዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፌስቲቫሉ ባሻገር ከአንድ እስከ አስረኛ ደረጃ የተመደቡ የኪነጥበብ ሥራዎች በተለያዩ ሀገር አቀፍ እና የክልል መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ በተለያዩ አግባብ ባላቸው የኢሰመኮ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ እና ሌሎች መድረኮች እንዲሰራጩ፣ እና ለዕይታ እንዲበቁ የሚደረግ ይሆናል። በዚህ ወቅት ለኪነጥበብ ሥራ አቅራቢው ዕውቅና የሚሰጥ ይሆናል፤
- በዝግጅቱ ለዕይታ የሚቀርቡ የኪነ ጥበብ ሥራ አቅራቢዎች/ ተሳታፊዎች ተጨማሪ የማስተዋወቂያ እና በተቻለ መጠን የተለያዩ የዐቅም ግንባታ እና የሥራ ዕድል መፍጠሪያ አጋጣሚዎች ለመፍጠር ኢሰመኮ ጥረት የሚያደርግ ይሆናል፤
- ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የተመደቡ የፎቶግራፍ እና የአጫጭር ፊልሞች ሥራዎች እንደየደረጃቸው በሚከተለው ሠንጠረዥ የተመለከተውን የገንዘብ ሽልማት (በኢትዮጵያ ብር) የሚያገኙ ይሆናል።
ደረጃ | የፎቶግራፍ ውድድር አሸናፊዎች | የአጫጭር ፊልሞች ውድድር አሸናፊዎች | |
የጀማሪ/የአማተር | የባለሞያ/የፕሮፌሽናል | ||
አንደኛ | 40 ሺህ | 50 ሺህ | 150 ሺህ |
ሁለተኛ | 30 ሺህ | 40 ሺህ | 120 ሺህ |
ሦስተኛ | 20 ሺህ | 30 ሺህ | 100 ሺህ |
ልዩ ትኩረት የማኅበርሰብ ክፍሎች ቦነስ/ማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት፡ በሁሉም ዘርፍ እና በሁሉም ደረጃ፡ 5000 ሺህ ብር |
- ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ተሸላሚ የሆኑ ተሳታፊዎች በቀጣይ ዙር የኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል በሚዘጋጁ ውድድሮች የሚቀርቡ የኪነጥበብ ሥራዎች ገምጋሚ ፓነል አባል እንዲሆኑ ጥሪ ይደረግላቸዋል።
- ገንዘብ ነክ ያልሆኑ ሽልማቶችን ወደ ገንዘብ ሽልማት የመቀየር አማራጭ የለም።
ገንዘብ ነክ ለሆኑ እና ላልሆኑ ሽልማቶች በሀገሪቱ ሕግ መከፈል ለሚኖርባቸው ቀረጦች እና ሌሎች ግብሮችን፣ ቅጣቶችን፣ ክፍያዎችን ወይም የአስተዳደር ጉዳዮችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኃላፊነት አይወስድም።
ይህ የውድድር ዘርፍ በቂ የሆነ መኖሪያ በማግኘት መብት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ተሳታፊዎች በቂ ስለሆነ መኖሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ፣ ሐሳብ የሚሰጡ፣ የመብቱ መከበር ወይም መጣስ በተጨባጭ ምን እንደሚመስል የሚገልጹ እና ለማሰላሰል የሚጋብዙ ምስሎችን (ፎቶግራፎችን) የሚያቀርቡበት ነው።
በቂ የሆነ መኖሪያ ማለት ምን ማለት ነው? መኖሪያ የሌለው ሰው አኗኗር ምን ይመስላል? መኖሪያ ለሴቶች እና ለወንዶች አንድ ዐይነት ትርጉም አለው? መኖሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸው ሰዎች ምን ዐይነት ችግር ደረሰባቸው? የአካል ጉዳተኞች መኖሪያ ምን ይመስላል?
ይህ የፎቶግራፍ ውድድር ዘርፍ እነዚህን እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በምስል ለመግለጽ እና ለማሰላሰል የሚጋብዝ ነው። በዚህ የውድድር ዘርፍ ለሚቀርቡ የኪነጥበብ ሥራዎች የመወዳደሪያ መስፈርቶች ለጀማሪ/አማተር እና ለባለሞያ/ፕሮፌሽናል ተመሳሳይ ናቸው።
የፎቶግራፍ ውድድር የቴክኒክ መስፈርቶች
- ለውድድር የሚቀርበው ፎቶግራፍ ለዘርፉ ከተመደበው ጭብጥ/ርዕሰ ጉዳይ ጋር (በቂ የሆነ መኖሪያ) ተያያዥነት ያለው ሊሆን ይገባል።
- በዚህ ዘርፍ የሚቀርቡ የፎቶግራፍ/የኪነጥበብ ሥራዎች ከመስከረም ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የተነሱ/የተወሰዱ ሊሆን ይገባል።
- ለዚህ ውድድር የሚቀርቡ ሥራዎች ከ1 ሜጋ ባይት ያላነሱ እና ከ5 ሜጋ ባይት የማይበልጡ ሊሆን ይገባል። በ JPEG ሴቭ የተደረጉ እና በተቻለ መጠን ለኅትመት አመቺ በሆነ ከፍተኛ የጥራት (ሪዞሉሽን) ደረጃ ሊሆኑ ይገባል።
- ለፎቶግራፍ ሥራ ከሚያስፈልገው የአርትዖት (editing) ሥራ በተጨማሪ፣ መጠነኛ በሆነ መልኩ ፎቶግራፉን ለማሳመር የሚደረጉ (digital manipulations) ሥራዎች ተቀባይነት አላቸው። ሆኖም እነኚህ ለውጦች ምን እንደሆኑ እና ለምን ዓላማ እንደተሠሩ በተሳትፎ ቅጹ ላይ በግልጽ ሊመላከት ይገባል። የውድድሩ አዘጋጆች ይህንን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለተሳታፊው ሊያቀርቡ ይችላሉ። እንዲሁም ተጨማሪ ሥራዎች ያልተሠራበትን (ኦሪጂናል) ፎቶግራፍ እንዲላክ ሊጠይቁ ይችላሉ።
- ተሳታፊው የሚጠቀመው ካሜራ ቢያንስ 3000 ፒክሰል (ወደ ጎን) እና 300 DPI/PPI setting ሊሆን ይገባል። በሞባይል/ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚነሱ ፎቶግራፎች ይህንን መስፈርት ማሟላት የሚጠበቅባቸው ባይሆንም፣ ለውድድር ተቀባይነት የሚኖራቸው ከፍተኛ ጥራት (high resolution) ያላቸው እና ከተመደበው ጭብጥ/ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ከሆነ ብቻ ነው።
- በተለይ በአንድ ሰው ላይ የሚያተኩሩ ፎቶግራፎች ከሆኑ የዛን ሰው ሙሉ ፈቃድ ማግኘት፣ ከ18 ዓመት በታች ከሆኑ ደግሞ በሕግ ሙሉ መብት ያለውን ወይም የአሳዳጊ ሙሉ ፈቃድ ማግኘቶትን ያረጋግጡ።
- Collage ወይም በአንድ ፍሬም በርካታ ምስሎችን የያዘ ፎቶግራፍ በውድድሩ አይካተትም። ለውድድር በሚቀርበው ፎቶግራፍ ላይ ፊርማ፣ watermark፣ overlay እና የመሳሰሉትን ምልክቶች ወይም ጽሑፎች መጨመር አይገባም።
ተጨማሪ ማብራሪያ
በእነዚህ መመሪያዎች እና ደንቦች ስለተጠቀሱ ሂደቶች ወይም መረጃዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት filmfest@ehrc.org ይላኩልን ወይም በ +251973149236 ይደውሉልን።
ይህ የውድድር ዘርፍ በሕይወት የመኖር መብት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ተሳታፊዎች ስለ ሕይወት እና በሕይወት የመኖር ትርጉም የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ፣ ሐሳብ የሚሰጡ፣ የመብቱ መከበር ወይም መጣስ በተጨባጭ ምን እንደሚመስል የሚገልጹ እና ለማሰላሰል የሚጋብዙ አጫጭር ቪድዮዎችን የሚያቀርቡበት ነው።
በዚህ የውድድር ዘርፍ ተሳታፊዎች በአንድ ሰው ሕይወት ዙሪያ (የራሳቸው አልያም የሦስተኛ ወገን) ቢያተኩሩ የሚመረጥ ቢሆንም፣ ከርዕሰ ጉዳዮ ጋር የተያያዙ የኪነጥበብ ሥራዎችን ማቅረብ ይችላል። አልያም በሕይወት ዘመናቸው በተለያዩ ዘርፎች አስተዋጽዖ ባደረጉ ሰዎች ሕይወት ዙርያ የሚያተኩር ሊሆን ይችላል። የአንድ ሰው ሕይወት ዋጋ ምን ያክል ነው? ትርጉም ያለው ሕይወት ምን ማለት ነው? የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የአረጋውያን፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ እና የስደተኞች ሕይወት እኩል ዋጋ አለው? ወዘተ
ርዕሰ ጉዳዩ ሰፊ እንደመሆኑ መጠን ይህ የአጫጭር ፊልሞች ውድድር ዘርፍ እነዚህን ወይም ሌሎች በሕይወት የመኖር መብትን እና የሕይወትን ዋጋ ለማሰብ እና ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎችን ለማስታወስ የሚጋብዝ ነው። በዚህ ውድድር መመሪያ እና ደንቦች በተገለጸው መሠረት ማስታወቂያ የሚያካትቱ የኪነጥበብ ሥራዎች ከውድድሩ ውጪ ይደረጋሉ። በዚህ የውድድር ዘርፍ ልብ ወለድ አልያም የዘገባ ሥራዎች (narrative or documentary) ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም፣ የሙዚቃ እና የዳንስ ይዘት ያላቸው ሥራዎች በዚህ ውድድር አይካተቱም። በሂደት ላይ ያሉ ወይም ያልተጠናቀቁ የኪነጥበብ ሥራዎችም ተቀባይነት አይኖራቸውም።
ለጀማሪ/አማተር (ሞባይል/ተንቀሳቃሽ ስልክ) እና ለባለሞያ/ፕሮፌሽናል የኪነጥበብ ሥራዎች የመወዳደሪያ መስፈርቶች ልዩነት አላቸው።
የጀማሪ/የአማተር የሞባይል/የተንቀሳቃሽ አጭር ፊልም የቴክኒክ መስፈርቶች
- ለውድድር ዘርፉ ከተመደበው ጭብጥ/ርዕሰ ጉዳይ (ሕይወት/በሕይወት የመኖር መብት) ጋር የተያያዘ መሆን አለበት።
- በአጠቃላይ ርዝመት ከ4 ደቂቃዎች ያላነሰ እና ከ9 ደቂቃዎች ያልበለጠ።
- በዚህ ዘርፍ የሚቀርቡ ሥራዎች ከመስከረም ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የተነሱ/የተቀረጹ ሊሆን ይገባል።
- በእንግሊዘኛ ቋንቋ ወይም በማንኛውም የኢትዮጵያ ቋንቋ የተሠራ ሥራ ለውድድሩ መቅረብ ይችላል። ሆኖም በአማርኛ ወይም በእንግሊዘኛ ቋንቋ “ሰብታይትል” ሊደረግ ይገባል።
- በተንቀሳቃሽ ስልክ ለሚቀረጹ አጫጭር ፊልሞች ለማሰራጨት በአብዛኛው ተመራጩ መንገድ ዩትዩብ እንደመሆኑ፣ ለዚህ ውድድር ዘርፍ የሚያገለግሉ የቴክኒክ መስፈርቶች የዩትዩብ መድረክ የሚጠይቃቸው ናቸው። በዋነኛነት ለውድድር የሚቀርቡ ሥራዎች የሚከተሉትን የጥራት መስፈርቶች ሊያሟሉ ይገባል።
- Aspect ratio: 9:16 (creates the vertical format)
- Resolution: 1920 pixels by 1080 pixels (standard length-by-width ratio for vertical content)
- ለዚህ ዘርፍ ለውድድር የሚቀርቡ ሥራዎች ማናቸውም የቪድዮ ዐይነቶች ሊሆኑ ይችላሉ፦ Animated፣ Live-action፣ Screen recording፣ Whiteboard፣ Motion graphics፣ Typography ወይም Combination።
በሞባይል አጫጭር ፊልሞችን ስለመቅረጽ ጠቃሚ ማብራሪያ እዚህ ወይም እዚህ ማግኘት ይቻላል። ኢሰመኮ ለሦስተኛ ወገን ይዘቶች ኃላፊነት አይወስድም።
የባለሞያ/የፕሮፌሽናል አጭር ፊልም የቴክኒክ መስፈረቶች
- ለውድድር ዘርፉ ከተመደበው ጭብጥ/ርዕሰ ጉዳይ (ሕይወት/በሕይወት የመኖር መብት) ጋር የተያያዘ መሆን አለበት።
- በአጠቃላይ ርዝመት ከ5 ደቂቃዎች ያላነሰ እና ከ25 ደቂቃዎች ያልበለጠ።
- በዚህ ዘርፍ የሚቀርቡ ሥራዎች ከመስከረም ወር 2015 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የተነሱ/የተቀረጹ ሊሆን ይገባል።
- በእንግሊዘኛ ቋንቋ ወይም በማንኛውም የኢትዮጵያ ቋንቋ የተሠራ ሥራ ለውድድሩ መቅረብ ይችላል። ሆኖም በአማርኛ ወይም በእንግሊዘኛ ቋንቋ “ሰብታይትል” ሊደረግ ይገባል።
- ለዚህ ዘርፍ ለውድድር የሚቀርቡ ሥራዎች ማናቸውም የቪድዮ ዐይነቶች ሊሆኑ ይችላሉ፦ Animated፣ Live-action፣ Screen recording፣ Whiteboard፣ Motion graphics፣ Typography ወይም Combination።
- ተመራጭ formats: An H264 or MP4 file compressed from the original 1080p or 720P master. ቢያንስ ሊያሟላ የሚገባው መስፈርት (Minimum Acceptable): An H264 or MP4 file at 480i. Do not rip from a DVD unless you have no other option.
- ለውድድር በሚቀርበው የኪነጥበብ ሥራ ላይ ፊርማ፣ watermark፣ overlay እና የመሳሰሉትን ምልክቶች ወይም ጽሑፎች መጨመር አይገባም።
- የምስጋና/ የዕውቅና ፍሬሙ ከ1 ደቂቃ ሊበልጥ አይገባም።
አጫጭር ፊልሞችን ስለመቅረጽ ጠቃሚ ማብራሪያ እዚህ ማግኘት ይቻላል። ኢሰመኮ ለሦስተኛ ወገን ይዘቶች ኃላፊነት አይወስድም።
ተጨማሪ ማብራሪያ
በእነዚህ መመሪያዎች እና ደንቦች ስለተጠቀሱ ሂደቶች ወይም መረጃዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት filmfest@ehrc.org ይላኩልን ወይም በ +251973149236 ይደውሉልን።
የተሳትፎ ቅጽ ⬇️ (የውድድሩ አጠቃላይ መመሪያዎች እና ደንቦች ⬇️)
ጠቃሚ ሰነዶች ⬇️