የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ ያለውን የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ እንዲሁም ብሔራዊ የንግድ እና የሰብአዊ መብቶች የድርጊት መርኃ ግብርን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ። የውይይት መድረኩ ከዳኒሽ ሰብአዊ መብቶች ተቋም (DIHR) ጋር በመሆን የተዘጋጀ ሲሆን ጥቅምት 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከአከባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከማዕድን ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት እንዲሁም ከሌሎች የሚመለከታቸው መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በውይይቱ የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖችን የተመለከተ ገለጻ የተደረገ ሲሆን በንግድ ዐውድ ውስጥ የመንግሥታት መብቶችን የመጠበቅ ግዴታ፣ የንግድ ድርጅቶች የሰብአዊ መብቶችን የማክበር ኃላፊነት እና ከንግድ ጋር ለተያያዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ውጤታማ መፍትሔ የመስጠት ኃላፊነትን በሚያስረዱ የንግድ እና የሰብአዊ መብቶች መመሪያ መርሖችና ዓምዶች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ በኢትዮጵያ ያሉ የንግድ እና የሰብአዊ መብቶችን የሚመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች የተዳሰሱ ሲሆን ኢሰመኮ ካከናወናቸው የሰብአዊ መብቶች አተገባበር ክትትል ሥራዎች በመነሳት በንግድ ዐውድ ውስጥ የሚስተዋሉ የሰብአዊ መብቶች አተገባበር ተግዳሮቶች እና የንግድ እና ሰብአዊ መብቶች የድርጊት መርኃ ግብርን አስፈላጊነት በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሦስተኛው ሁሉ-አቀፍ የግምገማ መድረክ (Universal Periodic Review) ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የሰብአዊ መብቶች መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላትን ብሔራዊ የድርጊት መርኃ ግብር እንድታዘጋጅ የተሰጣትን ምክረ ሐሳብ መቀበሏን፣ በዚህም የተገኙ መልካም አጋጣሚዎች፣ የድርጊት መርኃ ግብር ዝግጅት ሂደቶች እና ሂደቶቹን ሊደግፉ የሚችሉ መልካም ተሞክሮዎች ላይ ያተኮረ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች ተቋማቸው የተቋቋመበትን ዓላማ እና በሕግ የተጣለባትን ኃላፊነት መሠረት በማድረግ ከንግድና ከሰብአዊ መብቶች ጋር በተያያዘ ያላቸውን ድርሻ እና ልምድ አካፍለዋል። መልካም አጋጣሚዎችን እና ተግዳሮቶችን በተመለከተም የተወያዩ ሲሆን የቀጣይ እርምጃዎችን እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ተግባራትን ለይተዋል፡፡
የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል የንግድ ሥራዎች በአግባቡ መመራታቸው ለሰብአዊ መብቶች መተግበር የሚያበረክቱትን አወንታዊ አስተዋጽዖ የገለጹ ሲሆን በአግባቡ አለመመራታቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመፈጸም ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥሩ አመልክተዋል።