የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሲዳማ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ አራት የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከላት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ባደረገው ክትትል ዙርያ በመስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።
በኦሮሚያ ክልል እልፍነሽ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከልና ምግባረ ሰናይ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መርጃ ድርጅት፣ በአማራ ክልል አጣዬ የአረጋውያንና ምስኪኖች መርጃ ማእከል እና በሲዳማ ክልል የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ሃዋሳ ቅርንጫፍ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማእከላት ክትትል አከናውኗል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በክትትሉ ግኝቶች እና ምክረ-ሃሳቦች ዙርያ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ክትትሉ የተካሄደባቸውን ማእከላት አመራሮችን ጨምሮ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በዝግጅቱ ወቅት ተሳታፊዎች በክትትል ግኝቶቹ ላይ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፤ በክትትሉ ላይ የተመለከቷቸውን ውስንነቶች፣ ያላቸውን ልምድና ሊካተቱ ይገባሉ ያሏቸውን ምክረ-ሃሳቦች እንዲሁም የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
በአብዛኛው በአረጋውያን ላይ የሚደርሰው የመብቶች ጥሰት በቅርበት በሚሠሩ ሠራተኞች መሆኑን እና የተወሰኑ ማእከላት በአካባቢያቸው በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በሚያቀርቧቸው አገልገሎቶች ላይ ጫና እየተፈጠረባቸው ነው ሲሉ የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደ ተግዳሮት አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም አረጋውያን በማእከላት ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜ ሰላምታን ጨምሮ ማኅበራዊ ሕይወት የሚናፍቃቸው በመሆኑ በማኅበረሰቡ እንዲጎበኙ፣ የመንከባከቢያ ማእከላቶቹ ለአካል ጉዳተኛ አረጋውያን ተደራሽ እንዲሆኑና እነዚህ ማእከላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ መንግሥት አቅማቸውን መገንባት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የኢሰመኮ የአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ፣ ማእከላቱ እየሠሩ ላሉት ሥራ እውቅና እንደሚሰጡ በመግለጽ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አክለውም አረጋውያንን መንከባከብ ለማእከላቱ ብቻ የሚተው ሥራ ሳይሆን በዋናነት የመንግሥት ቀጥሎም የሁሉም ማኅበረሰብ ኃላፊነት መሆን እንዳለበትና ይህም ችሮታ ሳይሆን የአረጋውያን እንክብካቤ የማግኘት መብት መሆኑን ገልጸዋል። ይህ የምክክር መድረክ የተለያዩ የመንከባከቢያ ማእከላት እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና ልምድ እንዲለዋወጡ ያስቻለም ነበር፡፡