1. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ዐውድ ውስጥና ውጭ የሚፈጸሙ ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች አሳሳቢ ጉዳዮችንና ጥሰቶችን አስመልክቶ ክትትልና ምርመራ ማድረጉን ቀጥሏል። በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል በሚደረጉ ውጊያዎች እና ከውጊያ ዐውድ ውጭ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ዘረፋ፣ የሰዎች እገታ እና መፈናቀል መፍትሔ ለመስጠት የፌዴራል መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ እና ተጨባጭ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት የሚገባው መሆኑን የሚገልጹ ሪፖርቶችን ኢሰመኮ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። እንዲሁም በአማራ ክልል በቀጠለው የትጥቅ ግጭት ዐውድ ውስጥ ለሚፈጸሙ ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስር፣ እገታ፣ አስገድዶ መሰወር፣ ሲቪል ሰዎችን የማይለዩ የከባድ መሣሪያና የአየር ጥቃቶች፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ዘላቂ እልባት ለመስጠት ሰላማዊ መፍትሔ ማፈላለግን ጨምሮ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚያግዙ አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ኢሰመኮ በሰብአዊ መብት ምርመራ እና ክትትል ሥራዎቹ ላይ ተመሥርቶ በተለያየ ጊዜ ባወጣቸው መግለጫዎች ማሳሰቡ ይታወሳል።
2. በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከተራዘሙ የትጥቅ ግጭቶች ጋር በተያያዘና ከግጭት ዐውድ ውጭ የተፈጸሙ እንዲሁም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በአፋር፣ በሶማሊ፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ የቀጠሉና በቅርብ ጊዜያት የተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችንና ሥጋቶችን በተመለከተ ኢሰመኮ ክትትልና ምርመራ ማድረጉን ቀጥሏል። በዚህም መሠረት በተለይም የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት፣ ተጎጂዎችን እና የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዐይን ምስክሮችን እና ከአስገድዶ መሰወር የተለቀቁ ሰዎችን በማነጋገር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል። ይህ ሪፖርት ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ እጅግ አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀል ይገኙበታል።
3. ኢሰመኮ በዚህ ሪፖርት ውስጥ ያካተታቸው የተመረጡ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችና አሳሳቢ ሆነው የቀጠሉ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች እስካሁን በክትትልና በምርመራ ማረጋገጥ የቻላቸውን ብቻ ነው። በጸጥታ መደፍረስ፣ ከመንግሥት አካላት ተገቢውን ምላሽና ትብብር በወቅቱ ባለማግኘትና በሌሎች ምክንያቶች ምርመራቸውና ክትትላቸው የዘገዩና የተጓተቱ በርካታ ጉዳዮችን በመርመርና ክትትል በማድረግ በተገቢው ጊዜ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።
ከሕግ ውጭ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ
4. ከየካቲት 15 እስከ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ደጋ ዳሞት ወረዳ (ዝቋላ ወገም፣ ፈረስ ቤት 01፣ ገሳግስ እና ጉድባ ሰቀላ ቀበሌዎች) እና ሰከላ ወረዳ (አጉት፣ ጉንድል እና አምቢሲ ቀበሌዎች እና ግሼ ዓባይ ከተማ) በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል የተካሄዱ የትጥቅ ግጭቶችን ተከትሎ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት፣ አካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ደርሷል።
5. የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ ብራቃት ቀበሌ በሚገኘው የጋፊት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የአብነት ተማሪዎች የዕለቱን ትምህርትና ጉባኤ ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ አጠናቀው ወደ ማደሪያ ጎጇቸው ከገቡ በኋላ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች አባላት ከሌሊቱ 6፡30 ሰዓት ገደማ ወደ ቦታው ደርሰው ተማሪዎችን “ውጡ” እያሉ ተኩስ በመክፈት ቀድመው በወጡ 11 ተማሪዎች ላይ ግድያ እንደፈጸሙ፤ ሌሎች 8 ተማሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውለው ካሳደሩ በኋላ በማግስቱ ምንም ጥፋት የለባችሁም ብለው እንደለቀቋቸው ኢሰመኮ ለመረዳት ችሏል። በወቅቱ በአቅራቢያው የሚንቀሳቀስ የታጠቀ ኃይል እንዳልነበር ምስክሮች ለኢሰመኮ አስረድተዋል።
6. መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ከአማራ ክልል፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን የተነሱ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር በኤፍራታና ግድም እና ቀወት ወረዳዎች በሚገኙ የተወሰኑ ቀበሌዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት በሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸሙን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ ንብረት መውደሙን፣ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን እንዲሁም የቀንድ ከብቶችና ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች መዘረፋቸውን ኢሰመኮ ተረድቷል።
7. መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ ዘንዘልማ አካባቢ አቶ ብርሃኑ ሽባባው አካል፣ አቶ በላይ አካል እና አቶ ተሾመ ይበልጣል የተባሉ ነዋሪዎች አንዱ በሚሠራበት ሱቅ እና ሁለቱ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ በሚል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 14 በተለምዶ ጉዶ ባሕር አካባቢ የፊጥኝ እንደታሰሩ በጥይት ተገድለው ተገኝተዋል።
8. በባሕር ዳር ከተማ ዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ ጋጃ መስክ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት አካባቢ ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት በተፈጸመ ጥቃት ሶላት ስግደት አከናውነው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ የነበሩ የእስልምና ተከታይ 5 ሰዎች (አራቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ) ተገድለዋል።
9. ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ከጧቱ 3፡00 ሰዓት ላይ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ አጎና በተባለች መለስተኛ ቀበሌ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከእስቴ ወረዳ ወደ ላይ ጋይንት ወረዳ በመጓዝ ላይ እያሉ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች (በተለምዶ ፋኖ) ድንገተኛ የደፈጣ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ታጣቂዎቹ አካባቢውን ጥለው እንደሸሹ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወደ ቦታው (አጎና ቀበሌ) በመግባት 7 (1 ሴት እና 6 ወንዶች) ሲቪል ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ ግድያ መፈጸማቸውን፣ ከ15 በላይ የሚሆኑ የቆርቆሮ ክዳን ያላቸው መኖሪያ ቤቶች እና 3 የገለባ ቤቶችና ንብረት መቃጠላቸውን እንዲሁም ከ100 በላይ የሚሆኑ የቀበሌው ነዋሪዎች ወደ ሌላ አካባቢ የተፈናቀሉ መሆኑን የቀበሌው ነዋሪዎችና ተጎጂዎች ለኢሰመኮ ገልጸዋል። በወቅቱም ግለሰቦቹ ቃጠሎውን ለመቆጣጠርና ለማጥፋት ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም የመንግሥት የጸጥታ ኃሎች ጥይት በመተኮስ እንደከለከሏቸውና ሆን ተብሎ የግለሰቦቹ ቤት እና ንብረት እንዲቃጠል እንደተደረገም ጨምረው አስረድተዋል። በዚህም የተነሳ በመኖሪያ ቤቶቹ ውስጥ የነበሩ የቤት ቁሳቁስ፣ አልባሳት፣ እህል እንዲሁም የአንድ ግለሰብ 8 በጎች ሙሉ በሙሉ እንደተቃጠሉ ለመረዳት ተችሏል።
10. ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ ከ7፡00 ሰዓት አካባቢ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ተሬ ቀበሌ ውስጥ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በጉሎ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ግቢ ውስጥ 2 ሲቪል ሰዎች ሲገደሉ አንድ ሴት መምህርትን ጨምሮ ሌሎች 9 ሲቪል ሰዎች የቆሰሉ መሆኑን ኢሰመኮ ተረድቷል።
11. ታኀሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጉዱሩ ወረዳ ውስጥ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በየነ ጢቂ፣ ጉደታ ፊጤ፣ ሀብታሙ ንጋቱ፣ ታዴ መንገሻ፣ ዳመና ሊካሳ፣ ዱጋሳ ዋኬኔ፣ ሕፃን አብዲ ጥላሁን እና ሕፃን ኦብሳ ተሬሳ የተባሉ 8 ሰዎች ተገድለዋል። በተጨማሪም ስንታየሁ ታከለ፣ ሽቶ እምሩ፣ ተሜ ኑጉሴ እና አለሚ የተባሉት ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአካባቢው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) በሰፊው ይንቀሳቀስ የነበረ መሆኑን እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው በሚደረጉ ውጊያዎች አልፎ አልፎ በድሮን ይጠቀም የነበረ መሆኑን ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
12. ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለሌላ ግዳጅ አካባቢውን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች በማግስቱ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በኋላ “ለመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ምግብ ስታቀርቡ ነበር” በሚል ምክንያት በወረዳው 01 ቀበሌ የሚገኘው ሳላይሽ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ጥበቃ የነበሩት አቶ ስዩም ካሴን በጥይት በመምታት መግደላቸውን እንዲሁም ከበደ ዓለማየሁ የተባሉ ነዋሪን ከመኖሪያ ቤታቸው ከወሰዷቸው በኋላ በአካባቢው ጫካ ውስጥ አስክሬናቸው ወድቆ መገኘቱን ኢሰመኮ አረጋግጧል።
13. ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋት 2 ሰዓት ጀምሮ ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ ጉጂ ዞን፣ ገላና አባያ ወረዳ ኤርገንሳ ቀበሌ ለሚኖሩ ነዋሪዎች የኩፍኝ በሽታ ክትባት ለመስጠት በመጓዝ ላይ በነበሩ ሠራተኞች ላይ በፈጸሙት ጥቃት የገላና አባያ ወረዳ አስተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊን ጨምሮ ሁለት ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፤ እንዲሁም 3 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ጥቃቱን ተከትሎ በገላና አባያ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ሲሰጥ የነበረው የሕክምና አገልግሎት እና የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ስርጭት ተስተጓጉሎ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።
14. ከየካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በአማራ ክልል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የአማራ ታጣቂ ቡድኖች የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በሚገኙ አዋሳኝ ቀበሌዎች በሲቪል ሰዎች ላይ በተከታታይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች 25 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል፤ 4 ሲቪል ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል እንዲሁም ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ሲቪል ሰዎችን አግተው ወስደዋል። በታጣቂዎቹ በተፈጸመው ጥቃት በርካታ የመኖሪያ ቤቶችም ተቃጥለዋል። በተመሳሳይ በዚሁ ደራ ወረዳ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች ከኅዳር ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በወረዳው በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች በሲቪል ሰዎች ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች 15 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፤ ቁጥራቸው ለጊዜው በትክክል ያልታወቀ በርካታ ነዋሪዎችን አግተው ወስደዋል፤ በርካታ የቀንድ ከብቶችን ዘርፈዋል እንዲሁም መኖሪያ ቤቶችን አቃጥለዋል።
15. መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ስልካምባ ከተማ ላይ የኦሮሞ ነጸነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት የወረዳው አበዪ ሄቤን ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ አቶ ሹመቴ ፋርስ እና ወ/ሮ ተቀባ አበጋዝ የተባሉ አረጋዊያን በመኖሪያ ቤቶቻቸው ፊት ለፊት ተገድለዋል። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አንድ የቀበሌው ነዋሪ ለኢሰመኮ ሲያስረዱ፦
“የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በብዛት ወደ ስልካምባ ከተማ እያለፉ ነበር፤ ለሰዓታትም ተኩስ ነበር፤ በኋላ ላይ ታጣቂዎቹ ከከተማው ማፈግፈግ ሲጀምሩ ያገኙትን ነዋሪ ያለማመንታት ተኩሰው እየገደሉ ይሸሹ ነበር። አቶ ሹመቴ እና ወ/ሮ ተቀባም ያለምንም ምክንያት በቡድኑ ተገድለዋል” ብለዋል።
16. መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡00 እስከ 5፡00 ባሉት ሰዓታት ማንነታቸው በውል ያልታወቀ የታጠቁ ቡድኖች በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ 02 ቀበሌ ውስጥ 7 ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውን ለማወቅ ተችሏል። በዕለቱ በተፈጸመ ጥቃት የቀበሌው ነዋሪ የሆነ እና የምዕራብ አርሲ ሃገረ ስብከት የዶዶላ ደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆነ ግለሰብ፣ ከባለቤቱ እና ከሁለት ልጆቹ ጋር በመኖሪያ ቤታቸው እያሉ እንዲሁም ሌላ አንድ ዲያቆን ከባለቤቱ እና ከእህቱ ጋር በመኖሪያ ቤታቸው መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል። በተመሳሳይ ቀን በዶዶላ ወረዳ ደነባ ቀበሌ በግምት ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ 4 የቀበሌው ነዋሪዎች ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ሰዎች/ቡድኖች በጥይት ተመተው ሲገደሉ 5 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ለማወቅ ተችሏል።
17. የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) በኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አመያ ወረዳ “የመንግሥት ሠራተኞችና የመንግሥት ጸጥታ ኃይል አባላት ቤተሰቦች ናችሁ” በሚል ወይም “ለመንግሥት አካላት ትብብር አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት በወረዳው በተለያዩ ቀበሌዎች በየካቲት እና ሚያዝያ ወራት በፈጸማቸው ተከታታይ ጥቃቶች በሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ፣ አካል ጉዳት፣ እገታ፣ ንብረት ውድመት እና ዘረፋ ፈጽሟል። ለምሳሌ በወረዳው አቡዬ ጀብላል ቀበሌ የካቲት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በፈጸመው ጥቃት 11 ሲቪል ሰዎችን ገድሏል፤ መኖሪያ ቤቶችንና ሞተር ብስክሌቶችን አቃጥሏል፤ የቀንድ ከብቶችን ዘርፏል። መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በወረዳው ቆታ ከተማ ላይ በፈጸመው ጥቃት 31 ሲቪል ሰዎችን ገድሏል፣ 3 ሲቪል ሰዎችን አቁስሏል፣ የቀንድ ከብቶችንና ሌሎች ንብረቶችን ዘርፏል እንዲሁም ንብረቶችን አቃጥሏል። ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በወረዳው ደራ ቲርቲሪ ቀበሌ ላይ ታጣቂ ቡድኑ በፈጸመው ጥቃት 2 ሲቪል ሰዎችን ገድሏል፣ ከ100 በላይ የተለያዩ የቀንድ ከብቶች ዘርፏል እንዲሁም በሚያዚያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በጎምንቦሬ አሊይ ቀበሌ 36 የቀንድ ከብቶችንና 3 የሞቶር ብስክሌት ዘርፏል።
18. በሲዳማ ክልል በወንዶ ገነት ወረዳ፣ ኤዶ ቀበሌ ከዚህ ቀደም የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ በአካባቢው ተሰማርቶ ጸጥታ ሲያስጠብቅ የነበረው የፌዴራል ፖሊስ የጸጥታ ኃይል ከአካባቢው መልቀቁን ተከትሎ የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በቀበሌው ነዋሪ በሆኑ እና ወደ ኦሮሚያ ክልል የመካለል ጥያቄ ሲያነሱ በቆዩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች እና በወረዳው የጸጥታ አካላት መካከል በተከሰተ ግጭት ቢያንስ አንድ ሰው የአካል ጉዳት እንደደረሰበትና ከሐዋሳ ወደ ወንዶ ገነት ከተማ የሚወስደው ዋና መንገድም ለሰዓታት ተዘግቶ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል። በተመሳሳይ የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ድረስ በቀበሌው በሁለቱ ወገኖች መካከል እንደገና የተኩስ ልውውጥ ተካሂዶ በግጭቱ የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ 4 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በኤዶ ቀበሌ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ አጎራባች በሆነው እና በተመሳሳይ ወደ ኦሮሚያ ክልል የመካለል ጥያቄ ሲነሳበት በነበረው በወተራ ቀጨማ ቀበሌም በተወሰነ መልኩ አለመረጋጋት እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል። ግጭቱን ተከትሎ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው ተመልሶ በመግባት ግጭቱን ማስቆም ችሏል። ይህ ግጭት በአካባቢው እየጨመረ የመጣ የጸጥታ ሥጋት እና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያሳያል።
19. የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ባስኬቶ ዞንላስካ ዙሪያ ወረዳ፣ ቡኒ ባሳ ክላስተር ከደቡብ ኦሞ ዞን፣ ሰላማጎ አካባቢ የመጡ መሆናቸው የተገለጸ ታጣቂዎች የአካባቢው ነዋሪዎች ከብቶችን ለመዝረፍ በተደጋጋሚ ጥይት በመተኮስ በአካባቢው በነበረው የኢንቨስትመንት ማሳ በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ 4 ሰዎችን ገድለዋል። በአካባቢው ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች የተፈፀሙ መሆኑንና ከመስከረም 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ጊዜያት የአሁኑን ጨምሮ 10 ሰዎች (4 ሴቶች እና 6 ወንዶች) በተመሳሳይ ሁኔታ መገደላቸውን እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች 66 ከብቶች እና 29 ፍየሎች መዘረፋቸውን ኢሰመኮ ተረድቷል።
20. መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 11.00 ሰዓት አካባቢ ከኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ ጉጂ ዞን፣ ገላና ወረዳ ቀበሌዎች የመጡ ታጣቂዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ በፈጸሙት ጥቃት አንድ የእርሻ ሥራ ላይ የነበረ የቀበሌው ነዋሪ በተተኮሰበት ጥይት ተገድሏል። በተመሳሳይ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 11.00 ሰዓት አካባቢ በዚሁ ወረዳ ቆቦ ቀበሌ በታጣቂዎቹ በተፈፀመ ጥቃት ከብት በመጠበቅ ላይ የነበረ አንድ ሕጻን በተተኮሰበት ጥይት ተመቶ ተገድሏል። ታጣቂዎቹ ሚያዚያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 10፡00 ሰዓት አካባቢ በወረዳው ዳኖ ቀበሌ በፈጸሙት ሌላ ጥቃት 2 በእርሻ ሥራ ላይ የነበሩ የቀበሌው ነዋሪዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ተገድለዋል። በተመሳሳይ ሚያዚያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት አካባቢ በወረዳው ቆቦ በተባለ ቀበሌ በተፈፀመ ተጨማሪ ጥቃት ከብቶች በመጠበቅ ላይ የነበሩ 3 ሕፃናት እና አንድ በእርሻ ሥራ ላይ የነበረ ግለሰብ በድምሩ 4 ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ተመተው የተገደሉ ሲሆን ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ወንድማማቾች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። እነዚህ ታጣቂዎች በኮሬ ዞን ጎርካ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየፈጸሙ የሚገኙ ሲሆን፣ ከግድያ በተጨማሪ በአካባቢው ያሉ ከብቶችን ዘርፈው እንደሚሄዱ እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎችን የእርሻ ሥራዎችን እንዳይሰሩ እያደረጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የዘፈቀደ፣ ሕገወጥ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት
21. ኢሰመኮ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በአዋሽ 40 በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎችን ሰብአዊ መብቶች አያያዝ በሚመለከት ምልከታ አድርጎ አጠቃላይ አያያዛቸውን በሚመለከት ነሐሴ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣ መሆኑ የሚታወስ ነው። ይህንን ተከትሎ በጸጥታ አካላት ቃል በተገባው መሠረት ታሳሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ እንዲገናኙ መደረጉ እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው አማካኝነት አስፈላጊ የሆኑ አቅርቦቶች በፖሊስ እንዲወሰድላቸው መደረጉ አበረታች ቢሆንም ግለሰቦቹ የተያዙበት አካባቢ ከመኖሪያቸው ርቆ የሚገኝ ወታደራዊ የስልጠና ካምፕ በመሆኑ ለቤተሰብ ጥየቃ የማይመች መሆኑ እና በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል የተወሰኑት ካለባቸው የጤና ችግር አንጻር የአካባቢውን ከፍተኛ ሙቀት ለመቋቋም የተቸገሩ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
22. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በአዋሽ 40፣ በአዲስ አበባ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተለምዶ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ፤ በአማራ ክልል በባሕር ዳር፣ ሸዋሮቢት፣ ኮምቦልቻና ጎንደር በሚገኙ የኮማንድ ፖስቱ ማቆያ ስፍራዎች እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በርካቶች ለተራዘመና የዘፈቀደ እስራት ተዳርገዋል። የጸጥታ አካላት የማጣራት ሥራዎችን በመሥራት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለአግባብ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች እንዲለቀቁ ማድረጋቸው፣ የተወሰኑትም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጉ የሚበረታታ ቢሆንም ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በርካቶች ለወራት ከሕግ ባለሙያዎቻቸው ጋር እንዳይገኛኙ ተደርገው፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እና መብቶቻቸው ተገድበው በቁጥጥር ሥር የሚገኙ መሆኑ አሳሳቢነቱ እንደቀጠለ ነው። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አማካኝነት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ሰዎች ውስጥ ለተለያዩ የጤና ችግሮች የተጋለጡ መኖራቸውን፣ የተወሰኑትም ከሥራቸው የተሰናበቱ መሆኑን እና ቤተሰቦቻቸው ለከፍተኛ ጭንቀት የተዳረጉ መሆኑን ኢሰመኮ ለመረዳች ችሏል።
23. ከእነዚህም መካከል በላይ በቀለ ወያ የተባለ ገጣሚ ነሐሴ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ባህር ዳር ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሎ በመጀመሪያ ባህር ዳር ከተማ በሚገኝ የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ (መኮድ) ለ3 ሳምንታት በእስር ከቆየ በኋላ ወደ ባህር ዳር ማረሚያ ቤት( ሰባታሚት ) ተወስዶ ይህ መግለጫ ይፋ እሰከሆነበት ጊዜ ድረስ ለ9 ወራት በእስር ላይ ይገኛል። “የእርስ በእርስ ጦርነት ይብቃ! ሰላም ይስፈን!” በሚል መሪ ቃል ለህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲያስተባብሩ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ኃይማኖት፣ የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ አመራሮች የሆኑት አቶ ጊደና መድኅን እና አቶ ካልአዩ መሀሪ ከኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ አዋሽ አርባ በእስር ላይ ቆይተው ከሦስት ወራት እስራት በኋላ ባቀረቡት አካልን ነፃ የመውጣት ክስ መነሻነት በፍርድ ቤት በተሰጠ ትእዛዝ ከእስር የተለቀቁ ቢሆንም የቀድሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባል የሆኑት መምህር ናትናኤል መኮንን ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ አዋሽ አርባ የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ከተወሰደ በኋላ የካቲት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. የፌዴራል ፍርድ ቤት በአካል ነጻ ማውጣት ትእዛዝ ከእስር እንዲለቀቅ ቢወስንም፤ ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ ይገኛል። በተመሳሳይ ጋዜጠኛ በላይ ማናየ ህዳር 3 ቀን 2016 ዓ. ም. ተይዞ እስከ ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቆይቶ ህዳር 28 ቀን 2016 ዓ. ም. ወደ አዋሸ አርባ እንዲዛወር ተደርጎ በእስር ላይ ይገኛል። እንዲሁም ጋዜጠኛ አብነት ታምራት ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ከቢሮው በደኅንነት ሰዎች ተይዞ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተወስዶ ከሁለት ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ አዋሽ አርባ ከተዛወረ ጊዜ ጀምሮ ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ ይገኛል።
24. በአዲስ አበባ ከተማ ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው ታላቁ ሩጫ ላይ “የፖለቲካ መልእክት አስተላልፋችኋል” ተብለው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎች እስከ ሁለት ወር የሚደርስ የተለያየ ጊዜ መጠን በእስር ቆይተው በተለያየ ጊዜ ተለቀዋል። ሆኖም ግለሰቦቹ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት በቁጥጥር ሥር ያልዋሉና እስራቱም ሕገ ወጥ በመሆኑ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድና ተጠያቂነትም እንዲረጋገጥ ኢሰመኮ ጉዳዩን በመከታተል ላይ ይገኛል።
25. በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ቤት ለቤት የተደረጉ ፍተሻዎችን ተከትሎ በልዩ ልዩ በቂ ያልሆነ የሕግ ምክንያት ለምሳሌ አርማ የሌለው ባንዲራ በቤታችሁ ተገኝቷል በሚል፣ እንደ ጦር መሳሪያ የሚቆጠር አቅርቦ ማሳያ መነጽር አላችሁ በሚል፣ እና የተለያዩ ፖሊስ “አጠራጣሪ ያላቸው ነገሮች” ተገኝተውባቸዋል ያላቸውን ሰዎች በዘፈቀደ በቁጥጥር ሥር በማዋል በበርካታ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ እጅግ አላስፈላጊ እንግልትና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ደርሷል።
26. በማእከላዊ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ከተለያዩ ክሰተቶች ጋር በተያያዘ ተገቢ የሆኑ የሕግ ሂደቶችን ያልተከተሉ የተስፋፉ እስሮች ተፈፅመዋል። ከጥቅምት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር እና በቀቤና ልዩ ወረዳ በአካባቢው ተፈጥሮ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ፣ በምሥራቅ መስቃን እና በማረቆ ወረዳ አካባቢ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተገናኘ እንዲሁም በሀድያ ዞን በምሥራቅ ባዳዋቾ እና በከምባታ ዞን በማኅበራዊ ሚዲያ ሀሰተኛ መረጃ በማስተላለፍ እና የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት በሚል የተጠረጠሩ ቢያንስ 244 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በራስ ዋስትና እንዲፈቱ የተደረጉ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተያዙ መሆናቸውንና በሕግ በተቀመጠው መሠረት በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ መሆናቸውን በተደረገ ክትትል ማወቅ ተችሏል።
27. መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በከምባታ ዞን ሀደሮ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፊትለፊት፣ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በከምባታ ዞን ሀደሮ ከተማ አስተዳደር የሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ ምክር ቤት አፈጉባኤ መኖሪያ ቤት ፊት ለፊት እንዲሁም ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በከምባታ ዞን በሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ 01 ቀበሌ በአንድ የግለሰብ ምግብ ቤት ውስጥ ቦምብ ተጥሎ መፈንዳቱን ተከትሎ እንዲሁም ከዶንጋ ማኅበረሰብ የማንነት እና የመዋቅር ጥያቄ ጋር በተያያዘ የከምባታ ዞን እና የሀደሮ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ በአካባቢው ሁከት እንዲፈጠር አድርገዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ቢያንስ 75 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውለዋል። ተጠርጣሪዎች መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ ሚያዝያ 3 ቀን እና ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ሲሆን ሁሉም ተጠርጣሪዎች ከሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ባሉት በተለያዩ ቀናት በፍርድ ቤት ትእዛዝ በዋስ ተፈተዋል። ኢሰመኮ በአካባቢው በአካል በመገኘት ባደረገው ክትትል ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከል የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች ድብደባ የተፈፀመባቸው መሆኑን እንዲሁም በአካባቢው በነዋሪዎች እና በጸጥታ አካላት መካከል ተከስቶ በነበረው ግጭት ወቅት በፖሊስ በተወሰደ የኃይል እርምጃ 3 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ ተረድቷል።
28. በጋሞ ዞን በሦሰቱ የቁጫ መዋቅሮች ከፖሊስ ተቋማት ውጭ በሆኑ አካላት የሚፈፀሙ እስሮች እና ተጠርጣሪዎችን ከመደበኛ የማቆያ ስፍራ ውጭ የማቆየት ተግባር መቀጠሉን ኢሰመኮ ያሰባበሰባቸው መረጃዎች ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጫ ወረዳ ውዛቴ ቀበሌ ውስጥ የቀበሌው ሊቀመንበር 10 የቀበሌው ነዋሪዎችን የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊ በመሆን የልማት ሥራ ላይ አልተሳተፉም በሚል ምክንያት በቀበሌው በሚገኘው የበደና ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንዲቆዩ ማድረጉን እና በሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ተጠርጣሪዎቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ደጋፊ መሆን አለመሆናቸውን በቀበሌው ሕዝብ ፊት በአውጫጭኝ ለመለየት አስገዳጅ የሕዝብ ስብሰባ የጠራ ቢሆንም በዕለቱ በአከባቢው በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያትት ለአውጫጭኝ የተጠራ ስብሰባ ለሌላ ጊዜ ተላልፎ ሰዎቹ እንደገና በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንዲቆዩ መደረጋቸውን ኢሰመኮ ተረድቷል።
እገታ
29. በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን አካባቢ በታጣቂዎች የታገቱ ሰዎች ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በእገታ ላይ ሲሆኑ፤ የሰዎቹን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ዝርዝር ሁኔታው በዚህ ሪፖረት አልተገለጸም።
30. የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ በሰሜን አቸፈር ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ሱፐርቫይዘር፣ ርዕሰ መምህር እና ሌሎች መምህራን በወረዳው ትምህርት ለማስጀመር መስክ ወጥተው ወደ ወረዳው ዋና ከተማ ሊበን ሲመለሱ መንገድ ላይ በታጣቂ ኃይሎች (በተለምዶ ፋኖ) ተይዘው ለሦስት ቀን በእገታና በእንግልት ከቆዩ በኋላ “የብልጽግናን ዓላማ ለማራመድ ሁለተኛ እንዳትመጡ” በሚል ማስፈራሪያ የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለቀዋል።
31. የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሌ እና ጋርዱላ ከተባሉ ሁለት ዞኖች የቀን ሠራተኞች ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዞ በሚያደርጉበት ጊዜ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ፈንድቃ አካባቢ ሲደርሱ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች (በተለምዶ ፋኖ) ለቀን ሥራ የምትሄዱ ሳይሆን ምልምል ወታደር ናችሁ በሚል ምክንያት 274 ሠራተኞች፤ 4 ሹፊሮች፤ 4 ረዳቶች እና 2 አስተባባሪዎች ታግተው የነበረ መሆኑን፤ በመጀመሪያ መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. 4 ሹፊሮች፤ 4 ረዳቶች እና 2 አስተባባሪዎች የተለቀቁ መሆኑን ቀጥሎም የተቀሩት ሁሉም ታጋቾች መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የሠራተኞቹ ድርጅት ከአጋቾች ጋር ባደረገው ድርድርና የገንዘብ ክፍያ ጭምር የተለቀቁ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
32. መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ገደማ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት የሆኑትን ዶ/ር ንጉስ ታደሰን ደብረ ብርሃን ከተማ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በታጣቂ ኃይሎች (በተለምዶ ፋኖ) ተይዘው እንደተወሰዱ እና በቅርቡ ከእገታው እንደተለቀቁ ኢሰመኮ ለማወቅ ችሏል።
33. ጥር 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ቡድኖች ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ወደ ማእከላዊ ሲዳማ ዞንሎኮ አባያ ወረዳ ቡኪቶ ቡራ ቀበሌ በመግባት ሁለት የቀበሌው ነዋሪዎችን አግተው በመውሰድ የታጋች ቤተሰቦች የማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፍሏቸው በመጠየቅ እስከ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ አቆይተው ገንዘቡ ከተከፈላቸው በኋላ ግለሰቦቹን መልቀቃቸውን ማወቅ ተችሏል። በአካባቢው የሚፈጸመው ሰዎችን ለገንዘብ የማገት ድርጊት ተደጋጋሚ እና ላለፉት የተወሰኑ ዓመታት የቆየ እንደሆነ መረዳት ተችሏል። የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በወቅቱ ችግሩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን እና ተጨማሪ ኃይል በአካባቢው ማሰማራት አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሰ ቢሆንም ተጨማሪ ኃይል ባለመመደቡ እና ከኦሮሚያ ክልል የሚገቡት ታጣቂዎች የሚታጠቁት መሳሪያ ከወረዳ ፖሊስ አቅም በላይ በመሆኑ ችግሩን መከላከል አለመቻሉን ገልጸዋል። ወረዳው ለክልሉ መንግሥት ተጨማሪ ኃይል እንዲመደብ የጠየቀ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
34. የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ወንጂ ከተማ ዶዶታ ተብሎ የሚጠራ አካባቢ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) ታጣቂዎች በቀለ ጥሩነህ፣ ተሾመ ሔራም፣ ያለው ተመስገን፣ ካሚል አብዱራህማን እና ግርማ በላቸው የተባሉ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞችን ከሥራ ቦታቸው ላይ አግተው በመውሰድ ታጋቾችን ለመልቀቅ ለእያንዳንዳቸው 75 ሺ ብር እንዲከፈል በመጠየቃቸው የታጋቾች ቤተሰቦች ገንዘቡን በማሰባሰብ ክፍያውን ለመፈጸም ሲሞክሩ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ለወንጀል ሥራ መተባበር የለባችሁም በሚል ተከልክለዋል። ሆኖም ይህንን ተከትሎ ታጋቾቹ በሙሉ ተገድለው አስክሬናቸው መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዳማ ወረዳ ልዩ ስሙ ኡሞ ፈጫሳ የሚባል ቦታ ተጥለው ተገኝተዋል።
35. የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ”) መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ ቆታ ከተማ ላይ በፈጸመው ጥቃት ከዚህ በላይ ከተገለጸው የ31 ሲቪል ሰዎች ግድያና የ3 ሰዎች አካል ጉዳት በተጨማሪ 6 ሰዎችን አግቶ ወስዷል። በተጨማሪም ታጣቂ ቡድኑ ሚያዝያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በወረዳው ደራ ቲርቲሪ ቀበሌ 27 እንዲሁም ሚያዚያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በጎምንቦሬ አሊይ ቀበሌ 15 ሰዎችን አግቶ ወስዷል።
አስገድዶ መሰወር እና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ አስሮ ማቆየት
36. ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ኢሰመኮ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ከተወሰዱ በኋላ ያሉበትን ቦታ ሳይታወቅ የቆዩ ሰዎችን በተመለከተ የቀረቡለትን 42 ሰዎችን የተመለከቱ አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ በአደረገው ምርመራ እና ክትትል የጠፉት ሰዎች በመደበኛ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ስፍራ እንዳልነበሩ ተገንዝቧል።
37. ከእነዚህ ክስተቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ ድርጊቶች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በግዳጅ የተወሰዱና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የታሰሩ እና/ወይም የአስገድዶ መሰወርን ድርጊት የሚያቋቁሙ ናቸው። በዚህ መልክ ከተሰወሩ ሰዎች ውስጥ 31 ሰዎች ከአስራ ስምንት ቀናት እስከ ሁለት ወር ተኩል ድረስ ተገደው ከተሰወሩ በኋላ የተለቀቁ ሲሆን 11 ሰዎች ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በግዳጅ እንደተሰወሩ ቀጥለዋል። ከተለቀቁት ሰዎች ውስጥ አምስቱ ዓይናቸውን በጨርቅ ተሸፍነው በመወሰዳቸው የነበሩበትን ቦታ አያውቁም። በማይታወቅ ቦታ ተይዘው የነበሩ ሰዎች ለምርመራ እየተጠየቁ በጨለማ ክፍሎች ቆይተዋል፣ ዳቦ ይሰጣቸው እና ሽንት ቤት በተወሰነ ሰዓት እንዲጠቀሙ ይፈቀድላቸው የነበረ ቢሆንም የተሟላ ምግብ እና ማናቸውም አገልግሎት አልነበረም።
38. ወቅታዊ ጉዳይ በሚል በኦሮሚያ ፖሊስ ቢሾፍቱ ከተማ ባቡጋያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የፖሊስ ካምፕ በቁጥጥር ሥር ውሎ እንደነበር የተገለጸ አቶ ስማቸው አለማየሁ የተባለ የአዲስ አበባ ነዋሪ ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር በዋለበት ወቅት ተይዞበት የነበረውን ስልክ ለመቀበል ወደ ኦሮሚያ ኮሚሽን በሄደበት ወቅት ከፖሊሶች ጋር አለመግባባት መፈጠሩን እና በቁጥጥር ሥር መዋሉን ለጓደኞቹ ከነገራቸው በኋላ ስልኩ የተዘጋ ሲሆን የትና በምን ሁኔታ እንዳለ ለማወቅ አልተቻለም።
39. መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 1፡45 ሰዓት አካባቢ በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ስድስት ኪሎ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ባለው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ማንነታቸው ያልታወቁ 2 ግለሰቦች ታርጋ በሌለው ሚኒባስ መኪና ጆን ተሻገር የተባለውን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ አስገድደው ከወሰዱበት ጊዜ ጀምሮ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ቀን ድረስ ተማሪ ጆን ተሻገር የት እንደተሰወረ ማወቅ አልተቻለም።
40. የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. የአማራ ክልል ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ሀብታሙ በላይነህ መኮንን ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ከአዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን ኢሰመኮ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎችን ያነጋገረ ቢሆንም ግለሰቡ በሁለቱም ኮሚሽን ማቆያዎች ውስጥ እንደማይገኙ ፖሊስ ለኢሰመኮ አረጋግጧል። ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ አቶ ሀብታሙ በላይነህ የት እንዳሉ አይታወቅም።
የሀገር ውስጥ መፈናቀል
41. የትግራይ ታጣቂ ቡድኖች ወደ አላማጣ እና በኮረም ከተማ አስተዳደሮች፣ በራያ አላማጣ፣ ዛታ እና ኦፍላ ወረዳዎች መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ከሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች በደኅንነት ሥጋት ሳቢያ ከመኖሪያቸው እንደተፈናቀሉ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም ገጠራማ ቀበሌዎች በታጠቁ ኃይሎች የንብረት ዘረፋ እና ውድመት መፈፀሙን ለመረዳት ተችሏል። ተፈናቃዮች በሰሜን ወሎ እና በዋግ ኽምራ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ ለመስጠት በመንግሥት፣ በተራድዖ ደርጅቶች እና በአካባቢው ማኅበረሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን መረዳት ተችሏል። እስከ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰሜን ወሎ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና 39,000 ተፈናቃዮች እንዲሁም በዋግ ኽምራ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ከ8,000 በላይ ተፈናቃዮች ተመዝግበዋል። የፌደራል መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወደ አላማጣ ከተማ አስተዳደር መግባታቸውን ተከትሎ በከተማው የጸጥታ ሁኔታ የተሻለ ነው በሚል ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኃላፊዎች አስረድተዋል።
ምክረ ሐሳቦች
42. ኢሰመኮ ከዚህ በፊት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምና በአሮሚያና አማራ ክልሎች ከቀጠሉ የትጥቅ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ይፋ ባደረጋቸው መግለጫዎችና የክትትል ሪፖርቶች የተካተቱና በከፊል ወይም በሙሉ ተፈጻሚ ያልሆኑ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ እያሳሰበ በተለይም፦
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (2) በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁን የመተግበር ሂደት ሥልጣንን አላግባብ ለመጠቀም እና ከሕግ አግባብ ውጭ የሆኑ የጅምላ እስሮችን፣ ግድያዎችን ኢሰብአዊ አያያዝን እንዲሁም ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመፈጸም ክፍት እንዳይሆን ተገቢውን ጥንቃቄ እና የመከላከልና የማስተካከያ ሥራ እንዲሠራ፣ እንዲሁም ተገቢው የሕግ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲሰፍን፤
- በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ፤ በማናቸውም የግጭት ሂደት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰትን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ፣ በግጭቱ የሚፈጸም ጥሰትን በይፋ እንዲያወግዙ እና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፤ እንዲሁም በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ሰብአዊ መብቶችን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ፤ በሲቪል ሰዎች ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ፣
- መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልል በመካሄድ ላይ በሚገኘው የትጥቅ ግጭት፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ኃላፊዎችን እና አባላትን እንዲሁም የታጣቂ ቡድኖች አባሎች ተጠያቂ ለማድረግ ተዓማኒ እና የሰብአዊ መብቶች ደረጃን የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት እንዲጀመር፤ እንዲሁም በግጭቱ በሰው ሕይወት፣ በአካል፣ በሥነ-ልቦና እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በማጣራት ተጎጂዎች እንዲካሱ እና መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲደረግ፣
- ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ከተያዙት እጅግ ብዙ ታሳሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ ቢለቀቁም አሁንም በርካቶች በእስር ላይ ይገኛሉ። በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለተራዘመ ቅድመ ክስ እስር መዳረግ የሰብአዊ መብቶች መርሖችን የሚጥስ በመሆኑ ተዓማኒ ክስ ያልቀረበባቸው ታሳሪዎች እንዲሁም በማስገደድ የተሰወሩና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ከእስር እንዲለቀቁ፣ የመንግሥት የጸጥታና የአስተዳደር አካላት በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ግለሰቦችን በመደበኛ ማቆያዎች ብቻ እንዲይዙና ሁልጊዜም የተያዙ ሰዎች ያሉበት ቦታና ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው እንዲገለጽ፣
- በተለያየ ቦታዎች ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ እና አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብ፣ ሁሉም ተፈናቃዮች ወደ ቄያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች እንዲሁም ለመፈናቀል ምክንያት የሆነው የጸጥታ ሥጋት ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ኢሰመኮ ያሳስባል።