የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝን የተመለከተ ባለ 40 ገጽ የክትትል ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። ይህ የክትትል ሪፖርት የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ከአቤቱታ አቀራረብ ሥርዓት ጀምሮ፣ በምርመራ ሂደት፣ በክስ አቀራረብና አሰማም እንዲሁም በፍርድ ወቅት ያሏቸው የመብቶች አያያዝ በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ሀገር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች ከተጠበቁላቸው ሰብአዊ መብቶች መስፈርቶች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን በመፈተሽ አንኳር ግኝቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን የያዘ ነው።
ኢሰመኮ ሪፖርቱን ለማዘጋጀት ከሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በሰባት ክፍለ ከተሞች እና በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደር፣ በቡራዩ እና ሰበታ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን፣ ጅማ ከተማ እና ሸቤ ሶምቦ አዋሳኝ ወረዳ፣ በሐረሪ ክልል በሐረር ከተማ እና በኤረር አዋሳኝ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ 24 ዳኞች፣ 18 ዐቃቤያነ ሕግ፣ 23 ፖሊሶች፣ 8 የተቀናጀ የአንድ ማእከል ባለሙያዎች፣ 4 የመጠለያ ተቋማት ባለሙያዎች፣ 3 በፍርድ ቤት ከሚገኙ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች እና ከ22 የጥቃት ተጎጂዎች መረጃና ማስረጃዎችን ሰብስቧል።
የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት በሚያልፉበት ጊዜ በዓለም አቀፍ እና በአህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች የተጠበቁላቸውን ፍትሕ የማግኘት፣ ክብርን እና ምስጢራዊነትን በጠበቀ የፍትሕ ሥርዓት የመስተናገድ፣ ከሁለተኛ ደረጃ ጥቃት (secondary victimization) የመጠበቅ፣ የተፋጠነ ፍትሕ እና ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት፣ የመሰማት እና የደኅንነት ጥበቃና ድጋፍ የማግኘት መብቶች በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንደማይደረጉ ለማወቅ ተችሏል።
ለዚህም ምክንያት ከሆኑት ውስጥ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን አስመልክቶ ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚችሉ የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ደንቦችን አለማካተቱ፤ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከመደበኛው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ውጪ ተጎጂ ለሆኑ ሴቶችና ሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝን የተመለከተ አስገዳጅና ወጥ የሥነ ሥርዓት መመሪያ/ፕሮቶኮል አለመኖሩ፤ የጥቃት ተጎጂ ለሆኑ ሴቶችና ሕፃናት የመጠለያ፣ የማገገሚያ፣ ሕክምና እና የሥነ ልቦና አገልግሎትን ማግኘት የሚያስችሉ መፍትሔዎች በሕግ አለመደንገጉ እንዲሁም የተቀናጀ የአንድ ማእከል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተቀመጠላቸው የአሠራር ሥርዓት ማኑዋል መሠረት አለመሥራታቸው መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
መንግሥት አግባብነት ባላቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች እና በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ መሠረት የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናትን የተለየ አያያዝ የሚመለከት ግልጽ የሕግ ማዕቀፍ እንዲያወጣ፤ አግባብነት ያላቸው ስልጠናዎች ለሕግ አስከባሪና ለድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች የሚሰጡበት ወጥ ሥርዓት እንዲዘረጋ፤ የወንጀል ምርመራ የሚጠናቀቅበት እና በጉዳዩ ላይ ክስ ማቅረብ የሚቻልበት የጊዜ ገደብ እንዲቀመጥ ሪፖርቱ ዝርዝር ምክረ ሐሳብ አቅርቧል። ተጎጂዎች ካሳን ጨምሮ ውጤታማ መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያስችሉ የአሠራር ሥርዓቶች እንዲዘረጉ፣ የተቀናጀ የአንድ ማእከል ተቋማት ኢኮኖሚያዊ ተደራሽነት ችግርን ለመቅረፍ አገልግሎቶቹ በቅርበት በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች እንዲሰጡ እና በተቀናጀ የአንድ ማእከል ተቋማት የዐቃቤ ሕግ እና የፖሊስ የሥራ ክፍሎች አገልግሎት በድጋሜ እንዲጀምሩ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ “በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት መብቶችን አያያዝ ለማሻሻል እንዲሁም የጥቃት ፈጻሚዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ሁሉም የፍትሕ አካላት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንዲሁም በሪፖርቱ የተሰጡትን ምክረ ሐሳቦች ሊፈጽሙ ይገባል” ብለዋል።