የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት መብቶች አያያዝን በተመለከተ በ2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ ባደረገው የክትትል ሪፖርት የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አተገባበር ዙሪያ ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የጤና ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተቋማት፣ በሴቶችና እና በሕፃናት መብቶች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ከአፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ እና ሶማሊ፣ ክልሎች እና ከሸገር ከተማ አስተዳድር የተውጣጡ አቻ ተቋማት ተሳትፈዋል።

የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትሉ ከታኀሣሥ 16 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. እንዲሁም ከየካቲት 2 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን የሴቶች እና የሕፃናት ጥቃት ወንጀል ድርጊቶችን ከሚመለከቱ የፍርድ ቤቶች የውሳኔ መዝገቦች፣ የፖሊስ ምርመራ ፋይሎች እንዲሁም በፍትሕ ሥርዓቱ ካለፉ የጥቃት ተጎጂዎች የተሰበሰቡ የቃል እና የጽሑፍ ማስረጃዎችና መረጃዎች ደግሞ በመጀመሪያው ክትትል የተለዩ ግኝቶችን ይበልጥ ማጠናከር ላይ መሠረት ያደረገ ነው።


በውይይቱ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት ከአቤቱታ አቀራረብ ጀምሮ በምርመራ ሂደት፣ በክስ አቀራረብ እንዲሁም በችሎት ሂደት በዓለም አቀፍ፣ በአህጉራዊ እና በሀገራዊ ሕጎች የተጠበቁላቸው መብቶች፣ ተግባራዊ ያልተደረጉ ምክረ ሐሳቦች እና በመጀመሪያው የክትትል ሥራ የተለዩ እና የቀጠሉ አሳሳቢ ጉዳዮች ምክክር ተደርጎባቸዋል። በመጀመሪያው ክትትል የተጎጂዎች ፍትሕ የማግኘት መብት፣ የፍትሕ እና የድጋፍ ሰጪ ተቋማት ኢኮኖሚያዊ ተደራሽነት (Economic Accessibility)፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆን፣ የቋንቋ እና የመረጃ ተደራሽነት፤ ክብርን በጠበቀ እና ለዳግም ጥቃት በማያጋልጥ መልኩ የመስተናገድ፣ ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ የፍትሕ አገልግሎት፣ የደኅንነት ጥበቃ፣ የመሰማት ወይም የመሳተፍ፣ የተፋጠነ ፍትሕ እና ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት እንዲሁም የድጋፍ አገልግሎት የማግኘት መብቶቻቸው በተሟላ ሁኔታ የማይተገበሩ መሆናቸው ከተለዩ ግኝቶች መካከል ተጠቅሰዋል።


በተጨማሪም የወንጀል ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ረቂቅ ሕግ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ስለሚኖራቸው የተለየ የመብት አያያዝ እንደሚደነግግ የሚጠበቅ ቢሆንም የምክረ ሐሳብ አተገባበር ክትትል እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ ረቂቅ ሕጉ ባለመጽደቁ ነባሩ አሠራር መቀጠሉ፣ የዐቃቤ ሕግ እና የፖሊስ የሥራ ክፍሎች የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አለመጀመራቸው፣ በሥራ ላይ ያሉት የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተቋማት በአሠራር ማኑዋላቸው መሠረት አለመሥራታቸው እና የመጠለያ ተቋማት አለመስፋፋታቸው በምክረ ሐሳብ አፈጻጸም ክትትል በአሳሳቢነት የተለዩ ግኝቶች ናቸው።


የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ረቂቅ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ ሳይጸድቅ መዘግየት በጥቃት ተጎጂዎች መብቶች አያያዝ ላይ እክል መሆኑን ጠቅሰው በሥራ ላይ ያሉትን የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተቋማት የቅብብሎሽ ሥርዓት ማጠናከር እና በአሠራር ማኑዋል መሠረት እንዲሠሩ ማስቻል የተጎጂዎች መብቶች አያያዝን የተሻለ ለማድረግ እንደሚረዳ በአጽንዖት ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ አብዛኛው የጥቃት ወንጀሎች ሪፖርት እንደማይደረጉ ገልጸው “ፍትሕን ፍለጋ ሪፖርት ያደረጉ ውስን የጥቃት ተጎጂዎች በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ የሕግ እና የአሠራር ክፍተቶች የተነሳ ለተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መጋለጣቸው ተጎጂዎች የደረሰባቸውን ጥቃት እንዳያመለክቱ እንዲሁም የጥቃት ወንጀሎች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል።” ብለዋል። በመጨረሻም የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት መብቶች አያያዝን ለማሻሻል ሁሉም የፍትሕ አካላት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።