የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራት ላይ ሚያዝያ 15 እና 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ብሔራዊ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። የብሔራዊ ኮንፈረንሱ ዓላማ በፍትሕ ሥርዓቱ በተለይ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሂደት የሚሰጥ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በነባራዊ ጉዳዮች እና በሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትብብርና በቅንጅት ለመፍታት የጋራ መወያያ መድረክ መፍጠር ነው።






በኮንፈረንሱ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት፣ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የፍትሕ ቢሮና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሕግ ትምህርት ቤቶች ተወካዮች እና የሲቪል ማኅበራት እና የግል የጥብቅና ተቋማት ተሳትፈዋል። እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት የመድኃኒትና የወንጀል ጽሕፈት ቤት፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም፣ የዳኒሽ ሰብአዊ መብቶች ተቋም (DIHR) የአዲስ አበባ እና የዛምቢያ ቢሮ ተወካዮች እና የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ተሳታፊ ሆነዋል።




በኮንፈረንሱ በሀገሪቱ ያለውን ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ሕጎችና መመዘኛዎች የተቀመጡ ድንጋጌዎች ላይ ገለጻ እና በሕግ ድጋፍ አገልግሎት አቅርቦት ላይ የአፍሪካ ሀገራት መልካም ተሞክሮዎች፣ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ አደረጃጀትና መሠረታዊ ይዘት ለውይይት ቀርበዋል። ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በመስጠት ልምድ ያካበቱ የሲቪል ማኅበራት መልካም ተሞክሮዎቻቸውን አጋርተዋል። ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አስተዳደርና ተቋማዊ ማዕቀፍ፣ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ወሰን፣ የተጠቃሚና አቅራቢ መለያ መስፈርቶች፣ የአገልግሎቱ ዘላቂነት፣ ጥራት፣ ተደራሽነት፣ ቁጥጥር፣ የቅንጅት ሥራ/ማስተባበር እና የቅብብሎሽ ሥርዓትን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲ መምህራን የፓናል ውይይት ተደርጓል። በኮንፈረንሱ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምሕርት ቤት ተወካዮች በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ ሥራዎቻቸውን በተለይም የሕትመት ወጤቶችን አቅርበዋል።






የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ጥያቄዎችን እና ኢሰመኮ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ የውትወታ ሥራ ሊሠራባቸው ይገባል ያሏቸውን ጠቃሚ ሐሳቦችን አቅርበዋል። በተጨማሪም በኢሰመኮ አስተባባሪነት የድርጊት መርኃ ግብር የሚያዘጋጅ ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታዊ ተቋማት እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጣ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ከዓለም አቀፍ የልማት አጋር ድርጅቶች የመጡ ተሳታፊዎች ለኮሚቴው የቴክኒካል ድጋፍ እንዲሰጡ ከስምምነት ተደርሷል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት፣ ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር በላይሁን ይርጋ ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ለማስፋፋት ያወጣውን ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ረቂቅ ሕግ፣ ደንብ እና መመሪያዎች ማዘጋጀቱን እና በብሔራዊ ኮንፈረንሱ የሚነሱ ነጥቦች በነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ላይ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ ለማዳበር ግብአት እንደሚሆኑ ገልጸዋል።


የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ባስተላለፉት መልእክት ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ፍትሐዊ የፍትሕ ሥርዓት ከሚገለጽበት እና ሰብአዊ መብቶች ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች አንዱ መሆኑን አስታውሰው “ጥራቱ የተጠበቀ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ለተወሰኑ ተቋማት ብቻ የሚተው ኃላፊነት ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት ነው” ብለዋል። አክለውም የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱ ተደራሽ እና ውጤታማ እንዲሆን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሠራ እንዲሁም ወቅታዊ በሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ሀገራዊና ውጤት ተኮር የውትወታ መድረኮች ማዘጋጀቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።