የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ተማሪዎች የተረቀቀውን የግብረገብ ትምህርት መማሪያ (ከሪኩለም) ለሚገመግሙ ባለሙያዎች በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያተኮረ ስልጠና ግንቦት 29 እና 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ አዘጋጀ።
ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአፋር፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ሲዳማ፣ ሶማሌ እና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች፣ ከመንግሥትና ከግል ትምህርት ቤት እና ከኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ተቋማት ኅብረት ተወካዮች በስልጠናው ተሳትፈዋል። በተጨማሪም የግብረገብ ትምህርት መጻሕፍትን ያረቀቁ የባሕር ዳር፣ ሃዋሳ፣ ጅማ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የስልጠናው አካል ነበሩ።
ስልጠናው በሰኔ ወር መጀመሪያ በሚካሄደው የውይይት መድረክ፣ ከ1ኛ-6ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚማሩባቸው እና በትምህርት ሚኒስቴር በተቀጠሩ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በተረቀቁት የግብረገብ መጻሕፍት ላይ አስተያየት የሚሰጡ ተሳታፊዎች ከሰብአዊ መብቶች አንጻር አስተያየት ለመስጠትና ለመገምገም እንዲችሉ አቅም ለመፍጠር ያለመ ነው። በተጨማሪም ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት ለሚያደርገው ጥረት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል የሚያግዝ ነው።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት የቆየው ስልጠና የተለያዩ ግን ተዛማጅ ሦስት አበይት ክፍሎች ተከፍሎ ለሰልጣኞች ቀርቧል። ስለ ሰብአዊ መብቶች ምንነት፣ ባሕሪያት እና እሴቶች በመጀመሪያው ክፍል የተዳሰሱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ክፍል የግብረገብ እና የሰብአዊ መብቶች እሴቶች ምንነት፣ ግቦች፣ ተዛማጅነትና ተደጋጋፊነት ላይ ያተኮረ ነበር። አሳታፊ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ዘዴ እና ክህሎት ለግብረገብ ትምህርት አሰጣጥ ያለውን ጠቀሜታ ተገባራዊነት በመጨረሻው ክፍል ተዋውቀዋል ።
የስልጣናው ተሳታፊዎች የግብረገብ ትምህርት መጻሕፍትን ለመገምገም የሚያስችል አዳዲስ ግንዛቤዎችን እና መረጃዎችን ለማግኘት እንደቻሉ የተናገሩ ሲሆን፤ የተማሪዎችን እውቀት፣ አመለካከት እና ችሎታ ለማሳደግ እና ወደፊትም ተማሪን ያማከለ ዘዴን ለመጠቀም ያላቸውን ተነሳሽነት ገልጸዋል። አክለውም የኢሰመኮ እና ትምህርት ሚኒስቴር በትብብር መስራታቸው አበረታች ጅማሮ መሆኑን ገልጸው ለወደፊቱ መጻሕፍት ከመረቀቃቸው ቀደም ብሎ ይህን መሰል ስልጠናዎች ቢዘጋጁ ውጤቱ የላቀ እንደሚሆን አመላክተዋል።
በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያሰሙት የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጂብሪል፣ “ሰብአዊ መብቶችን መሰረት ያደረገ ትምህርት በሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ እንዲካተት የማድረግ ጥረት የአትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ሀገር አቀፍ ደረጃ ከተገባው ግዴታ ጋር የሚያያዝ ነው” ብለዋል። በሂደት በሀገራችን ውስጥ ሰብአዊ መብቶችን ባሕሉ ያደረገ ዜጋ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አክለው ገልጸዋል፡፡