የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል በሚገኙ 4 ማረሚያ ቤቶች፣ 15 ፖሊስ ጣቢያዎች እና 5 መደበኛ ያልሆኑ ማቆያዎች ላይ በ2016 በጀት ዓመት ባከናወነው የተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትል ግኝቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የጋምቤላ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የአራቱም ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊዎች፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የክልሉ ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትሕ እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የፍትሕ ቢሮ ተወካዮች፣ የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋምቤላ ቅርንጫፍ የወንጀል ምርመራ አስተባባሪዎች፣ በክልሉ የሚገኙ የፖሊስ መምሪያ እና ፖሊስ ጣቢያ አዛዦች እንዲሁም በክልል እና በዞን ደረጃ የሚገኙ የፍትሕ አካላት ተወካዮች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
በውይይት መድረኩ በፖሊስ ጣቢያዎች እና መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ሥፍራዎች ተጠርጣሪዎች በሕግ ሥልጣን በተሰጣቸው አካላት ብቻ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው፣ የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች እና ታራሚዎች በፍርድ ቤት ትእዛዝ ወይም ውሳኔ ብቻ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገቡ መደረጋቸው፣ በሁሉም ማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች የመጎብኘት መብት ላይ ገደብ አለመጣሉ፣ የእምነት ነጻነት መከበሩ፣ ተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች በግዳጅ ሥራ ላይ አለመሠማራታቸው በክትትሉ በመልካም እመርታነት ከተለዩት መካከል መሆናቸው ተነስቷል። በተመሳሳይ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲገቡ የማይፈቀዱ የተጠርጣሪና የታራሚ ንብረቶች በአግባቡ ተመዝግበው መያዛችው፣ በተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች ያሉ ፖሊሶች ከተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት መልካምና ሰብአዊነትን መሠረት ያደረገ መሆኑ፣ በማጃንግ ብሔረሰብ ዞን ማረሚያ ቤት ተጨማሪ የታራሚ ክፍሎች መገንባታቸው እና በዋንቱዋ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ የመጸዳጃ ቤት ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጉ በክትትል ሪፖርቱ የተለዩ አወንታዊ ለውጦች መሆናቸውም ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል በማረሚያ ቤቶች ለቀለብ የተመደበው በጀት ከወቅታዊ የገበያ ሁኔታ ጋር የማይመጣጠን መሆኑ፣ በተወሰኑ ማረሚያ ቤቶች የውሃ አቅርቦት አለመኖር እና በቂ የሕክምና አገልግሎት አለመሰጠቱ በተግዳሮትነት ተጠቅሷል። በተመሳሳይ በፖሊስ ጣቢያዎች በመንግሥት የሚሰጥ የሕክምና እና የምግብ አገልግሎት አለመኖሩ፣ በተወሰኑ የተጠርጣሪ ማቆያዎች የሴቶች ማደሪያ ክፍሎች የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው መሆናቸው፣ ሕገ ወጥ እና የዘፈቀደ እስራት የሚፈጸም መሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው፣ ለረጅም ጊዜ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በጊዜ ቀጠሮ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸው እና የተራዘመ ቅድመ ክስ እስራት የሚስተዋል መሆኑ በአሳሳቢ ጉዳይነት ተገልጸዋል።
በማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች የቅሬታ ማቅረቢያና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደረግ የተለየ እንክብካቤና ድጋፍ አለመኖር፣ በአብዛኛው ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች ያሉ ማደሪያ ክፍሎች የተጨናነቁ፣ ከፍተኛ የንጽሕና ጉድለት ያለባቸው እና ለመኝታ አገልግሎት የሚያስፋልጉ ቁሳቁሶች የሌሏቸው መሆኑ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንደሆኑ በክትትል ሪፖርቱ ተገልጿል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል የተለዩ የመብት ጥሰቶች እና አሳሳቢ ጉዳዮች የሚቀበሏቸው መሆኑን ጠቅሰው በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው የፍትሕና የአስተዳደር አካላት የቀረቡትን ምክረ ሐሳቦች ለመተግበር ትኩረት በመስጠት መሥራት እንዳለባቸው ሐሳብ ሰጥተዋል። በሚመሯቸው ተቋማት በኩልም የተጠርጣሪዎችና የታራሚዎች መብቶች እንዲጠበቁና እንዲከበሩ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ዶ/ር አለሙ ምሕረቱ በክትትል ሪፖርቱ የተለዩ አወንታዊ ለውጦች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፤ ትኩረት የሚሹና ተጨማሪ ሀብት ሳይጠይቁ የአሠራር ለውጥ በማድረግ ብቻ ሊፈቱ የሚችሉ የመብቶች ጥሰቶች ላይ አፋጣኝ እርማት እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡ አክለውም በማቆያዎች እና ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ያለውን መጨናነቅ እና አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ/አያያዝ ለማሻሻል የአማራጭ ቅጣቶችን ጨምሮ ሌሎች የፖሊሲ አማራጮች መተግበርን እና በየደረጃው የሚገኙ የፍትሕ አካላት ተቀናጅተው መሥራትን እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።