የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል በሚገኙ 4 ማረሚያ ቤቶች፣ 21 ፖሊስ ጣቢያዎች እና 5 ኢ-መደበኛ ማቆያዎች ላይ ባከናወነው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትል የተለዩ ግኝቶች ላይ ሰኔ 20 እና 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የክልሉ ምክር ቤት የፍትሕ እና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን እና የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋምቤላ ቅርንጫፍ ተወካዮችን ጨመሮ በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ የፍትሕ፣ የጸጥታ እና የአስተዳደር አካላት የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።


በውይይት መድረኩ ታራሚዎች እና የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች በፍርድ ቤት ትእዛዝ ወይም ውሳኔ ብቻ ወደ ማረሚያ ቤት እንደሚገቡ፣ ተጠርጣሪዎች በሕግ ሥልጣን በተሰጣቸው አካላት ብቻ በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉ፣ በማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች የመጎብኘት መብት ላይ የሚጣል ገደብ አለመኖሩ፣ የእምነት ነጻነት መከበሩ፣ ተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች በግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ አለመደርጉ፣ በፍርድ ቤት የተፈቀደ ዋስትና በፖሊስ ጣቢያዎች መከበሩ፣ እንዲሁም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ የተያዙበት ምክንያት የሚገለጽላቸው መሆኑ በክትትሉ በመልካም እመርታነት ከተለዩት መካከል መሆናቸው ተነስቷል። በተመሳሳይ በማጃንግ ብሔረሰብ ዞን ማረሚያ ቤት የንጹሕ መጠጥ ውሃ አገልግሎት አቅርቦት መጀመሩ፣ በጎደሬ፣ ኢታንግ፣ ጋምቤላ ወረዳ እና ጋምቤላ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች ተጨማሪ የማረፊያ ክፍሎች መገንባታቸው በአዎንታዊ መሻሻል ተጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በጋምቤላ ክልል በማረሚያ ቤቶች የሙያ ማሰልጠኛ ማእከላት እንዲሁም ለቀለም ትምህርት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ከ8ኛ እና 10ኛ ክፍል በላይ መማር ለሚፈልጉ ታራሚዎች የተመቻቸ ዕድል አለመኖሩ፣ በፖሊስ ጣቢያዎች እና በኢ-መደበኛ ማቆያዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎች መኖራቸው እና የተራዘመ ቅድመ ክስ እስራት የሚስተዋል መሆኑ በአሳሳቢነት ተነስተዋል።


በተጨማሪም በማረሚያ ቤቶች እና ፖሊስ ጣቢያዎች ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ እና የቅሬታ ማቅረቢያ ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደረግ የተለየ እንክብካቤና ድጋፍ አለመኖር፣ በአብዛኛው ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች ያሉ ማደሪያ ክፍሎች የተጨናነቁ፣ የንጽሕና ጉድለት ያለባቸው እና ለመኝታ አገልግሎት የሚያስፋልጉ ቁሳቁሶች የሌሏቸው መሆኑ፤ እንዲሁም የመጸዳጃ ቤትን ጨምሮ የመጠጥ እና የንጽሕና መጠበቂያ ውሃ አቅርቦት ውስን መሆኑ፣ ለሕግ ታራሚዎች የምግብ አቅርቦት እና በቂ የሕክምና አገልግሎት አለመኖሩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተብለው ከቅረቡ ተግዳሮቶች መካከል የተገለጹ ናቸው።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢሰመኮ ባካሄደው የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሥራ የተለዩ የመብት ጥሰቶች እና አሳሳቢ ጉዳዮች የሚቀበሏቸው መሆኑን ጠቅሰው የቀረቡትን ምክረ ሐሳቦችን ተቀብለው ለመተግበር በትኩረት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ጋምቤላ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሙሉቀን አሰፋ በክትትል ሪፖርቱ የተለዩ ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። አክለውም “በማረሚያ ቤቶች እና በፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ በጀት የሚፈልጉትን መሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦትን ጨምሮ ተጨማሪ ሀብት መመደብ ሳያስፈልግ ወዲያውኑ ሊተገበሩ የሚገቡ የታራሚዎች እና የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።