የአፍሪካ ሕጻናት መብቶች እና ጥበቃ ቻርተር (African Charter on the Rights and Welfare of the Child) 30ኛ ዓመቱን ማስቆጠሩን ታሳቢ በማድረግ “አጀንዳ 2040: ለሕጻናት ምቹ የሆነች አፍሪካ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የአፍሪካ ሕጻናትን ቀን በማስመልከት፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በመነደፍ ወይም በመካሄድ ላይ የሚገኙ ግጭት የተከሰተባቸውን አካባቢዎች መልሶ የማቋቋም ተግባራት በአካባቢዎቹ የሚኖሩና የሚያድጉ ሕጻናትን ያማከሉ እንዲሆኑ ጠየቀ። በአጀንዳ 2040 እንደተመለከተው፣ የአጀንዳው ዋና ዓላማ በሚቀጥሉት ሁለት አስርት ዓመታት አፍሪካውያን ሕጻናት ክብር ያለው ሕይወት እንዲኖሩ ማስቻል እና ኢትዮጵያ በ1982 ዓ.ም. ያጸደቀችውን የአፍሪካ ሕጻናት መብቶች ቻርተር ለመተግበር የሚያግዱ ሁኔታዎችን መቅረፍ ነው። አጀንዳው ከዘረዘራቸው አስር ራዕዮች ወይም ግቦች (Aspirations) አንዱ ማንኛውም ልጅ ከግጭት፣ ከጦርነት እና ከሌሎች የተፈጥሮ እና አስቸኳይ ሰብአዊ ቀውሶች አስከፊ ተጽእኖ ስር እንዳይወድቅ መከላከል ነው።
በአገር አቀፍ ደረጃ ምግብ፣ መጠለያ፣ ሕክምና እና የተለያዩ ሰብአዊ ድጋፎች ያስፈልገዋል ተብሎ ከሚገመተው 23.2 ሚልዮን ሕዝብ መካከል፣12.5 ሚልዮኑ ሕጻናት መሆናቸውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የተሰሩ ጥናቶች ያመላክታሉ። እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው በግጭቶች ምክንያት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ተፈናቅለው ከሚገኙ 1.82 ሚልዮን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት (58%) ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት እና ታዳጊዎች እንደሆኑ ይነገራል። ኢሰመኮ የሚያከናውናቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሁኔታ ክትትል ስራዎች በተለይ በጊዜያዊ መጠለያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች በአብዛኛው ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውን ያመላክታሉ።
በተጨማሪም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ከሚነገረው 670 የገጠር እና 100 የከተማ ወረዳዎች መካከል፣ 359 የሚሆኑት ተፈናቃዮችን ተቀባይ ወይም አስተናጋጅ ሲሆኑ፣ 115 የሚሆኑት ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው የነበሩ ተመላሾች የሚኖሩባቸው ናቸው። ከተፈናቃዮች ጊዜያዊ መጠለያ ወረዳዎች መካከል በተለይም በአስቸኳይ የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ተብለው ከተለዩ 220 ወረዳዎች መካከል፣ 64ቱ በኦሮሚያ፣ 62ቱ በሶማሊ እና 39ኙ በትግራይ ክልሎች የሚገኙ ናቸው። በተ.መ.ድ የአስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪ ቢሮ (UNOCHA) በእ.ኤ.አ. የካቲት ወር 2021 ይፋ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው በወቅቱ ከተመዘገቡት ተፈናቃዮች መካከል 21 ሺህ 659 ወላጆቻውን ወይም አሳዳጊዎቻቸውን ያጡ ሕጻናት ናቸው። ተፈናቃዮች በመመለስ ላይ ባሉባቸው 115 የአገሪቱ ወረዳዎች እንዲሁ 78ቱ በእጅግ አሳሳቢ ወይም “extreme (severity 4) humanitarian condition” ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ይኸው ጥናት አክሎ ያሳያል።
በሌላ በኩል ከአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር 53% የሚሆነው ከ18 ዓመት በታች፣ እንዲሁም 43.5% ወይም 45 ሚልዮን 850 ሺህ በላይ የሚገመት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ15 ዓመት በታች መሆኑ በተለያዩ ሪፖርቶች ተመልክቷል። ከነዚህ መካከል ወደ 32 ሚልዮን የሚጠጉት “በዘርፈ ብዙ ድህነት” (multidimensionally poor) ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን የተ.መ.ድ የሕጻናት ድርጅት (UNICEF) እ.ኤ.አ. ጥር ወር 2019 ይፋ ያደረገው ጥናት ያሳያል። በሪፖርቱ እንደተገለጸው በዘርፈ ብዙ ድህነት የሚኖሩ ሕጻናት ማለት በአፍሪካ የሕጻናት መብቶች ቻርተርም ሆነ በዓለም አቀፉ የሕጻናት መብቶች ስምምነት (Convention on the Rights of the Child) ከተደነገጉት መብቶችና እና የምግብ፣ ጤና፣ የውሃ እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች መካከል ቢያንስ ሦስቱን የማያገኙ ማለት ነው። በተለይ ችግሩ በስፋት የሚታይባቸው ክልሎች አፋር፣ አማራ እና ሲዳማን ጨምሮ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቢሆኑም በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል እና በሶማሊ ክልሎችም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ ጥናቱ ያሳያል።
እነዚህ መረጃዎች በተናጠል ሲታዩ አሳሳቢ እንደሆኑት ሁሉ፣ በቅንጅት ሲታዩ በዋነኛነት ሁለት በፍጥነት ሊተገበሩ የሚገቡ የአረዳድና የአሰራር ለውጦችን ያስረዳሉ። በአንድ በኩል ግጭት ያለባቸውንና የነበረባቸውን አካባቢዎች መልሶ የማቋቋም እና የመገንባት ተግባራት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ በመሆኑ፣ እነዚህን እንቅስቃሴዎች ለማቀናጀት የሚቀረጹ ፖሊሲዎች፣ የሕግ ማዕቀፎችና አሰራሮች በአካባቢዎቹ የሚገኙ ሕጻናት ቁጥር አብላጫ እንደሆነ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። የሕጻናት ቁጥሩ ብዛት በአስቸኳይ ጊዜ ሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱም ሆነ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን መጠገን ጨምሮ በመካከለኛ ጊዜ የመልሶ መቋቋም ስራ ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ አስቀድሞ ማጥናትና ማካተት እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው።
በሌላ በኩል ለመካከለኛ ጊዜም ሆነ ለረዥም ጊዜ የሚያዙ አገር አቀፍና ክልላዊ የልማትና በተለይም የመጠለያ፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች የልማት አቅርቦት እቅዶች፣ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፎች እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስራዎች በሙሉ 55 ሚልዮን በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ18 በታች ከመሆኑ አኳያ ሊፈተሹና ሊሻሻሉ ይገባል። ይህም በተለይ ግጭት ባለባቸውና ከግጭት በመውጣት ላይ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕጻናት ከደረሰባቸው ሥነ-ልቦናዊና አካላዊ ጉዳት እንዲያገግሙ የሚያግዝ ድጋፍ አቅርቦት ማሟላትን ጨምሮ የአስፈጻሚና የፍትሕ ተቋማትን አሰራርና አደረጃጀት ዳግም መፈተሽ የሚያካትት ነው።
ይህንን በተመለከተ፣ በእ.ኤ.አ 2050 የኢትዮጵያ ሕጻናት ቁጥር የአፍሪካን ሕጻናት ቁጥር 6% እንደሚሆን እንደሚገመት በማስታወስ፣ የኢሰመኮ የሴቶችና ሕጻናት መብቶች ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ራኬብ መሰለ “የአፍሪካ ሕጻናት መብቶችና ጥበቃ አጀንዳ 2040 ሁኔታውን በተገቢው ሁኔታ ያገናዘበ የሃብት ምደባና የአሰራር ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የፖሊሲ አቅጣጫ ይሰጣል። ስለሆነም አጀንዳውን እንደ አቅጣጫ ጠቋሚ ማዕቀፍ ወስዶ የሕጻናትን ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከቱትም ሆነ ሌሎች አገር አቀፍ ፖሊሲዎችና አሰራሮች ሊጤኑና ሊሻሻሉ እንደሚገባ” አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል። ከአጀንዳ 2040 አስር ዋና ዋና ግቦች መካከል በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ነጥብም አባል አገራት በአፋጣኝ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ ሕጻናት ተኮር አገር አቀፍ የሕግ፣ የፖሊሲና የመዋቅር ማዕቀፍ ማስቀመጣቸውን መከታተል መሆኑን አክለው አስታውሰዋል።