የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአብዛኛው ውሎ እና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ (በተለምዶ አጠራሩ ጎዳና ተዳዳሪዎች ተብለው የሚታወቁ) ሰዎች ከጎዳና ላይ ተነስተው እንዲቆዩ የሚደረግበት በሸገር ከተማ፣ ሲዳ አዋሽ ወረዳ በተለምዶ “ሲዳሞ አዋሽ” በመባል የሚታወቅ አካባቢ የሚገኘው ጊዜያዊ ማቆያ ማእከል/ቦታን ጨምሮ በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ቢሮ ሥር የሚተዳደሩ ማእከላትን/ቦታዎችን በመጎብኘት እና ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው።

ኢሰመኮ ነሐሴ 24 እንዲሁም በጳጉሜን 2 እና 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በዚህ ማቆያ ማእከል/ቦታ ባደረገው ጉብኝት እንዲሁም፣ በማቆያ ማእከሉ የሚገኙ ሰዎችን እና የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮን ጨምሮ የሚመለከታቸውን የመንግሥት የጸጥታ አካላት በማነጋገር ክትትል አካሂዷል። በተጨማሪም የማቆያ ማእከሉ አስተባባሪዎች እና ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትን፣ በቦታው የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ባለሞያዎችን እና ተጨማሪ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኝ የነበረውን የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ኃላፊዎችን እና ባለሞያዎችን በማነጋገር ስለጉዳዩ አስፈላጊ መረጃና ማስረጃዎች አሰባስቧል፡፡

በማቆያ ማእከሉ የሚገኙት ሰዎች ውሎ እና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎች ሲሆኑ፤ አረጋውያን፣ ሕፃናት፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችም ይገኙበታል። እነዚህ በተለያየ ጊዜ ወደ ማእከሉ እንዲመጡ የተደረጉ ሰዎች ብዛት በየጊዜው ተለዋዋጭ ሲሆን፣ በሺዎች የሚገመቱ ሰዎች በማቆያ ማእከሉ ውስጥ ይገኙ እንደነበርና ኮሚሽኑ ክትትል ያደረገበትን ጊዜ ተከትሎ እና በዚህ ሪፖርት ዝግጅት ወቅት ቁጥሩ ከግማሽ በላይ ቀንሶ በመቶዎች የሚገመቱ ሰዎች መኖራቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

የማቆያ ማእከሉ አስተባባሪዎች ለኮሚሽኑ እንዳስረዱት የጊዜያዊ ማእከሉ ዋነኛ ዓላማ ከጎዳና ላይ እንዲነሱ የተደረጉትን ሰዎች በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም በማገዝ ወደ መጡባቸው አካባቢዎች እንዲመለሱ እና ከጎዳና ላይ ውሎና አዳር እንዲወጡ ማድረግ መሆኑንና በዚሁ መሠረት በተለያየ ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ መጡባቸው አካባቢዎች እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በማእከሉ ከሚገኙት ሰዎች ውስጥ 29 በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች፣ የጥበቃ እና የግንባታ ሠራተኞች እንዲሁም ሴቶችና ሕፃናት ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲለቀቁ እንደተደረገ የማእከሉ አስተባባሪዎች ገልጸዋል።

በማቆያ ማእከሉ ለሚገኙ ሰዎች ምግብ በቀን 3 ጊዜ እና የመጠጥ ውሃ የሚቀርብ ሲሆን፤ በአንጻሩ ይህ ጊዜያዊ ማቆያ ማእከል ለሰዎች መጠለያ ወይም ማቆያ ተብሎ የተዘጋጀና የተደራጀ ሳይሆን፤ ለኢንዱስትሪ ዕቃዎች ማከማቻ ተዘጋጅቶ የነበረ ስፍራ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያነት እንዲያገለግል የተደረገ ነው። ስለሆነም የተሟላ መሠረተ ልማት የሌለውና ለተፈለገበት ዓላማ ምቹ ባለመሆኑ በጣቢያው የሚገኙ ሰዎችን ሰብአዊ ክብር የጠበቀ አያያዝ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ የተሟላ የንጽሕና ቤቶች አለመኖራቸው እንዲሁም ለግል ንጽሕና መጠበቂያ የሚሆን የውሃና የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦት፣ የመኝታ አልጋ፣ ፍራሽና አልባሳት አለመኖራቸው፣ ለማደሪያ የተዘጋጀው ቦታ በቂ አየርና የፀሐይ ብርሃን የማያገኝ መሆኑ እና ከፍተኛ የንጽሕና ጉድለት ኮሚሽኑ ከተመለከታቸው ችግሮች ውስጥ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

በማቆያ ማእከሉ በቅርቡ በተባይ የሚተላለፍ ሕመም መከሰቱን ተከትሎ ለተላላፊ በሽታው የተጋለጡ ሰዎች ወደ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና እንዲሰጥ ተደርጓል። የተከሰተው ተላላፊ በሽታ በተባይ (በቅማል) የሚመጣ የተስቦ በሽታ (Relapsing fever) መሆኑን፣ በመጠለያ ጣቢያው ከነበሩ ሰዎች መካከል 190 ሰዎች በሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት ያገኙ መሆኑን እና ክትትሉ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ የ3 ሰዎች ሕይወት ያለፈ መሆኑን እና 3 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ሕክምና እያገኙ እንደነበር ከሕክምና ተቋሙ ማወቅ ተችሏል።

ኢሰመኮ ሚያዝያ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት እንዲሁም በመዲናዋ የሚደረጉ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባኤዎች እና ሌሎች ተመሳሳይ ኹነቶች ጋር በተያያዘ በርካታ በጎዳና ላይ ያሉ ሰዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በኃይል ከጎዳና ላይ እንዲነሱ በማድረግ በአንድ ስፍራ እንዲቆዩ የሚደረጉበት ሁኔታ በተመለከተ የክትትል ውጤቱን ይፋ ያደረገ መሆኑ የሚታወስ ነው። በተለይም ሰዎቹን መልሶ የማቋቋም ሥራ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚገባውና ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ከተመቻቹ በኋላ ሊተገበር እንደሚገባ፣ እንዲሁም ችግሩ ዘላቂ የፖሊሲ መፍትሔ የሚሻ መሆኑን በመጥቀስ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ምክረ ሐሳቦችን መስጠቱም ይታወሳል፡፡

ይህንን አስመልክቶ ኮሚሽኑ የሚያደርገው የክትትል እና የውትወታ ሥራ የሚቀጥል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ የሚመለከታቸው የከተማ የጸጥታ እና አስተዳደር አካላት በአሁኑ ወቅት በዚህ ማቆያ ማእከል የሚገኙ ሰዎችን አያያዝ ለማሻሻልና ሰብአዊ ክብርና አያያዝን ለማረጋገጥ የሚያስችል በቂ የምግብ፣ የውሃ፣ የመኝታ፣ የንጽሕና እና የሕክምና አገልግሎቶችን በአፋጣኝ ሊሟሉ ይገባል።

ሰዎችን በግዳጅ ወደ አንድ ማቆያ ማእከል/ቦታ ማስገባት ወይም ለኑሮ ከመረጡት ቦታ ወደ ማይፈልጉበት አካባቢ እንዲሄዱ ማስገደድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚያስከትል በመሆኑ፤ ይህ አስገዳጅ አሠራር በአስቸኳይ እንዲቆም በማድረግ በጎዳና ላይ ያሉ ሰዎችን ከጎዳና ላይ ማንሳትና ተገቢ አገልግሎቶችን መስጠት በፈቃደኝነትና አስፈላጊ ሁኔታዎችን ሁሉ በማመቻቸት ሊተገበር የሚገባ በመሆኑ በአስቸኳይ የእርምት እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።