የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከፕሮጀክት ኤክስፔዳይት ጀስቲስ (Project Expedite Justice, PEJ) ጋር በመተባበር በሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ ምርመራ እና ስነዳ ላይ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል።
በኢሰመኮ፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻዎች መካከል ያለውን ትብብርና ቅንጅት ማጠናከርን ዓላማ ባደረገው ውይይት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በሲዳማ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሰጪ አካላት ተሳትፈዋል።




በውይይት መድረኩ ኢሰመኮን ጨምሮ የሦስት ተቋማት የሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ ምርመራ እና ስነዳን የተመለከቱ ገለጻዎች፣ መልካም ተሞክሮዎች እና ተግዳሮቶች ቀርበዋል። በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ ምርመራ እና ስነዳ ፅንሰ ሐሳባዊ ማብራሪያ፣ የሰብአዊ መብቶች ስነዳ ዐይነቶች፣ የስነዳ አስፈላጊነት፣ በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና ማስፋፋት ላይ ኢሰመኮ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚጋሯቸው ጉዳዮች፣ በሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ መካከል ያለው ልዩነት እና አንድነት እንዲሁም ተግባራዊ ሊሆኑ የሚገቡ የሰብአዊ መብቶች መርሖች፣ የሰብአዊ መብቶች ክትትል፣ ምርመራ እና ስነዳ ወሰን (scope) እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ገለጻ ተድርጓል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ገመቹ በሰብአዊ መብቶች ምርመራ እና ስነዳ እንዲሁም በአጋርነት መሥራትን በተመለከተ የሲቪል ማኅበራት የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች አቅርበዋል። በተጨማሪም የሲቪል ማኅበረሰብ ባለሙያዎች እንደ ኢሰመኮ ዐይነት ያለመከሰስ እና ያለመታሰር መብት እንዲኖራቸው፣ ለሚያከናውኗቸው ምርመራዎች መረጃ ለሚሰጡ ምስክሮች ጥበቃ እንዲኖራቸው የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ እንዲደረግ፣ ኢሰመኮ ከሲቪል ማኅበራት እገዳ ጋር በተያያዘ የጀመረውን የምርመራ ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም በአጠቃላይ በሲቪል ምህዳሩ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በሚያሳድሩ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንዲሠራ የመፍትሔ ሐሳብ አቀርበዋል።


በመጨረሻም የፕሮጀክት ኤክስፔዳይት ጀስቲስ ዋና ዳይሬክተር ሲንቲያ ታይ የሲቪል ማኅበራት እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት በስነዳ እና በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምርመራ ያላቸው ሚና ላይ ገለጻ ሲያደርጉ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ስነዳ አስፈላጊነት፣ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት እና ሲቪል ማኅበረሰብ አብሮ መሥራት ያለው ጠቀሜታ እንዲሁም መመዘኛዎችን አንስተዋል። በተጨማሪም ተቋማቸው በሱዳን የተመለከተውን መልካም ተሞክሮ አቅርበዋል።


ተሳታፊዎች ኢሰመኮ እና ሲቪል ማኅበራት በቅርቡ የጀመሩትን ቅንጅታዊ አሠራር አጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ ኢሰመኮ ያለውን ትልቅ ዐቅም በመጠቀም ለሲቪል ማኅበራት መብት ጥበቃ አስተዋጾ ያላቸውን እንዲሁም የዐቅም ግንባታ ሥራዎችን እንዲሠራ እና መንግሥት እና ሲቪል ማኅበራት ተቀራርበው መሥራት እንዲችሉ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ጠይቀዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ የሰብአዊ መብቶች ሥራ በከፍተኛ ፈተናዎች ውስጥ ጭምር የሚከናወን መሆኑን አስታውሰው፣ የተጀመረው ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኢሰመኮ ያለውን ዝግጁነት ገልጸዋል። አክለውም ከሲቪል ማኅበራት ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ለማጠናከርና ተናቦ ለመሥራት አስቻይ የሆነ የኢሰመኮ-ሲቪል ማኅበራት ማስተባበሪያ መድረክ በማቋቋም ተቋማቱ በጋራ ዕያቀዱና እየተገበሩ መሆኑን አስረድተዋል።